አርሰናል ነጥብ ሲጥል ማንቸስተር ዩናይትድ ከሁለት ጎል ዕዳ ተነስቶ ማሸነፍ ችሏል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሶስተኛው ሳምንት የፕሪሚዬር ሊግ መርሃ ግብር አርሰናል በሜዳው ነጥብ ሲጥል ማንቸስተር ዩናይትድ ከሁለት ጎል ዕዳ ተነስቶ ማሸነፍ ችሏል።
በኤሜሬትስ ስታድየም ፉልሃምን ያስተናገደው አርሰናል በጨዋታው መገባደጃ በተቆጠረበት ጎል ምክንያት 2 አቻ ተለያይቷል።
ፉልሃም በ57ኛው ሰከንድ የመጀመሪያዋን ጎል በማስቆጠር መሪነቱን ቢወስድም አቻ ለመሆን አርሰናል በሰጠው ምላሽ እንደተደሰተ አሠልጣኙ ማይክል አርቴታ ተናግሯል።
መድፈኞቹ በቡካዮ ሳካ ፍፁም ቅጣት ምት እና በኤዲ ንኬቲያህ ጎል አማካይነት መሪነት ቢወስዱም ድል ግን አልቀናቸውም።
ካልቪን ቤሲ በ83ኛው ደቂቃ ንኬቲያህ ላይ በሠራው ቅጣት ምክንያት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
በ10 ተጫዋቾች እየተፋለመ የነበረው ፉልሃም በጃዎ ፓሊንሃ ጎል ከሜዳው ውጭ አቻ በመውጣት ከአርሰናል ነጥብ ተጋርቷል።
ማሸነፍ ይገባን ነበር ያለው ማይክል አርቴታ አርሰናል ከአምናው በጣም የተሻሻለ ቡድን ሆኗል የሚል አስተያየት ሰጥቷል።
በተመሳሳይ በሜዳው በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጎል በማስተናገድ ጨዋታውን የጀመረው ማንቸስተር ዩናይትድ የኋላ ኋላ ድል ቀንቶታል።
ኖቲንግሃም ፎረስት በመጀመሪያዎቹ ሶስት ደቂቃዎች ሁለት ጎል በማስቆጠር ኦልድ ትራፈርድን ማስደንገጥ ቢችሉም ውጤቱን ማስጠበቅ ግን ተስኗቸዋል።
የማሸነፊያዋን ፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠረው የማንቸስተር ዩናይትዱ አምበል ብሩኖ ፈርናንዴዝ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ አምሽቷል።
የፎረስቱ ናይጄሪያዊ አጥቂ ታይዎ አዎንይ የመጀመሪያዋን ጎል ከሰከንዶች በኋላ ደግሞ ዊሊ ቦሊ አንድ ጎል በማከል ሁለት ለባዶ ሲመሩ ቆይተዋል።
ነገር ግን በ17ኛው ደቂቃ ክሪስቲያን ኤሪክሰን፤ በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ደግሞ ካሴሚሮ ከፌርናንዴዝ ያገኛትን ጎል ወደ ጎል በመቀየሩ ዩናይትድ አቻ መሆን ችሏል።
የኖቲንግሃም ፎረስቱ ተከላካይ ዳኒሎ፤ ራሽፈርድ ላይ በሠራው ጥፋት ምክንያት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ፈርናንዴዝ ወደ ጎል በመቀየር ለቡድኑ ሶስት ነጥብ አስገኝቷል።
ማንቸስተር ዩናይትድ 13 ጊዜ ከሁለት ለባዶ እና ከዚያ በላይ ከሆነ የጎል ዕዳ ተነስቶ በማሸነፍ የፕሪሚዬር ሊጉን ክብረ-ወሰን ጨብጧል።
በሌሎች ጨዋታዎች ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከሜዳው ውጭ ቦርንመዝን 2-0 ሲያሸንፍ ብሬንትፈርድና ክሪስታል ፓላስ አቻ ተለያይተዋል።
ድል የራቀው ኤቨርተን በሜዳው በዎልቭስ አንድ ለምን ሲረታ ዌስትሃም ዩናይትድ ወደ ብራይተን ተጉዞ 3-1 በመርታት አስደናቂ 3 ነጥብ ይዞ ተመልሷል።
አርብ ምሽት ቼልሲ በስታምፈርድ ብሪጅ ሉቶን ታውንን 3-0 መርታቱ ይታወሳል።
እሑድ በሚካሄዱ ጨዋታዎች በርንሊ ከአስተን ቪላ፤ ሼፊልድ ዩናይትድ ከማንቸስተር ሲቲ፤ ኒውካስል ከሊቨርፑል ይገናኛሉ።












