ትዳሯ የፈረሰው ብሪትኒ ስፒርስ “ስሜቴን በእንባ ብገልፀው ደስ ባለኝ” ስትል በፍቺው መደናገጧን ገለጠች

ብሪትኒ ስፒርስና ሳም አስጋሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፖፕ ሙዚቃ ኮከቧ ብሪትኒ ስፒርስ ትዳሯ የፈረሰው “ስቃዩን መሸከም ስላቃተኝ ነው” ስትል ስለትዳሯ መፍረስ ለመጀመሪያ ጊዜ አስተያየቷን ሰጠች።

የ29 ዓመቱ የቀድሞ ባሏ ሳም አስጋሪ “ሊፈቱ በማይችሉ ልዩነቶች” ምክንያት ባለፈው ሳምንት የፍቺ ወረቀት ማስገባቱ ተሰምቷል።

የፍቺ ወረቀቱ እንደሚጠቁመው ከፍቺው ጋር የተያያዙ የሕግ አማካሪዎች ወጪን ብሪትኒ እንድትሸፍን እና ከፍቺ በኋላ በብሪትኒ ስፒርስ የገንዘብ ድጋፍ እንዲሰጠው ሳም ጠይቋል።

የ41 ዓመቷ ብሪትኒ ስፒርስ በበኩሏ ከሳም አስጋሪ ጋር የመሠረተችው ትዳር በመቋጨቱ “ትንሽ ደንግጫለሁ” ብላለች።

ስለትዳሯ መፍረስ በኢንስታግራም ገጿ ሐሳብ የሰጠችው ዘፋኟ “ለማንም የማስረዳት ኃላፊነት የለብኝም ምክንያቱም ይህ የማንም ጉዳይ አይደለም” የሚል ፅሑፍ ለጥፋለች።

“ለረዥም ጊዜ ጠንካራ ሆኜ ለመታየት ሞክርያለሁ። የኢንስታግራም ገፄ እኔ ፍፁም ሰው እንደሆንኩ ሊያስመስል ይችላል። ነገር ግን እውነታው ሌላ ነው፤ ይሄን ሁላችንም እናውቀዋለን።”

“የሚሰማኝን ስሜት በእንባ ብገልፀው ደስ ባለኝ ነገር ግን እንደሁልጊዜው ደካማ ጎኔን መደበቅ መርጫለሁ” ይላል የብሪትኒ ፅሑፍ።

አክላ ከዚህ በኋላም “ጠንካራ” ሆና እንደምትቀጥል ገልጣ “ኧረ እንዲያውም በመልካም ሁኔታ ላይ ነኝ” ብላለች።

ሳም አስጋሪ ኢራናዊ አሜሪካዊ ተዋናይ፣ ሞዴል እና የሰውነት ማጎልመሻ አሠልጣኝ ነው።

ሳም እና የፖፕ ኮከቧ የተገናኙት በአውሮፓውያኑ 2016 ብሪትኒ ስፒርስ ስላምበር ፓርቲ ለተሰኘው ሙዚቃዋ ቪድዮ ስትሰራ ነው።

ሳም፤ ብሪትኒ ስፒርስ በአባቷ ጄሚ ቁጥጥር ሥር በነበረችበት ወቅት ከዚህ እንድትላቀቅ ትልቅ ድጋፍ ሲያደርግ ነበር።

ብሪትኒ ከአባቷ ቁጥጥር ከወጣች ከወራት በኋላ ነው ከሳም ጋር ጋብቻ የመሠረተችው።

ጥንዶቹ በአውሮፓውያኑ 2021 መስከረም የጋብቻ ቃል-ኪዳን ገብተው ባለፈው ዓመት ሰኔ ነበር አነስ ባለ ሥነ-ሥርዓት የተጋቡት።

ታውዘንድ ኦክስ በተሰኘው የካሊፎርኒያ መንደር የተሰናዳው የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት እነ ማዶና፣ ፓሪስ ሒልተን እና ድሩ ባሪሙር የተጋበዙበት ነበር።

ጋብቻ ከመፈፀማቸው በፊት ጥንዶቹ የመጀመሪያ ልጃቸውን ሊቀበሉ ዝግጅት ላይ እንዳሉ ቢገልጡም የኋላ ኋላ በእርግዝና ችግር ምክንያት ሕልማቸው እውን ሳይሆን እንደቀረ አሳውቀዋል።

ነገር ግን በቅርቡ የጋብቻ ቀለበታቸውን አውልቀው መታየታቸውን ተከትሎ ጥንዶቹ ትዳራቸው እየተንገዳገደ እንደሆነ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ሲዘግቡ ቆይተዋል።

ሳም አስጋሪ በኢንስታግራም ገፁ “ከስድስት የፍቅርና መደጋገፍ ዓመታት በኋላ ሚስቴ እና እኔ ትዳራችንን ልንቋጭ ወስነናል” ሲል ፅፏል።

“ሁሌም ቢሆን አንዳችን ለሌላችን ያለን ፍቅር እና መከባበር ይቀጥላል። ሁሌም መልካሙ እንዲገጥማት እመኛለሁ።” ብሏል።