"አዞው" የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ምናንጋግዋ ተጭበርብሯል በተባለው ምርጫ ለሁለተኛ ዙር ተመረጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ከአጠቃላይ ድምጽ 52.6 በመቶ የሚሆነውን በማግኘት ለሁለተኛ ዙር መመረጣቸውን የአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን አስታወቀ።
ይሁን እንጂ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከፍተኛ የሆነ የምርጫ ማጭበርበር ተካሂዷል ያሉ ሲሆን ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ደግሞ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ መስፈርቶችን አላሟላም ብለዋል።
ኤመርሰን ምናንጋግዋ እአአ 2017 ላይ በቀድሞ መሪ ሮበርት ሙጋቤ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ከተፈጸመ በኋላ ወደ ስልጣን መምጣታቸው ይታወሳል።
ጭካኔያቸውን ለመግለጽ ዘ ክሮኮዳይል ወይም አዞው ተብለው የሚታወቁት ምናንጋግዋ ወደ ስልጣን በመጡ ወቅት ለአገሬ ሕዝብ አዲስ ተስፋን እሰጣለሁ ብለው ነበር።
ይሁን እንጂ የዚምባብዌ ዜጎች አሁንም ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት ውስጥ በድኅነት የሚኖሩ ሕዝቦች ናቸው።
ከዓለም ከፍተኛ የዋግ ግሽበት ካለባቸው አገራት መካከል ደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ተጠቃሽ ነች። ሐምሌ ወር ላይ የዋጋ ግሽበቱ ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረበት በ101 በመቶ ጭማሪ አሳይቶ ነበር። የሥራ አጥ ቁጥሩም ሰማይ ነክቷል። ከአጠቃላይ የዚምባብዌ ዜጎች 25 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው ሥራ ያላቸው።
ተቃዋሚዎችን በማፈን የሚታወቁት የ80 ዓመቱ ፖለቲከኛ ይህን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደሚያሸንፉ ቅድመ ትንበያዎች ተሰጥተው ነበር።
የዚምባብዌ ምርጫ ኮሚሽን የፕሬዝዳንቱ ዋነኛ ተፎካካሪ የሆኑት ኔልሰን ቻሚሳ የሚመሩት ‘ሲትዝንስ ኮአሊሽን ፎር ቼንጅ’ ፓርቲ 44 በመቶ ድምጽ ማግኘት ችሏል ብሏል።
እንደ ኮሚሽኑ ከሆነ ምናንጋግዋ ከአጠቃላይ ድምጽ 2.3 ሚሊዮን ሲያገኙ ቻሚሳ ያገኙት ድምጽ 1.9 ሚሊዮን ነው።
የምርጫ ውጤቱን ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲው አልቀበለውም ቢልም ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤቱ ግን የምርጫ ውጤቱን አጽድቆታል።
የቻሚሳ ፓርቲ ቃል አቀባይ በቀጣይ የምንወስደውን እርምጃ ለደጋፊዎቻችን ይፋ እናደርጋለን ሲሉ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ምርጫውን ለመታዘብ የአውሮፓ ኅብረት፣ የኮመንዌልዝ አገራት እንዲሁም የደቡብ አፍሪካ አገራት ቀጠናዊ ድርጅት (ሳዳክ) ተወካዮች በዚምባብዌ ተገኝተው ነበር።
ዓለም አቀፍ ምርጫ ታዛቢዎቹ ተቃዋሚዎች ሰልፍ እንዳያደርጉ መከልከላቸው፣ የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ አካሄድ፣ የቴሌቪዥን የአየር ሰዓት አደላደል ላይ እንዲሁም ድምጽ ሰጪዎችን በመዋከባቸው በምርጫ ሂደቱ ላይ ጥያቄ አለን ብለዋል።
የምናንጋግዋ ፓርቲ ዛኑ-ፒኤፍ ዚምባብዌ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ አገሪቱን ሲመራ ቆይቷል።
ዛኑ-ፒኤፍ ፓርቲ በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበርንም አሸንፏል።












