ኢትዮጵያ ለውጭ ኢንቨስተር የመጀመሪያውን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ፈቃድ ለሳፋሪኮም ሰጠች

ለሳፋሪኮሙ ኤምፔሳ

የኢትዮጵያ መንግሥት ለውጭ ኢንቨስተር የመጀመሪያ የሆነውን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ፈቃድ ለሳፋሪኮም ሰጠች።

ፈቃዱ የተሰጠው ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 03/ 2015 ዓ.ም. ለሳፋሪኮሙ ኤምፔሳ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ሰጪ ተቋም መሆኑንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።

የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ፈቃድ መሰጠቱ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ሥርዓት ፈጠራዎችን ለማጎልበት እና በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ለማካተት የያዘውን ዓላማ የሚያንጸባርቅ መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባጋሩት መግለጫ ውስጥ ተካትቷል።

በአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ውስጥ በጥሬ ገንዘብ ላይ የተመሠረተውን የግብይት ሥርዓት በዲጂታል የክፍያ ሥርዓቶች መተካትን እና መስፋፋትን በጥብቅ እንደሚደግፍ ብሔራዊ ባንኩ በመግለጫው አስፍሯል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ክፍት ባደረገቻቸው የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓቶች ውስጥ የሞባይል ባንክ አገልግሎት እና የካርድ የባንክ አገልግሎት ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በፍጥነት መስፋፋቱን ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ በዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ላይ እየታየ ያለው ለውጥም በፍጥነት እያደገ ያለውን የፋይናንስ ሥርዓቱ ቀልጣፋ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ግልጽነት የተላበሰ እንደሚያደርገው ተጠቁሟል።

ኬንያ ከ14 ዓመታት በፊት የጀመረችው 'ኤምፔሳ' የተሰኘውን የሞባይል ገንዘብ ዝውውር ሥርዓት አሁን ላይ 72 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ እየተጠቀመው እንደሚገኝ ቮክስ ከተባለ ድረ ገጽ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

በሰባት አገራት አገልግሎት የሚሰጠው ኤምፔሳ 42 ሚሊዮን ደንበኞች እና 400 ሺህ ወኪሎች አሉት።

50 በመቶ የሚሆነው የኬንያ አጠቃላይ አገራዊ ምርት (GDP) በዚሁ ሥርዓት በኩል ይንቀሳቀሳል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም የመጀመሪያውን የግል የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት 'ካቻ ዲጂታል ፋይናንሻል ሰርቪሰ' ለተባለ ተቋም መሰጠቱ ተዘግቧል።

ካቻ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት በኢትዮጵያ ገበያ በተንቀሳቃሽ ስልኮች የተለያዩ የገንዘብ አገልግሎቶች ለማቅረብ የሚያስችል ፈቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በማግኘት በግሉ ዘርፍ ቀዳሚ መሆኑም መገለጹ የሚታወስ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኢትዮ ቴሌኮም ገንዘብ ለመቀበል፣ ለመላክ፣ የግብይት እና የአገልግሎትን ክፍያን ለመፈጸም እንዲሁም ከውጭ አገራት ገንዘብ መቀበል የሚያስችለውን ቴሌ ብር ከሁለት ዓመት በፊት መጀመሩ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ የፋይናንስ አገልግሎቶች በባንክ እና በመሰል ተቋማት ብቻ እየተሰጠ የነበረው የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ላይ ማሻሻያ በመደረጉ ነው ኢትዮ ቴሌኮም ከቴሌኮም አገልግሎት በተጨማሪ የፋይናንስ ሥርዓቱ ላይ መሳተፍ የጀመረው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም በመጋቢት እና በነሐሴ 2012 ዓ.ም. ሁለት መመሪያዎችን የክፍያ መፈጸሚያ መንገዶች እና አገልግሎቶችን ለማስተዳደር ያወጣ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ለባንኮች እና ለማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ብቻ ተዘግቶ የቆየውንም ዘርፍ ለሌሎች ድርጅቶች ክፍት መደረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ፓርላማ ባለፈው ዓመት የብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ ማሻሻያ ያጸደቀ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደምም የውጭ ኩባንያዎች በክፍያ ሥርዓት ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ በር ከፍቷል።

የኬንያው ግዙፍ የቴሌኮም ኩባንያ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ባለፈው መስከረም 26/2015 ዓ.ም. በአገሪቱ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ለ125 ዓመታት በላይ በመንግሥት የልማት ድርጅት በብቸኝነት ተይዞ የነበረውን የቴሌኮም ዘርፍ ክፍት በማድረግ የቴሌኮም ፈቃድ የሰጠችው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።

በኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ለመሰማራት በተደረገው ዓለም አቀፍ ጨረታ በኬንያው ሳፋሪኮም የሚመራው ጥምረት በ850 ሚሊዮን ዶላር ማሸነፉ ይታወሳል።

ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ የተሰኘው ይህ ጥምረት፣ በዘርፉ አሉ የሚባሉ ስመ ጥር የቴሌኮም ኩባንያዎችን እና ተቋማትን በቅንጅት የያዘ ሲሆን እነዚህም ሳፋሪኮም፣ ቮዳኮም ግሩፕ፣ ቮዳፎን ግሩፕ እና ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን እንዲሁም ሲዲሲ ግሩፕ የተካተቱበት ነው።