“የመጀመሪያ የጥብቅና ሥራዬ የአባቴን ገዳይ መፋረድ ነበር”

የፎቶው ባለመብት, Salman Saeed
ሻጉፍታ ታባሱም አሕመድ ሕግ ለማጥናት የወሰነችው የቤተሰቧን ምክር ሰምታ ነው።
ጠበቃ መሆን አትፈልግም ነበር።
አባቷ ሲገደሉ ግን ሕግ ውስጥ ለመግባት ወሰነች።
የአባቷን ገዳዮች በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ 16 ዓመት ወስዶባታል። ለቢቢሲዋ ዘጋቢ ሜጋን ሞሐን ታሪኳን እንዲህ አካፍላለች።

አባቴ ዶ/ር ታህር አሕመድ በተገደለበት ቀን ከሆኑ ነገሮች መካከል ከፊሉን በደንብ ሳስታውስ፣ ከፊሎቹ ደግሞ ጠፍተውብኛል።
አርብ ቀን ነበር። ሰዓቱ ግን ትዝ አይለኝም።
ክፍሉ ትዝ ይለኛል። ማን ክፍሉ ውስጥ እንደነበረ ግን አላስታውስም።
የቤታችን ስልክ ሲጠራ አስታውሳለሁ። ማን ስልኩን እንዳነሳ ግን ረስቼዋለሁ።
የደወለው ወንድሜ ነበር።
“ተገድሏል” አለን። ሕይወቴ ተገለባበጠ።
እናቴ ታለቅስ ጀመር።
የአባቴ አስከሬን ራጅሻይ ዩኒቨርስቲ የውሃ ማጠራቀሚያ ውስጥ ተገኘ።
በዩኒቨርስቲው ጂኦሎጂ ክፍል መምህር ነበር።
በባንግላዲሽ መዲና ዳካ በሚገኘው የወንድሜ ቤት ዘመድ አዝማድ ተሰባሰበ።
አባቴ ጠፍቶ ስለነበር ወንድሜ ሊፈልገው ወደ ባንግላዲሽ እና ሕንድ ድንበር ከተማ ራጅሻይ ሄዶ ነበር።
ለምን? እንዴት? ማን ነው ገዳዩ? እያለ መላው ዘመድ አዝማድ ይጠይቅ ጀመር።
አባቴ ቅንጡ መኪና ከመግዛት ይልቅ በሕዝብ ትራንስፖርት መሄድ ይመርጥ ነበር።
ተማሪዎቹ ያከብሩት ነበር።
በአገራችን ባልተለመደ ሁኔታ አስቤዛ የሚገዛ፣ የሚያበስል ሰው ነበር።
ይሄንን የመሰለ ሰው ማን ይገድለዋል?
አባቴ ከዳካ ወደ ራጅሻይ የሄደው በአውቶብስ ነበር።
የዩኒቨርስቲው ውስጥ ያለው ወከባና ግርግር ያስደስተዋል። ልጅ ሳለሁ የምንኖረው እዚያ ነበር።
እኔና ወንድሜ ሳንዚድ ጊዜ የምናሳልፈው ከሌሎች የአስተማሪ ልጆች ጋር ነበር።
ደስ የሚል ኑሮ አሳልፈናል።
ከዚያ ኑሯችንን በዳካ አደረግን።
ሳንዚድ በአንድ ትልቅ መሥሪያ ቤት ውስጥ የሰው ሀብት አስተዳደር መሥራት ጀመረ።

