የግብፅ መሪዎች ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ የሚያደርጉት ንግግር ምን ያመለክታል?

የግብፅ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ እና ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ሞሰጣፋ ማደቡሉ
የምስሉ መግለጫ, የግብፅ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ እና ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ሞሰጣፋ ማደቡሉ

በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት የውዝግብ ምክንያት ሆኖ የቆየው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ ግብፅ በከፍተኛ ባለሥልጣናቷ አማካኝነት በኢትዮጵያ ላይ የምታቀርበውን ክሰ አጠናክራ ቀጥላለች።

ኢትዮጰያ፣ ግብፅ እና ሱዳን ከግድቡ ግንባታ አንስቶ በውሃ ሙሌት እና በግድቡ አስተዳደር ላይ ድርድር ሲያደርጉ ቢቆዩም ከስምምነት ላይ ሳይደርሱ የሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ ሥራ ጀምሯል።

በተለይ ከአባይ ወንዝ የሚመነጨውን አብዛኛውን ውሃ የምትጠቀመው እና ወንዙ "የኅልውናዬ መሠረት ነው" የምትለው ግብፅ፣ ግድቡ የውሃ ድርሻያን ይቀንሰዋል በማለት ስትከራከር ቆይታለቸ።

በኢትዮጵያ በኩል ግን ግደቡ የኃይል ማመንጫ በመሆኑ ለታችኛው ተፋሰስ አገራት የሚደርሰውን ውሃ የተመጣጠነ ያደርገዋል ስትል ትከራከራለች።

ግብፅ ግድቡ ኢትዮጵያ የውሃን ፍሰት እንድተቆጣጠረው በማድረግ የበላይነትን ይሰጣታል በሚል ስጋት ከግንባታው ወቅት አንስቶ አስገዳጅ ሕጋዊ ስምምነት እንዲፈረም ስትጥር የቆየች ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ በኩል ግን ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱ ይታወቃል።

ከግድቡ ምረቃ ከሳምንታት በኋላ በሱዳን የደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ ግብፅ እያሰማችው ላለው ተቃወሞ አዲስ በር የከፈተላት ሲሆን፣ ለተከሰተው ጎርፍ እና ለደረሰው ጉዳት ግዙፉን የኢትዮጵያ ግድብ ተጠያቂ አድርጋለች።

በኢትዮጵያ በኩል ግን ይህ ተቀባይነትን አላገኘም።

ይልቁንም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መኖር በሱዳንም ሆነ በግብፅ ሊደርስ ይችል የነበረን ከባድ ጉዳት አስቀርቷል በማለት የቀረበውን ክስ አጣጥላዋለች።

ኢትዮጵያ አሁንም በድርድሩ ለመቀጠል እና ሁሉንም ከሚጠቅም ስምምነት ላይ ለመድረስ ፍላጎት እንዳላት እየገለጸች ቢሆንም ከግብፅ በኩል ግን እየተሰማ ያለው ምላሽ ወደ ፍጥጫ ያዘነበለ ይመስላል።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ገንብታ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ካስመረቀችው በኋላ የግብፅ ፕሬዝዳንትን ጨምሮ የአገሪቱ ዲፕሎማቶች እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ዛቻ አዘል ንግግሮችን በይፋ እየተናገሩ ነው።

"ግብፅ እጇን አጣጥፋ አትመለከትም"

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከቀናት በፊት የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ካይሮ ውስጥ በተካሄደ 8ኛው የውሃ ሳምንት ስብሰባ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አገራቸው ብሔራዊ ጥቅሟን አና የውሃ ደኅንነቷን ለማስጠበቅ አስፈላጊ የሆኑትን ሁሉንም እርምጃዎችን ትወስዳለች ብለዋል።

ይህ የፕሬዝዳንቱ ንግግር የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት እና የሁለቱ አገር ወዳጅ የሆነችው አሜሪካ ከሚያረምዱት አቋም አንጻር ለንግግር የሚኖረውን ዕድል የሚያደናቅፍ ሊሆን ይችላል።

ፕሬዘዳንቱ ኢትዮጵያ በግዛቷ ውስጥ ገንብታ ሥራ ላይ ያዋለችውን ግድብ አስተዳደርን በተመለከተ ግብፅ ደስተኛ አለመሆኗን ጠቅሰው ይህንን "ኃላፊነት የጎደለው" ያሉትን ሁኔታ አገራቸው "እጇን አጣጥፋ አትመለከትም" ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሰጠው ምላሽ የፕሬዝዳንቱ ንግግር ግብፅ የአባይ ወንዝን በበላይነት ለመቆጣጠር ያላት ፍላጎት መገለጫ መሆኑን በመጠቀስ፣ እንዲህ ያለው ንግግር ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን አሳልፋ እንድትሰጥ የሚያደርጋት እንዳልሆነ በመግለጽ ተቃውሞውን ገልጿል።

ከዚህ ከፕሬዝዳንቱ ንግግር ቀደም ብሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ በተካሄደበት ወቅት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጉዳይ አንስተው አገራቸው ኢትዮጵያን ወደ ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት እንደምትወስድ ገልጸው ነበር።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ "በአባይ ላይ የተናጠል እርምጃ ወስዳ ግድብ በመገንባት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የግብፅ እና የሱዳን ሕዝቦችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥላለች" በማለት ከመከሰሳቸው በተጨማሪ ኢትዮጵያ የተናጠል እርምጃ በመወሰድ በቀጣናው "አደጋ ደቅናለች" ብለዋል።

