በፍሎሪዳ ዘርን መሠረት ባደረገ ጥቃት አንድ ነጭ ሦስት ጥቁሮችን ገደለ

ጃክሰንቫይል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በአሜሪካዋ ፍሎሪዳ ግዛት ዘርን መሠረት ባደረገ ጥቃት አንድ ነጭ ሦስት ጥቁር አሜሪካውያን መግደሉን ፖሊስ አስታወቀ።

በጃክሰንቪል በ20ዎቹ መጀመሪያ የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሆነ የተገለጸው ጥቃት አድራሽ ሦስቱን ሰዎች ተኩሶ ከገደለ በኋላ እራሱን ማጥፋቱን ፖሊስ አስታውቋል።

የፖሊስ አዛዡ ቲ ኬ ዎተርስ ሁለት ወንዶች እና አንዲት ሴትን የገደለው ግለሰብ ጥይት መከላከያ ለብሶ እንደነበረ እና ዓላማውን የዘረዘረበትን ዝርዝር ጽሑፍ ትቶ ማለፉን ገልጸዋል።

የከተማዋ ከንቲባ ዶና ዴጋን “ጥላቻ የተሞላበት ወንጀል የተፈጸመው” ዘረኛ በሆነ ግለሰብ ነው ብለዋል።

እስካሁን ማንነቱ ይፋ ያልሆነው ግለሰብ ሁለት መሳሪያዎችን ታጥቆ አንድ መደብር ውስጥ ከገባ በኋላ ነው ተኩስ ከፍቶ ሦስቱን ሰዎች የገደለው።

ይህ በጃክሰንቪል ከተማ ከወላጆቹ ጋር ይኖረው የነበረ በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የነበረ ወጣት ሊፈጽም ስላቀደው ተግባር ለወላጆቹ እና ለመገናኛ ብዙሃን ዝርዝር ጽሑፍ አስቀምጧል።

የፖሊስ አዛዡ እንዳሉት ጥቃት አድራሹ ታጥቋቸው ከነበሩት መሳሪያዎች መካከል በአንዱ ላይ የናዚ መልክት የሆነው የስዋስቲክ ምስል ተስሎበታል።

የፍሎሪዳ ሃገር ገዥ ሮን ዲሳንቲስ ጥቃት አድራሹን አብጠልጥለው “ሰዎችን ዒላማ ያደረገው በቆዳ ቀለማቸው ነው፤ ይህ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው” ብለዋል፤ በቀጣይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሪፓብሊካኖችን ወክለው ለመሳተፍ ዝግጅት ላይ የሚገኙት ፖለቲከኛ።

ዲሳንቲስ ጨምረው ግለሰቡ ለፈጸመው ተግባር ኃላፊነትን ከመጋፈጥ ይልቅ ፈሪዎች እንደሚያደርጉት እራሱን አጥፍቷል ብለዋል።

ዋይት ሃውስ የጅምላ ግድያውን በተመለከተ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንዲያውቁት ተደርጓል ብሏል።

የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ትልቅ የፖለቲካ አጀንዳ በሆነባት አሜሪካ፤ በጦር መሳሪያ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሕይወታቸውን የሚያጡ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር አሁንም እንደጨመረ ነው።

በአገሪቱ በመሳሪያ በመታገዝ የሚፈጸሙትን ጥቃቶች መዝግቦ የሚይዝ ድረ-ገጽ በተያዘው 2023 የአውሮፓውያን ዓመት ብቻ በአሜሪካ 28ሺህ ሰዎች በጥይት ተገድለዋል ይላል።