በሱዳን መስጂድ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት 78 ሰዎች መገደላቸው ተነገረ

በሱዳን ዳርፉር ክልል በአንድ መስጂድ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ከ70 በላይ ሰዎች መገደላቸውን አንድ ከፍተኛ የሕክምና ምንጭ ለቢቢሲ ተናገሩ።

አርብ ዕለት በኤል-ፋሸር ከተማ ውስጥ ለተፈጸመው ጥቃት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ተጠያቂ ነው የሚል ክስ የቀረበበት ቢሆንም ቡድኑ ግን ኃላፊነቱን አልወሰደም።

በሱዳን ውስጥ እየተካሄደ ሁለት ዓመት ባለፈው የእርስ በርስ ጦርነት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና የሱዳን ሠራዊት እየተፋለሙ ይገኛሉ።

በዳርፉር የሱዳን ጦር ሠራዊት የመጨረሻዋ ጠንካራ ይዞታ የሆነችውን እና ከ300 ሺህ በላይ ሕዝብ የሚኖርባትን ኤል-ፋሸርን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር በሚያደረገው ፍልሚያ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ድል እየቀናው ነው።

አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደተናገረው በአርብ ጠዋቱ የጸሎት ወቅት የተፈጸመው የድሮን ጥቃት በርካታ ሰዎችን ገድሏል።

የሕክምና ምንጩ እንዳሉት ደግሞ በጥቃቱ 78 ሰዎች ሲገደሉ 20 የሚደርሱ ደግሞ የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ነገር ግን ከመስጂዱ ፍርስራሽ ውስጥ ሰዎችን የማውጣቱ ተግባር ሳይቋረጥ ቀጥሏል።

በከተማዋ ምዕራባዊ ክፍል ውስጥ በሚገኘው መስጂድ አቅራቢያ በጨርቅ እና በብርድ ልብስ የተሸፈኑ ወደ 30 የሚጠጉ አስከሬኖችን የሚያሳይ ምሥልን ትክክለኝነት ቢቢሲ ቬሪፋይ ለማረጋገጥ ችሏል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከአንድ ዓመት በላይ በከበባው ውስጥ ባቆያት በኤል-ፋሸር ላይ በዚህ ሳምንት አዲስ ጥቃት ከፍቷል። ከፍተኛ ጥቃት በከተማዋ አቅራቢያ በሚገኝው እና የተፈናቀሉ ሰዎች መጠለያ በሆነው አቡ ሹክ ካምፕ ላይ መፈጸሙን መፈጸሙን ዘገባዎች አመልክተዋል።

ጦርነቶችን የሚከታተለው የዬል ዩኒቨርስቲ የሰብአዊ እርዳታ ማዕከል እንዳመለከተው የሳተላይት ምሥሎች የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አብዛኛውን የመጠለያ ጣቢያውን ክፍል ተቆጣጥሮታል።

ማዕከሉ እንዳለው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የሱዳን ጦር ኃይል አጋር የሆኑ ጥምር ኃይል ተብለው የሚጠሩት የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች ዋና ማዘዣ ወደ ሆነው ስፍራ መግባታቸውን የሳተላይት ምሥሎች ያሳያሉ።

ዋና ማዘዣው የሚገኘው በቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅጽር ጊቢ ውስጥ ሲሆን፣ ቦታውም ለመከላከያነት የሚያገለግለ ወሳኝ መስመር መሆኑ ይነገርለታል።

የቢቢሲ የመረጃ ማጣሪያ የተመለከተው ምሥል የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች ውድ በሆነው ጊቢ ውስጥ እንዳሉ አረጋግጧል። ነገር ግን ኃይሉ ስፍራውን ሙሉ ለሙሉ ስለመቆጣጠሩ ግልጽ አይደለም።

ይህ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ግስፋሴ የኤል-ፋሸር አየር ማረፊያን እና የሠራዊቱ ዋና ማዘዣ በቡድኑ የቀጥታ ዒላማ ክልል ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል።

የዬል ዩኒቨርስቲ ማዕከል እንደሚለው የሱዳን ጦር በአስቸኳይ ደጋፊ ኃይል ካልደረሰለት ኤል-ፋሸር በፈጥኖ ደራሹ ኃይል ቁጥጥር ስር ትገባለች።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከተማዋን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ከቻለ በሱዳን ምዕራባዊ ክፍል ላይ ያለውን ይዞታ በማጠናከር ጦር ሠራዊቱ ሰሜን ምሥራቁን የአገሪቱን ክፍል ስለሚቆጣጠር ሱዳንን በሁለቱ ኃይሎች መካከል ይከፍላታል።

የሱዳን ጉዳዮች ተንታኞች እንደሚሉት በከተማዋ ያሉትን አብዛኞቹ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጠላት የሚላቸው ጎሳዎች አባላት በመሆናቸው ዒላማ ሊያደርጋቸው ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

አርብ ዕለት የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው ሪፖርት ሁለቱም ኃይሎች ከተቀናቃኛቸው ጋር ወግነዋል የሚሏቸውን ሰዎች በማጥቃት ግጭቱ "ጎሳን መሠረት ወዳደረገ ሁኔታ እያሸጋገሩት ነው" ብሏል።

የመንግሥታቱ ድርጅት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች አረብ ባልሆኑ ማኅበረሰቦች ላይ በተቀናጀ ሁኔታ የሚካሄድ የዘር ማጽዳት ፖሊሲ እንዳለው መረጃዎችን አጠናቅረዋል።

የበጎ አድራጎት ድርጅት የሆነው ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (አርኤስኤፍ) በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወታደሮች "ኤል-ፋሸርን አረብ ካልሆኑ ማኅበረሰቦች 'ስለማጽዳት' ያላቸውን ዕቅድ ተናግረዋል" ብሏል።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከዚህ ቀደም "ከጎሳ ግጭት ጋር የሚያገናኘኝ ነገር የለም" በማለት እንዲህ ያለው ክስ እንደማይመለከተው በመግለጽ አስተባብሏል።