ይህንን ክስ ተከትሎም በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ ተወካይ የሆኑት አምባሳደር ዮሴፍ ካሳዬ በሰጡት ምላሽ "ግብፅ ስለ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ያደረገችው ንግግር መሠረት አልባ እና አሳሳች ነው" በማለት "ግብፅ ከቅኝ ግዛት ስምምነት የተወረሰ 'ታሪካዊ መብት' አለኝ በሚል የተፋሰሱን አገራት አግልላች" ብለዋል።

አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት እንዲሁም አገራት ኢትዮጵያ እና ግብፅ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ንግግር በማድረግ ከስምምነት እንዲደርሱ እየጠየቁ ባለበት በአሁኑ ጊዜ በግብፅ በኩል ግን ሌሎች አማራጮችን ለመፈለግ አዝማሚያ እንዳለ የሚያመለክቱ ንግግሮች እየተሰሙ ነው።

"ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ አትደራደርም"

ፕሬዝዳንት አልሲሲ አገራቸው በአባይ ውሃ ላይ ያላትን ጥቅም ለማስከበር ማንኛውንም እርምጃ እንደሚወስዱ በተናገሩበት መድረክ ላይ የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሰጣፋ ማደቡሉ የግብፅ የውሃ ደኅንነት ጉዳይ "የኅልውና ጉዳይ ስለሆነ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም" ማለታቸው ተዘግቧል።

ፕሬዝዳንት አልሲሲ በመክፈቻው ላይ ንግግር ባደረጉበት 8ኛው የውሃ ሳምንት ጉባኤ ማብቂያ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ጋር የማያስማማቸውን "ታሪካዊ እና ሕጋዊ" መብትን አንስተዋል።

የግብፅ የውሃ ደኅንነት ጉዳይ የፖለቲካ ወይም የድርድር ቦታ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን ታሪካዊ እና ሕጋዊ መብት ለድርድር ታቀርባለች ብሎ ማሰብ ተራ ቅዥት ነው" በማለት ለግብፅ የኅልውና ጉዳይ በሆነው በአባይ ውሃ ላይ ድርድር እንደማይኖር ተናግረዋል።

ይህ ግብፅ ከአባይ ወንዝ የምታገኘው የውሃ መጠን እንዳይነካባት የምትጠቅሰው "ታሪካዊ እና ሕጋዊ" ድርሻ ሌሎችን አገራት ያገለለ እና ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀሪዎቹ የናይል ተፋሰስ አገራት ተቀባይነት የሌለው የቅኝ ግዛት ስምምነት ነው።

ይህ በአውሮፓውያኑ 1959 በቀኝ ገዢዋ ብሪታኒያ የተፈረመው እና የአብዛኛውን የውሃውን ድርሻ ለግብፅ የሚሰጠው የቅኝ ግዛት ስምምነት አብዛኛውን የተፋሰሱን ውሃ ለግብፅ የሚሰጥ ነው።

ስምምነቱ ለ85 በመቶ በላይ ውሃን ለወንዙ የምታመነጨውን ኢትዮጵያን ያላካተተ ሲሆን፣ ግብፅ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃ እንዲሁም ሱዳን 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃ እንዲያገኙ የሚፈቅድ ነው።

በየዓመቱ በናይል ወንዝ ላይ ከሚፈሰው 84 ቢሊዮን ኩዩቢክ ውሃ 12 በመቶው በትነት የሚያልቅ ሲሆን፣ አብዛኛውን ቀሪ ውሃ ለግብፅ በመስጠት በወቅቱ ግብፅን ትገዛ የነበረችው ብሪታንያ ለጥጥ ምርቷ እንድትጠቀምበት የሚያመቻች ነው።

ኢትዮጵያ ይህ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነት እሷን ያገገለለ ከመሆኑ በተጨማሪ ፍትሐዊነት የጎደለው በመሆኑ እንደማትቀበለው በመገለጽ በተፋሰሱ አገራት መካከል ድርድር ተደርጎ አዲስ ሁሉንም የሚያስማማ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ስትጠይቅ ቆይታልቸ።

ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ከጀመረች በኋላ በአገራቱ፣ በአፍሪካ ኅብረት፣ በአሜሪካ እና በዓለም ባንክ አማካኝነት በተደጋጋሚ እየተቋረጠ ድርድር ሲካሄድ ቆይቷል።

ነገር ግን ግብፅ ያቀረበችው አስገዳጅ እና ሕጋዊ ስምምነት እንዲፈረም መጠየቋ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ድርድሮቹ ውጤት አላስገኙም።

ግድቡ ተገንብቶ በውሃ ከተሞላ እና ሥራ ከጀመረ በኋላም ድርድር እንዲካሄድ የተለያዩ ወገኖች እየወተወቱ ባለበት ጊዜ ኢትዮጵያ ዝግጁነቷን ብትገልጽም የግብፅ ፕሬዝዳንትን ጨምሮ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚያደርጉት ንግግር ግን ለድርድር በር የሚከፍት አይደለም።

ፕሬዝዳንቱ የግብፅን ጥቅም ለማስከበር ማንኛውንም እርምጃ እንደሚወስዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ በናይል ውሃ ላይ ድርድር የሚታሰብ እንዳልሆነ በአንድ ሳምንት ውስጥ በተከታታይ ማሳወቃቸው በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅት የነበረው ውጥረት አሁንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሚያመለክት ነው።

ባለፉት ሳምንታት የግብፅ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚያደርጓቸው ንግግሮችን እየተከታተለች ምላሽ እየሰጠች ያለችው ኢትዮጵያ ግብፅ አሉታዊ ዘመቻ መክፈቷን በመጥቀስ ተቃውሞዋን አሰምታለች።

የኢትዮጵያ ውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዳለው "ግብፅ ከዓባይ ወንዝ እና ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ የከፈተችውን ዘመቻ አጠናክራ ቀጥላለች" በማለት ገልጾታል።