'የእኔ ሐሰተኛ ምስክርነት ሦስት ንፁኃን ታዳጊዎችን ለእስር ዳርጓል"

አልፍሬድ ቼስትነት፣ አንድሪው ስቲዋርት እና ራንሰም ዋትኪንስ ባልሰሩት ጥፋት 36 ዓመታት በእስር አሳልፈዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አልፍሬድ ቼስትነት፣ አንድሪው ስቲዋርት እና ራንሰም ዋትኪንስ ባልሰሩት ጥፋት 36 ዓመታት በእስር አሳልፈዋል

ሮን ቢሾፕ እየዋሸ መሆኑን ያውቃል።

በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ለቀረበው ክስ ዋነኛ ምስክር ሆኖ ችሎት ፊት ሲቀርብ 14 ዓመቱ ነበር።

ክሱ በኅዳር 1983 የቅርብ ጓደኛውን ዴዊት ዱኬትን በመግደል የተከሰሱ ሦስት ታዳጊዎችን ያካተተ ነበር።

ቢሾፕ በአልፍሬድ ቼስትነት፣ አንድሪው ስቲዋርት እና ራንሰም ዋትኪንስ ላይ እየመሰከረ ነበር። ሌሎች ሦስት ምስክሮች በሰጡት ምስክርነት የተደገፈው የዐቃቤ ሕግ ክስ ጠንካራ መሰለ። ቢሾፕ ከእነርሱ ጋር የሚቃረን ምስክርነት የሚሰጥ ከሆነ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ፈራ።

"እውነቱን ከተናገርኩ ሁሉንም እቃወም ነበር" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

"እነዚህ ሦስት ሰዎች ጥፋተኛ መሆናቸውን የሚናገሩ ሦስት ምስክሮች ነበሩ። እና ጁሪዎቹ እየዋሸሁ ነው ብለው ያስባሉ ብዬ አስብ ነበር።"

በዕለቱ በባልቲሞር ፍርድ ቤት የተሰጡ ሐሰተኛ ምስክርነቶች ሦስት ጥቁር ታዳጊ ልጆችን በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ አድርጓል።

የጥፋተኝነት ውሳኔው በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ከታዩት ትልቅ የፍትህ መዛባቶች አንዱ ተደርጎ ይወሰዳል።

ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት፣ ቢሾፕ የሰጠው ምሰክርነት ሦስት ታዳጊዎችን ወደ እስር ቤት እንደላካቸው እያወቀ የጥፋተኝነት ስሜቱን ተሸክሞ ኖሯል።

በትምህርት ቤት የተፈጸመ ግድያ

የ14 ዓመቱ ዴዊት ደኬት

የፎቶው ባለመብት, Ron Bishop

የምስሉ መግለጫ, ደዊት ደኬት የተገደለው ለለበሰው የጆርጅታወን ጃኬት በሚል ነው

በባልቲሞር ውስጥ ያደገው ቢሾፕ ትምህርት ቤት ሊቆይበት የሚችል፣ ደህነንነቱ የተጠበቀ ቦታ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ወንድሙን የገደለው ግለሰብ ባለመያዙ የደህንነት ስሜቱ ደካማ ነበር።

በትምህርት ቤት ውስጥ አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው ከሁለት የቅርብ ጓደኞቹ ጋር ነበር። ከእነርሱ መካከልም አንዱ ዱኬት ነው።

ቢሾፕ "ዝም ያለ እና የተረጋጋ ልጅ ነበር" በማለት ያስታውሰዋል። "እርስ በርስ ከተዋወቅን በኋላ በምንኖርበት ሰፈር ያደገ ሌላ ጓደኛ አገኘን።"

ሃርለም ፓርክ ትልቅ እና አስቸጋሪ ትምህርት ቤት ነበር። ስለዚህ እነዚህ ሦስት ተማሪዎች ብዙ ጊዜ በተማሪዎች መካከል ችግሮች የሚፈጠሩበትን በርካታ ተማሪዎች የሚሰበሰቡበትን ቡድን ለመሸሽ አቋራጭ መንገድ መፈለግ ጀመሩ።