የፎቶው ባለመብት, Salman Saeed
ዩኒቨርስቲ ስገባ ሕግ አጠናሁ።
ግን ጠበቃ መሆን አልፈልግም ነበር።
ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ባልሆነ ተቋም ውስጥ መሥራት ወይም አስተማሪ መሆን ነበር ሐሳቤ።
አባቴ ግን ጠበቃ እንድሆን ፈለገ።
ምናልባት ቤተሰባችን ጠበቃ እንደሚያስፈልገው ቀድሞ አውቆ ይሆናል።
ዩኒቨርስቲ የገባሁት እአአ በ2006 ነው።
እናቴ ዳካ አብራኝ ለመኖር መጣች።
አባቴ በሞተበት ሳምንት ሊጠይቀን ዳካ መጥቶ ነበር።
ከዚያ ወደ ራጅሻይ ሄደ።
ሰላም መድረሱን ማታ 3 ሰዓት ለእናቴ ደውሎ ነገራት።
ከዚያ በኋላ ይተኛል ብዬ አስባለሁ።
ኋላ ላይ ፖሊሶች ለብሶት የነበረውን ሱሪ መኝታ ቤቱ ተሰቅሎ አግኝተውታል።
እናቴን አዋርቷት ብዙም በሕይወት አልቆየም።
የሞተው ማታ 4 ሰዓት ነው።
አባቴ ስለ ዩኒቨርስቲው እጣ ፈንታ ውይይት ለማድረግ ነበር የሄደው።
ውይይቱን የሚያደርገው ከዶ/ር ሚያ ሞሐመድ ሞሂዲን ጋር ነበር።
ዶ/ር ሚያ በአንድ ወቅት የቤተሰቡ የቅርብ ሰው ናቸው።
አንድ ወቅት ላይ ግን ከአባቴ ጋር ተቆራረጡ።
በዶ/ር ሚያ የጥናት ጽሑፍ ውስጥ የተሰረቁ ጽሑፎች አባቴ አግኝቶ ነበር።
ይህንንም ለትምህርት ክፍሉ አሳውቋል።
ጉዳዩን የሚመረምር ስብሰባም ተጠርቷል።
አባቴ ስብሰባውን አልተካፈለም። ስልክም አያነሳም ነበር።
ቤት ጠባቂው ዣህጊር አልም አባቴ ቤት እንዳልገባ ተናገረ።
እናቴ ነገሩ አሳስቧት ወንድሜን እንዲያጣራ ላከች።
ወንድሜ የአባቴን አስክሬን ያገኘው በነጋተው ነበር።
ከዚያ የግድያ ምርመራ ተጀመረ።
የአባቴ መገደል ትልቅ ዜና ሆነ። ሁሉም ሰው ስለ ቤተሰቤ ማውራት ጀመረ።
ማን ገደለው? የሚለው በርካቶችን አነጋገረ።
አባቴ በቴሌቭዥን ይታይ፣ ጋዜጣ ላይ ፎቶው ይወጣ ጀመር።
ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃንም ግድያውን ዘገቡ።
የቤተሰባችን ሰቆቃ የአገር መነጋገሪያ ሆነ።
የተከበረ የዩኒቨርስቲ መምህርን ማን ይገድላል? እየተባለ ተወራ።

የፎቶው ባለመብት, Salman Saeed
አባቴ ከመገደሉ በፊት ድብደባ ደርሶበታል።
ወንድሜና እናቴ ከፖሊሶች ጋር በምርመራው እየተባበሩ ነበር።
ከሳምንት በኋላ ዶ/ር ሚያ፣ ወንድማቸው፣ የባለቤታቸው ወንድምና አንድ ሌላ ሰው በግድያ ተጠርጥረው ታሰሩ።
ዶ/ር ሚያ አባቴን እንዲገድሉ እንዳግባቧቸው ለፍርድ ቤት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
አባቴን ከገደሉ ገንዘብ፣ ኮምፒውተርና የዩኒቨርስቲ ሥራ እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸው ነበር።
ዶ/ር ሚያ ድርጊቱን እንዳልፈጸሙ ተከራክረዋል።
በ2008 አራቱ ግለሰቦች ጥፋተኛ ሆነው ተገኙ። የሞት ፍርድም ተላለፈ።
ግን አራቱ ግለሰቦች ይግባኝ ብለው ጉዳዩ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመራ።
እናቴና ወንድሜ ለአባቴ ፍትሕ ለማስገኘት ያላደረጉት ጥረት የለም።
እኔ ግን ምንም እያደረግኩ እንደሆነ አልተማኝም።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሲተላለፍ ገና ወጣት ነበርኩ።
አባቴ ከሞተ በኋላ ትምህርቴ ላይ ብቻ እንዳተኩር ቤተሰቤ ይገፋኝ ነበር።
በገንዘብም በሥነ ልቦናም ይደግፉኝ ነበር።
ጊዜዬን የማጠፋው የሕግ መጻሕፍት በማንበብ ነበር።
ግን ምን መሥራት እንዳለብኝ አልወሰንኩም።
በ2011 የአባቴ ግድያ ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተወሰደ።
ዶ/ር ሚያ በዋስ እንዲወጡ ተወሰነ።

