የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሁለተኛው ምዕራፍ ድርድር ተቃርቧል አሉ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ ያለውን ጦርነት ለማስቆም በዩናይትድ ስቴትስ አደራዳሪነት ወደሚደረገው ሁለተኛ ዙር ድርድር ለመግባት መቃረባቸውን ገለፁ።

ነገር ግን ቁልፍ ጉዳዮች አሁንም ሊፈቱ ይገባል ብለዋል።

በሁለተኛው የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዕቅድ መሠረት በጋዛ የሽግግር አስተዳደር ተቋቁሞ ዓለም አቀፍ የጸጥታ ኃይል ሲሰማራ እስራኤል ወታደሮቿን ከጋዛ ማስወጣት አለባት።

ከዚህም በተጨማሪ ሐማስ ትጥቁን ፈትቶ ጋዛን መልሶ መገንባት መጀመር ይኖርበታል።

የሐማስ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ቡድኑ የቀረውን የጦር መሣሪያ "ላለመጠቀም ወይም ለማከማቸት" ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ እና ሌሎች አደራዳሪዎች ወደ ቀጣዩ የትራምፕ ዕቅድ መሄድ እንዲቻል በሁለቱም ተደራዳሪ አካላት ላይ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የአረብ መገናኛ ብዙኃን የቀይ መስቀል ቡድን እና የሐማስ ታጣቂ ክንፍ አባላት በጋዛ ከተማ ዜይቱን አካባቢ የቀረውን የእስራኤላዊ ታጋች አስከሬን ፍለጋ መቀጠላቸውን ዘግበዋል።

ይህ እስራኤላዊ ፖሊስ የነበረ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ሙሉ ስሙ ሳጅን ራን ጊቪሊ እንደሚባል ይፋ ተደርጓል።

ሐማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በፈጸመበት መስከረም 26፣2016 ዓ.ም. ጊቪሊ የተገደለ ሲሆን አስከሬኑ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በተደረገው የመጀመሪያ የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት መመለስ አለበት።

ኔታንያሁ እሁድ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ "እናመጣዋለን" ሲሉ ቃል ገብተዋል።

የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ሁለት ወራት የሞላው ሲሆን ሁለቱም ወገኖች በየቀኑ አንዳቸው ሌላኛቸውን ስምምነቱን በመጣስ እርስ በርስ መወነጃጀላቸውን ቀጥለዋል።

የእስራኤል ጦር ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የጋዛ ሰርጥ ይቆጣጠራል። ሐማስ ደግሞ በተቀረው የግዛቱ ክፍል ውስጥ ዳግም ራሱን አደራጅቷል።

ኔታንያሁ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ በወሩ መጨረሻ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር የዕቅዱን ሁለተኛ ምዕራፍ ማሳካት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ጠቃሚ ውይይት እንደሚያካሂዱ ተናግረዋል።

የእስራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ ስብሰባው እአአ ታኅሳስ 29 እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

ኔታንያሁ እሁድ ዕለት ከጀርመን መራሄ መንግሥት ፍሬድሪክ መርዝ ጋር በእየሩሳሌም ከተገናኙ በኋላ ሐማስ ጋዛን የሚያስተዳድርበት ዘመን ማብቃት እንዳለበት እና ቡድኑ የታጠቀውን መሳሪያ ለመፍታት እና አካባቢውን ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ለማድረግ "በቁርጠኝነት" እንዲወጣ በድጋሚ ተናግረዋል።

የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ባሴም ናኢም ከአሶሼትድ ፕሬስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ቡድናቸው የጦር መሣሪያ መፍታትን አስመልክቶ "ላለመጠቀም ወይም በመጋዘን እንዲቀመጥ ማድረግ" ላይ ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ አባል የሆኑት ናኢም አብዛኛው የቡድኑ አመራር በሚገኝባት በኳታር በሰጡት ቃለ ምልልስ "ከዚህ የበለጠ ግጭቱ እንዳይቀጥል ወይም ተጨማሪ ግጭቶችን እና ፍንዳታዎችን ለማስቀረት አጠቃላይ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ዝግጁ ነን" ብለዋል።

ሐማስ ከዚህ ቀደም ነፃ የፍልስጤም መንግሥት ሳይፈጠር የጦር መሳሪያዎቹን ለመፍታት ፈቃደኛ አለመሆኑን ሲናገር ነበር።

ናኢም እስራኤል ቁልፍ የተኩስ አቁም ቃል ኪዳኖችን ሳትፈጽም ቀርታለች በማለት የከሰሱ ሲሆን ወደ ጋዛ በቂ እርዳታ እየገባ አለመሆኑን እና ከግብፅ ጋር ያለው የራፋህ ድንበርም እንደገና እንዳልተከፈተ ተናግረዋል።

የሰብዓዊ እርዳታ ኤጀንሲዎች ወደ ሰርጡ የሚገቡት እርዳታዎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውን፤ ነገር ግን አሁንም በፀጥታ እጦት እና በእስራኤል ጦር እገዳ ምክንያት እግር እየገጠማቸው መሆኑን ይናገራሉ።

በሰላም ዕቅዱ የመጀመሪያ ምዕራፍ መሠረት በሕይወት ያሉ 20 ታጋቾች እንዲሁም 28 የታጋቾች አስከሬኖች እንዲመለሱ ይጠበቃል።

እስራኤል በሕይወት ያሉ ታጋቾችን ለማስፈታት ወደ 2,000 የሚጠጉ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለቅቃለች።

ሐማስ በሕይወት ያሉትን ታጋቾች በሙሉ የለቀቀ ሲሆን፣ ከሟቾች የቀረው የአንድ ፖሊስ አስከሬን ብቻ ነው።

እስራኤል ሐማስን የሟቾችን አስከሬን ለመመለስ ሆን ብሎ ያዘገያል ስትል ትከስሳለች።