በኅዳር 1983 አንድ ቀን ከእነዚህ አቋራጭ መንገዶች መካከል አንዱን መረጡ።

ሮን ቢሾፕ በ14 ዓመቱ

የፎቶው ባለመብት, Ron Bishop

የምስሉ መግለጫ, ሮን ቢሾፕ በ14 ዓመቱ ወንድሙ ስለተገደለበት የደህንነት ስሜት አይሰማውም ነበር

ቢሾፕ "በኮሪደሩ ላይ እየተጓዝን ነበር፣ ሁልጊዜም እንደምናደርገው ታሪኮችን እያወራን፣ እየተቀላለድን" ይላል።

"አንድ ሰው 'ሄይ ጃኬቱን ስጠኝ!' ሲል የሰማሁት ያኔ ነው።"

ዱኬት በወቅቱ በባልቲሞር አካባቢ ሁሉም ሰው መልበስ ይፈልግ የነበረውን፡ የጆርጅታውን ዩኒቨርሲቲ የቅርጫት ኳስ ቡድን ጃኬት ለብሶ ነበር።

"ዞር ስል ፊት ለፊቴ ላይ ሽጉጥ እንዳለ ተረዳሁ። እና ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ ስሸሽ ሰውዬው በዴዊት አንገት ላይ ደቀነ።"

ቢሾፕ እና ጓደኛው ሮጡ። ከዚያ በኋላ ትርምስ ሆነ።

"ኮሪደሩን አቋርጠን ከደረጃው ስንወርድ ነው ተኩሱን የሰማነው።"

እሱና ጓደኛው ዋናው ካፍቴሪያ እስኪደርሱ ድረስ መሮጣቸውን ቢሾፕ ያስታውሳል። ብዙም ሳይቆይ ዴዊት አንገቱን ይዞ ወለሉ ላይ ተዘረረ።

ምርመራው ተጀመረ

የባልቲሞር ፖሊስ አርማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዴዊት ዱኬት ከተገደለ በኋላ ምርመራውን የያዘው የባልቲሞር ፖሊስ ነበር

በድንጋጤ ውስጥ ያሉት ሁለቱም ልጆች የዴዊትን የጉዳት ክብደት ሳያውቁ ወደ ቤታቸው ሄዱ። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ፖሊሶች እነርሱን ፍለጋ መጡ።

ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲወሰድ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር። እዚያም ከመርማሪ ዶናልድ ኪንኬይድ ጋር ተገናኘ።

ቢሾፕ "በጣም ጥሩ ሰው ይመስል ነበር" ይላል። "እሱ የሆነ የሚያስፈራ ግርማ፣ የመሪነት ስሜት ነበረው እና ሙሉ ትኩረቱን ሰጠኝ፤ ይህም በጣም አስገርሞኝ ነበር።"

ቢሾፕ ተጠርጣሪውን በዝርዝር ገልጾታል። ከእኔ ረዘም ይላል፤ ቀጭን፣ ጠቆር ያለ ቀጭን ፂም ያለው። የለበሰውን ልብስ በዝርዝር ገልጿል።

ቢሾፕ መርማሪ ኪንኬያዲ ማስታወሻዎችን ከያዘ በኋላ ክፍሉን ለቅቆ መውጣቱን ያስታውሳል። ሲመለስ ዴዊት የመሞቱን መርዶ አረዳው።

"እየሆነ ያለውን ነገር ማመን አቃተኝ። እሱን ለመግለፅ ምንም ቃላት የሉኝም" ይላል። "ሌላ ዓለም ውስጥ እንዳለሁ ሆኖ ተሰማኝ፤ ወደ ቤት እንድሄድ እንዲፈቅዱልኝ እና አልጋ ላይ እንድተኛ ፈልጌ ነበር።"

ከአንድ ተጠርጣሪ ወደ ሦስት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ግድያው ከተፈጸመ ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ መርማሪ ኪንኬይድ ቢሾፕ ቤት መጣ።