የፎቶው ባለመብት, Salman Saeed
ዶ/ር ሚያ ከ10 በላይ ጠበቆች ነበሯቸው።
በዚህ ወቅት ነው ጠበቃ ለመሆን የወሰንኩት።
የሕግ ዲግሪዬን ተጠቅሜ የአባቴን ገዳይ ለመፋረድ ቆርጬ ተነሳሁ።
ለአባቴ ፍትሕ ማምጣት እንደምችል እራሴን አሳመንኩ።
ከተጠርጣሪዎቹ ሁለቱን አውቃቸዋለሁ። ፖሊሱንም አውቀዋለሁ።
2012 ላይ ስመረቅ ዐቃቤ ሕጉን ማገዝ ጀመርኩ።
በባንግላዲሽ ብዙም ሴቶች በሕግ ዘርፍ አይታዩም።
ሌሎች የፍርድ ቤት ጉዳዮችን ትቼ የአባቴን ክስ ብቻ እከታተል ነበር።
በ2013 ከፍተኛው ፍርድ ቤት ዶ/ር ሚያን በሞት ለመቅጣት የተላለፈውን ውሳኔ አጸደቀ።
ሌሎቹ ሁለት ተከሳሾች ግን ፍርዳቸው ወደ ዕድሜ ልክ እስራት ተቀነሰላቸው።
የአባቴ ቤት ተጠባቂ አንድ ተከሳሽ ነበር።
የዶ/ር ሚያን ጠበቆች የተከሳሾቹን ጉዳይ ከከፍተኛው ፍርድ ቤት ውጭ ከፋፍለው ይግባኝ አሉ።
ያኔ አለ የሚባል ሰነድ ማሰባሰብ ጀመርኩ።
ወንጀሉ እንዴት እንደተፈጸመ ለማሳየት ማስረጃ እያሰባሰብኩ ነበር።
የምተኛው አምሽቼ ነበር። ቅዳሜ እና እሑድ ሳይቀር እሠራ ነበር።
ብዙ የረመዳን ዓመት በዓል ያሳለፍኩት ፍትሕ ለማግኘት በመጸለይ ነው።
እኛ ለፍርድ ቤቱ ያዘጋጀነው የማስረጃ ዝርዝር እስከሚታይ ስምንት ዓመት ጠብቀናል።
በዚህ ጊዜ በ30ዎቹ ዕድሜ ክልል ነበርኩ።

የፎቶው ባለመብት, Salman Saeed
ዶ/ር ሚያ ተጽዕኖ ፈጣሪና ሀብታም ናቸው።
በባንግላዲሽ ፖለቲከኞች ዘንድ ተደማጭነት አላቸው።
ብዙ ጠበቆችም ነበሯቸው።
ከአባቴ ግድያ ነጻ እንዲወጡ ጠበቆቻቸው በጽኑ ታግለዋል።
አባቴና ዶ/ር ሚያ ጓደኞች እንደሆኑና አባቴ በዶ/ር ሚያ ስለመገደላቸው አካላዊ ማስረጃ እንደሌለ ተከራክረዋል።
ሦስቱ ተከሳሾች ግን የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
እስከ 2022 ፍትሕ አላገኘንም።
ከፍተኛው ፍርድ ቤት ዶ/ር ሚያ ከግድያው ተጠያቂ መሆናቸውን የፈረደው በ2022 ነው።
የሞት ቅጣቱ ተፈጻሚ እንዲሆንም ወስኗል።
በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቤተሰባችን ደስተኛ ነው።
ያለፉት 16 ዓመታት ለቤተሰቤ እንዴት ከባድ እንደነበሩ ለመግለጽ ቃላት የለኝም።
የአባቴን አሟሟት ሳስብ ቤተሰባችን እስከወዲያኛው ሰላም ያገኛል ብሎ ማሰብ ይከብደኛል።
ወጣትነቴን ያሳለፍኩት ለአባቴ ፍትሕ በመታገል ነው።
ብዙዎች ለምን ቤተሰብ አትመሠርችም ብለው ይጠይቁኛል።
የአባቴ ገዳዮች ከሞቱ በኋላ ቤተሰብ እመሠርት ይሆናል።
አባቴ ዓለሜ ነበር።
ጨዋ፣ ብልህና በጎ ሰው ነበር።
ለአባቴ ስል ለፍትሕ መታገል አላቆምም።












