ኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት የዓባይ ውሃን በተመለከተ ከግብፅ ጋር በጋራ ያወጣውን መግለጫ ተቃወመች

የፎቶው ባለመብት, Council of the European Union
በብራሰልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ የአውሮፓ ኅብረት ከግብፅ ጋር በመሆን ካይሮ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታነሳውን "የቅኝ ግዛት እና የብቸኛ ተቆጣጣሪነት መብት የሚያስተጋባ" መግለጫ አውጥቷል በማለት ወቀሰ።
የአውሮፓ ኅብረት እና ግብፅ ያወጡት የጋራ መግለጫ፤ "በኢትዮጵያ ላይ የተሳሳተ፣ አድልዎ ያለበት እና ጠበኛ አቋም" ያሳየ እንደሆነ በመግለጽም ተቃውሞውን አሰምቷል።
በተለይም ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት ወዲህ ተጠናክሮ የቀጠለው የአዲስ አበባ እና የካይሮ የቃላት ምልልስ ቀጣይ ክፍል የሆነው ይህ መግለጫ የወጣው አርብ ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም. ነው።
የአውሮፓ ኅብረት ዋና ከተማ ተደርጋ በምትቆጠረው የቤልጂየሟ ብራሰልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያሳየው አቋም ረዕቡ ዕለት ለወጣው መግለጫ ምላሽ የሰጠ ነው።
ለመጀመሪያ ጊዜ ከተካሄደው የአውሮፓ ኅብረት እና ግብፅ ጉባኤ በኋላ የወጣው መግለጫ፤ ሁለቱ አካላት የጋራ አቋም የያዙባቸውን ጉዳዮች ዘርዝሯል። መግለጫው የአውሮፓ ኅብረት እና ግብፅ "የምግብ እና ውሃ ደኅንነትን" በተመለከተ ያላቸውን "ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር መስማማታቸውን" ያስረዳል።
ሁለቱ አካላት "በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ [ባሉ] ከውሃ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ እንደሚተባበሩ" ያሰፈረው መግለጫው፤ ከዚህ ቀደም የውሃ አጋርነት በተመለከተ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ያስታውሳል።
የአውሮፓ ኅብረት፤ ግብፅ ካለባት "የውሃ እጥረት" የተነሳ "በናይል ወንዝ ላይ በከፍተኛ መጠን ጥገኛ መሆኗን እንደሚገነዘብ" በመግለጫው አስፍሯል። "የግብጽን የውሃ ደኅንነት እና ዓለም አቀፍ ሕግን ማክበርን" በተመለከተ ለካይሮ ያለውን ድጋፍ የገለጸው የአውሮፓ ኅብረት፤ ይህ አቋሙ "የኢትዮጵያን ግድብም እንደሚያካትት" አስታውቋል።
"የአውሮፓ ኅብረት በአስቀድሞ ማሳወቅ፣ በትብብር እና 'ጉዳት አለማድረስ' መርሆዎች ላይ የተመረኮዘ የተፋሰሱ አገራት ድንበር ተሻጋሪ ትብብርን አጥብቆ ያበረታታል" ሲል አቋሙን በመግለጫው ላይ አስፍሯል።
ለዚህ አቋም ምላሽ የሰጠው በብራሰልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ መግለጫው "ችግር ያለበት እና እጅግ አሳዛኝ" ሲል ጠርቶታል። የጋራ መግለጫው ግብፅ በናይል ወንዝ ላይ አለኝ የምትለውን "የቅኝ ግዛት እና የብቸኛ ተቆጣጣሪነት መብት" የሚያስተጋባ መሆኑን በመጥቀስ ተችቷል።
'የጋራ መግለጫው' በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ መካከል ካለው "ታሪካዊ ግንኙነት ጥራት ጋር የሚቃረን፣ የተሳሳተ፣ አድልዎ ያለበት እና ጠበኛ አቋምን የሚያስፋፋ ነው" ሲልም ተቃውሟል።
በናይል ወንዝ ተፋሰስ ላይ 11 አገራት መኖራቸውን ያስታወሰው ኤምባሲው፤ የሁለቱ አካላት መግለጫ "የሌሎች የተፋሰሱ አገራት አመለካከት እና ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ችላ መባሉን" እንደሚያሳይ ገልጿል።
የአውሮፓ ኅብረት ከግብፅ ጋር ባካሄደው በሁለትዮሽ መድረክ "ኢትዮጵያን ዝቅ ለማድረግ መወሰኑ አሳዛኝ ነው" ሲልም ወቅሷል።
ኅብረቱ፤ የሕዳሴ ግብድን በተመለከተ በአፍሪካ ኅብረት አመቻችነት በተካሄዱ ንግግሮች ላይ የነበረውን የታዛቢነት ሚና አስታውሶ፤ ይህ አጋጣሚ "ሚዛናዊ፣ ምክንያታዊ እና ገለልተኛ" አካሄድን እንዲከተል ሊያደርገው ይገባ እንደነበር በመግለጫው አስፍሯል።
ኤምባሲው አክሎም፤ የአወሮፓ ኅብረት "በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ የተዛባ አመለካከት" መያዙን በጠቀስ ወቅሷል።
የወጣው የጋራ መግለጫም፤ ከናይል ወንዝ ተፋሰስ አገራት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የውሃ ስምምነት እና ሕጎች ካስቀመጧቸው መርሆዎች ጋር "የሚቃረን" ነው ሲል ተችቷል።
በተጨማሪም ኤምባሲው በመግለጫው ላይ "ግድቡ" በሚል የተጠቀሰው የኃይል ማመንጫ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚል ይፋዊ ስያሜ እንዳለው አስታውሷል።
"ራስን የመቻል እና የአፍሪካን ዳግም መንቃት የሚያንጸባርቀው [ይህ] ስያሜ፤ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ አህጉርም ጭምር ትልቅ ትርጉም አለው" ብሏል።