"የብዙ ተጠርጣሪዎችን ፎቶግራፎች አሳይቶኛል፤ ሁሉንም አውቃቸዋለሁ። አልፍሬድ፣ አንድሪው እና ራንሰምን አይቻቸዋለሁ። እና ከዴዊት ግድያ ጋር የተገናኘ ሰው እንዳላየሁ ለኪንኬይድ ነገርኩት።"

ቢሾፕ የመርማሪውን ምላሽ በደንብ ያስታውሳል።

"ፊቱ ላይ የብስጭት መልክ አየሁ፤ ልክ እንደ ቁጣ ይመስላል፤ ከዚያ ሄደ።"

ከቀናት በኋላ መርማሪው ወደ ጣቢያው ወሰደው። ቢሾፕ እንደሚለው ያኔ ነው ሁሉም ነገር የተቀየረው።

"እዚያ ነበር ከእኔ ጋር በምርመራ ክፍል ውስጥ ራሱን ሲቆልፍ ሁሉም መጥፎ ነገሮች የተከሰቱት።"

በተለያዩ አጋጣሚዎች፣ ኪንኬይድ ቢሾፕ ከዚህ በታች የሚገልጻቸውን ውድቅ አድርጓል።

"እየዋሸሁኝ እንደሆነ የሚያስረዳ አዲስ መረጃ እንዳለው ነገረኝ፤ መረጃ እንደደበቅኳቸው ነገረኝ። እንዲያውም የበለጠ በቀጥታ እየጮኸ እና ጣቱን ወደ እኔ እየቀሰረ" ነበር የሚያናግረኝ።

ቢሾፕ እንደሚያስረዳው መርማሪ ኪንኬይድ ያገኛቸው አዲስ ምስክሮች በዱኬት ግድያ ሦስት ተጠርጣሪዎችን ለይቷል። እና ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ የምስክር ቃሎችን የሚደግፉ ናቸው።

ነገር ግን ቢሾፕ አንድ ሰው ብቻ በግድያው ላይ እንደተሳተፈ ያውቅ ነበር።

በቀጣዮቹ ቀናት የሚደርስበት እንግልት ተባባሰ።

ቢሾፕ አንድ ጊዜ መርማሪው በጣም ከመናደዱ የተነሳ "ሽጉጥ" ማሳየት እንደጀመረ ይናገራል።

ያኔ ነበር፣ በተስፋ መቁረጥ ስሜት፣ ቢሾፕ ለመርማሪ ኪንኬይድ መስማት የሚፈለገውን እንደሚናገር ቃል የገባለት።

በምርመራው መጨረሻ፣ ቢሾፕ ቼስትነት፣ ስቱዋርት እና ዋትኪንስ በጓደኛው ግድያ ውስጥ የተሳተፉት ልጆች መሆናቸውን የሚገልጽ የምስክርነት ቃሉ ላይ ፈረመ።

በዚያ ሰነድ መሰረት ታዳጊዎቹ በቁጥጥር ስር ውለው መደበኛ ክስ ተመስርቷል።

ቢሾፕ የእናቱን እና የቤተሰቡን ምላሽ በመፍራት የሆነውን ላለመናገር ወሰነ።

 የባልቲሞር ከተማፍርድ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አቃቤ ሕግ በዴዊት ዱኬት ግድያ አራት ምስክሮችን ያቀረበ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንዱ ሮን ቢሾፕ ነበር

የችሎቱ ሂደት

በሦስቱ ወጣቶች ክስ የባልቲሞር ዐቃቤ ሕግ አራት ምስክሮችን አቅርቧል፣ ሁሉም ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሲሆን ከእነርሱ መካከል ቢሾፕ ይገኝበታል።

ከኪንኬድ እና ከዋና ዐቃቤ ሕግ ጋር በነበረው የመጀመሪያ ስብሰባ ወቅት ባለሥልጣናቱ ምስክሮቹን በዋና ዝርዝሮች ነጥቦች ላይ የሚናገሩትን ለማጣጣም መሞከራቸውን ያስታውሳል።

