ኢላን መስክ የኤክስ ተጠቃሚዎች ሌላ ሰው ‘ብሎክ’ እንዳያደርጉ አደርጋለሁ አለ

የፎቶው ባለመብት, ETIENNE LAURENT/EPA-EFE/REX/SHUTTERSTOCK
የቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ስሙ ኤክስ ባለቤት የሆነው ኢላን መስክ ‘ብሎክ’ የተሰኘውን ቁልፍ እንደሚያስወግድ ገልጧል።
በእንግሊዝኛው ብሎክ የተሰኘው ቁልፍ ተጠቃሚዎች የማይፈልጉት ሰው የሚያስወግዱበት አማራጭ ነው።
የኤክስ አለቃ እንዳለው ተጠቃሚዎች ሰዎችን ብሎክ ማድረግ የሚችሉት በመልዕክት መላላኪያ ሳጥን ውስጥ ብቻ ይሆናል::
ነገር ግን በርካታ ሰዎች ይህ ቁልፍ ከተነሳ ተጠቃሚዎች የማይፈልጉትን አሊያም ጥቃት የሚያደርስባቸውን ሰው ለመሸሽ ይቸገራሉ ሲሉ የኢላንን ሐሳብ ተቃውመዋል።
ኢላን መስክ የቀድሞውን ትዊተር በ44 ቢሊዮን ዶላር ከገዛ በኋላ ከስም ቅያሪ ጀምሮ ካደረጋቸው በርካታ ለውጦች ይህ አንደኛው ነው።
አሁን ባለው አማራጭ አንድ የኤክስ ተጠቃሚ ሌላ አካውንት ‘ብሎክ’ ካደረገ የሚለጥፉትንም ማየት አይችልም፤ ብሎክ የተደረገው አካውንትም እንዲሁ የሌላኛውን ተጠቃሚ ይዘት ማየት እንዳይችል ይሆናል።
ከዚህ በተጨማሪ ብሎክ የተደረጉ አካውንቶች ብሎክ ወዳደረጋቸው ሰው መልዕክት መላክም አይችሉም።
የቀድሞው የትዊተር መሥራች ጃክ ዶርዚ፤ ከኢላን መስክ ጋር መስማማቱን በመግለጥ “መቶ በመቶ ትክልል። ‘ሚዩት’ ማድረግ ብቻ” ሲል ፅፏል።
ነገር ግን ‘ሚዩት’ የተሰኘው አማራጭ ትንኮሳ፣ ጥቃት እና ክትትል የሚያደርጉ ሰዎችን ለማስቆም በቂ አይደለም የሚል ሐሳብ ያላቸው ተጠቃሚዎች ስጋታቸውን እየገለጡ ይገኛሉ።
‘ሚዩት’ የተባለው አማራጭ ደግሞ አንድ አካውንት ይዘት ሲለጥፍ ማስታወቂያ ከመላክ ውጭ ጥቅም የለውም።
አንድ ተጠቃሚ ሌላ አካውንትን ሚዩት አደረገ ማለት ሌሎች የሚለጥፉትን ማየት አይችልም፤ አሊያም ምላሽ መስጠት ይሳነዋል ማለት አይደለም።
አንድ የኤክስ ተጠቃሚ የኢላን መስክን ውሳኔ “ትልቅ ስህተት” ብሎት ኤክስ ላይ “ሌሎች ሰዎች ሊያይዋቸው የማይፈልጉ በጥባጭ ተጠቃሚዎች አሉ” ሲል ስጋቱን አጋርቷል።
ቢሆንም ብሎክ የተባለውን አማራጭ ማንሳት የመተግበሪያ [አፕ] ማውረጃዎቹ አፕ ስቶርና ጉግል ፕለይን አቋም የሚፃረር ነው።
ሁለቱ ግዙፍ አፕ ማውረጃዎች፤ ማሕበራዊ ሚድያዎች ተጠቃሚዎች የማይፈልጉትን ሰው የሚያስወግዱበት አማራጭ እንዲኖር ያስገድዳሉ።
ኢላን መስክ በውሳኔው ከፀና ኤክስን ከእነዚህ የአፕ ቋቶች ማውረድ አይቻልም ማለት ነው።
አዲሱ ፖሊሲ የሚፀና ከሆነ ሰዎች ከዚህ ቀደም ‘ብሎክ’ ያደረጓቸው አካውንቶችን ከብሎክ ነፃ ይወጣሉ ወይስ አይወጡም የሚለው ግልጥ አይደለም።
ነገር ግን አሁንም ቢሆን ተጠቃሚዎች አካውንታቸውን ‘ፕራይቬት’ ማድረግ ይችላሉ። ይህ ማለት የሚፈልጉት ሰው ብቻ የሚለጥፉትን ይዘት እንዲመለከት ማድረግ ይችላሉ ማለት ነው።
የዓለማችን ልጥጡ ሃብታም ኢላን መስክ ማሕበራዊ ሚድያውን የግሉ ካደረገ በኋላ በርካታ ለውጦች ተግባራዊ አድርጓል።
ከእነዚህ መካከል የኩባንያውን ከፍተኛ ሥራ አስፈፃሚዎች ማባረርና ተጠቃሚዎች ‘ብሉ ቲክ’ እንዲገዙ ማድረግ የሚጠቀሱ ናቸው።
ኢላን መስክ ለውጦች ያደረገውን ያክል አንዳንድ ጊዜ አንድ ውሳኔ አስተላልፋለሁ ብሎ ካወጀ በኋላ በቃሉ ባለመፅናቱ ብዙ ጊዜ ትዝብት ላይ ወድቋል።
ኤክስ ለጋዜጠኞች ብዙውን ጊዜ ምላሽ ስለማይሰጥ የኢላንን ውሳኔ ማጣራት ለመገናኛ ብዙኃን ከባድ ሆኗል።












