ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጎንደር በአጋቾቿ ለተገደለችው ህጻን ቁጣቸውን ለማሰማት የወጡ ሰዎች “በመንግሥት ኃይሎች” መገደላቸው ተነገረ
በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ የሁለት ዓመት ህጻን በአጋቾች መገደሏን ተከትሎ ቁጣቸውን ለማሰማት አደባባይ የወጡ ሰዎች ላይ በተከፈተ ተኩስ ቢያንስ አራት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ከቀናት በፊት የእገታ ማስለቀቂያ የተጠየቀባት እና ከሦስት ቀን በኋላ ተገድላ ለተገኘችው ህጻን ኖላዊት ዘገየ ፍትሕ ለመጠየቅ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ፒያሳ በሚባለው የከተማው አካባቢ ወጥተዋል።
ቢቢሲ ያናገራቸው አንድ ነዋሪ ‘ስሜቱን ለመግለጽ’ አደባባይ በወጣው ሕዝብ ላይ ጥቃት ተፈፅሞበታል ብለዋል።
አንድ የዓይን እማኝ “ፍትሕ ለመጠየቅ የወጣ ሕዝብ” በጥይት መመታቱን ተናግረው በጥቃቱ ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።
“የህጻኗን አስከሬን ይዞ ‘ድምጻችን ይሰማ፤ የጎንደር መታፈን ይብቃ’ ብሎ እሪ እያለ ወጣ” ያሉት ሌላ እማኝ ሰልፈኞቹ ድምጻቸውን አሰምተው እየተመለሱ እያለ ግን የመንግሥት ሹማምንትን የሚጠብቁ እና የሚያጅቡ ናቸው ባሏቸው ኃይሎች ተኩስ እንደተከፈተባቸው ተናግረዋል።
“በአንድ አገር ላይ መንግሥት አለ ብለን በምኖርበት ቦታ ላይ ማንም እየመጣ የሚገድለን ከሆነ ትልቅ አደጋ ነው። እና ይህን ስሜት ለመግለጽ ወጣቱ መሀል ከተማ ላይ [የህጻኗን] አስከሬን ይዞ ወጥቶ ነበር። ከዛ በኋላ ተኩሰው መቷቸው” ብለዋል።
“ከንቲባ ጽ/ቤት እና አስተዳደር ጽ/ቤት የሚባል አለ። ሰው በሰላማዊ መንገድ እየሄደ ባለበት ነው በቀጥታ ተኩስ ከፍተው የመቷቸው” ሲሉ ሌላ ነዋሪ ተናግረዋል።
ከምሽቱ 12 ሰዓት አካባቢ “ጸረ ሽምቅ ኃይል” የተባለ እና በአካባቢው አስተዳደር የተቋቋመ ኃይል ጥቃቱን ማድረሱን የተናገሩት አንድ የዐይን እማኝ፤ “ለምን ድምጻችሁን አሰማችሁ?” በሚል ጥቃቱ ተፈጽሟል ይላሉ።
ሕዝቡ 10 ሰዓት አካባቢ ወደ አደባባይ መውጣቱን የተናገሩ አንድ የዓይን እማኝ ደግሞ፤ ፖሊስ እና መከላከያ ሕዝቡ ወደ አደባባይ እንዲያልፍ ፈቅደው እንደነበር ገልፀዋል።።
“ከመጀመሪያው ቢሆን [ሰልፉን] ለመበተን የተደረገ ጥረት ሊሆን ይችላል። ፒያሳ፣ መምሪያ ጮኸው ሲመለሱ የጥይት እሩምታ [ተከፈተባቸው]” ብለዋል።
“መሳሪያ ለመቀማትም ሆነ ሌላ ጥቃት ለማድረስ የሞከረ [ሰልፈኛ] የለም” ያሉ ሌላ ነዋሪ “ሰልፈኞችን ለመበተን” በሚል ጥቃቱ ተፈጽሟል ብለዋል።
“ከተማ ላይ ያለ የመንግሥት ኃይል ነው። ተተኮሰበት የሚባለው የዞን አስተዳደር ጽ/ቤት አካባቢ ነው፤ መሀል ከተማው ፒያሳ አካባቢ ላይ ነው። አኛ እስከምናውቀው ድረስ ከተማውን የሚጠብቀው መንግሥት ነው” ሲሉ ጥቃቱን የመንግሥት ኃይል እንጂ ሌላ አካል አልፈጸመውም ብለዋል።
በጥቃቱ ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ እንዳላወቁ የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ “ብዙ የወደቁ አሉ፤ ማታ [ሰኞ ነሀሴ 27] ላይ አነሷቸው” ሲሉ በቁጥሩ እርግጠኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
ጥቃቱ ሲፈጸም ቦታው ላይ የነበሩ አንድ የዓይን እማኝ ጥቃቱ በተፈጸመበት ቅጽበት ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። የሟቾች ቁጥር ግን ከዚህ ከፍ ሊል እንደሚችልም ጠቁመዋል።
ሌላ የጎንደር ነዋሪ ደግሞ በጥቃቱ ሴቶችን ጨምሮ አራት ሰዎች መገደላቸውን እንደሰሙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሁለቱ የባጃጅ ሹፌር መሆናቸውን እንደተረዱ የገለጹት ነዋሪው፤ ቀብራቸው በከተማው ጥንታዊ ደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን እንደተፈጸመ ተናግረዋል።
ሌላ ነዋሪ “በየ ቤተ-ክርስቲያኑ ቀብር እንዳለ ነው የሰማሁት” ያሉ ሲሆን፤ በርካታ ሰዎችም ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውን ገልጸዋል።
ጥቃቱን ተከትሎ በጎንደር መደበኛ መገደቡን የጠቆሙ አንድ ነዋሪ፤ በከተማዋ አካባቢዎች የመንግሥት ኃይሎች በቡድን በቡድን ቆመው ይታያሉ ብለዋል።
ሆኖም ከተማው የደኅንነት ስጋት ውስጥ እንደሚገኝ ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
“ምንም አይነት የመኖር ዋስትና የሌለው ከተማ ነው ማለት ይቻላል። አንደኛ ዙሪያውን ታጥሯል። እኛ መሀል ላይ ነው ያለነው። ግን ከከተማው ከ10 ኪ.ሜ በዘለለ መሄድ አይቻልም። ወጥተንም በየመንገዱ ፍተሻ ይኖራል። ማን እንደሚፈትሸን አናውቅም” ሲሉ የደኅንነት ስጋቱ ማኅበረሰቡ ላይ ምሬት እንደፈጠረ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።
ሌላ ነዋሪ ደግሞ “ቤት ለማደር ምንም ዋስትና የለንም። ማንም ሰው ዋስትና የለውም። . . . ጦርነት አለ ተብሎ ጉድጓዳችን [ቤታችን] ገብተን እንዘጋለን ወይም ደግሞ ጦርነት የለም ብለን እንቀሳቀሳለን። ጎንደር ዋስትና በሌለበት ሕይወት ነው ያለው” ብለዋል።
የጎንደር ከተማ የመንግሥት ኃላፊዎችን በማነጋገር ሃሳባቸውን ለማካተት ቢቢሲ ያደረግው ጥረት አልተሳካም።
በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ባለው አንድ ዓመት ካለፈው ግጭት ጋር ተያይዞ በጎንደርና በተለያዩ የአማራክልል አካባቢዎች በሚፈጸሙ እገታዎች ነዋሪዎች ከባድ ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን እየገለጹ ነው::