ለመናገር ተራው ሲደርስ ቢሾፕ ታገለ።

"ሀሳቤን አንድ ላይ ማያያዝ አልቻልኩም" ሲል ያስታውሳል። "ያልተፈጸመ ነገር እንዳስታውስ ስለ ጠየቁኝ ተደናግጫለሁ። እንድዋሽ ጠይቀውኛልና ፈርቼ ነበር።"

በመጨረሻ ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ የተስፋ መቁረጥ እርምጃ የወሰደው ቢሾፕ፣ ዱኬት በተተኮሰበት ወቅት እዚያ ከነበረው ጓደኛው ጋር ችሎቱ ሲጀመር እውነቱን ለመናገር ቃል ገባ።

ነገር ግን ቀኑ ሲደርስ ነገሮች እንደታሰበው አልሄዱም።

"እኔ ለመመስከር የመጀመሪያ ሰው መሆን ነበረብኝ፤ ነገር ግን መጨረሻ ሆንኩኝ። እና እውነቱን ከመናገር የከለከለኝ ጓደኛችንን ማየቴ ነበር ... ወንጀሉ የተፈጸመው በሦስት ሰዎች እንጂ አንድ አይደለም ሲል መሰከረ።"

"በ14 ዓመቴ ጁሪዎቹ እውነቱን እየተናገርኩ እንዳልሆነ ያውቃሉ ብዬ አስቤ ነበር። እና መርማሪ ኪንኬይድ ሦስቱን ለመከላከል በመሞከር እንደ ተባባሪ ሊከሱኝ እንደሚችሉ አስቀድሞ አስፈራርቶኛል።"

በመጨረሻ ቢሾፕ ሦስቱን በፍርድ ቤት ወንጀለኞች መሆናቸውን በመለየት አሳይቷል።

ምስክሮች ከተሰሙ እና ጁሪዎቹ ከተከራከሩ በኋላ በዱኬት ግድያ የተከሰሱት ሦስት ታዳጊዎች የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደባቸው።

ሮን ቢሾፕ

የፎቶው ባለመብት, Ron Bishop

የምስሉ መግለጫ, ሮን ቢሾፕ ምንም እንኳን ወንጀሉ ከተፈጸመ ረዥም ጊዜ ቢሆንም አሁንም የጥፋተኝነት ስሜት እንደሚሰማው ይናገራል

የጥፋተኝነት ስሜት

"ከጥፋተኝነት ስሜት ጋር መኖር ነበረብኝ" ይላል ቢሾፕ። "እነዚህ ልጆች ቀሪው ሕይወታቸውን እስር ቤት ለማሳለፍ ሲሄዱ ማየት፣ አስከፊ ስም ወዳለው ወደ ሜሪላንድ ግዛት እስር ቤት ሲላኩ፣ ከገዳዮች ጋር የእስር ቤት ክፍሎችን እንደሚጋሩ ማወቅ፤ እና ገና የ16 እና 17 ዓመት ታዳጊዎች መሆናቸው ጥፋተኝነት ስሜቱን ያከብደዋል።"

ስቃዩ ግን ከችሎቱ ጋር አላበቃም።

ቢሾፕ "ማንንም አታምንም" ሲል ያስታውሳል። "እነሱ እንዳላደረጉት ታውቃለህ፤ እና ግድያውን የፈጸመው ሰው ከሁላችን ጋር እንዳለ ጭምር፤ አንድ ሰው ግድያውን እንደፈጸመው ታውቃለህ። ስለዚህ ሁልጊዜ አንድ ሰው ሊያጠቃኝ ይመጣ ይሆን? ስትል ትጠይቃለህ። እኔንም ይገድሉኝ ይሆን?"

ምንም እንኳን የተሸከመው የጥፋተኝነት ስሜት ከባድ ቢሆንም ቢሾፕ ትምህርቱን ጨርሶ በሳይኮሎጂ ተመርቋል።

ሁልጊዜም ግን የቅርብ ጓደኛው በተገደለበት ቀን ምን እንደተፈጠረ እውነቱን የመናገር አንድ ግብ በአእምሮው ውስጥ ነበረው።

ያ ዕድል የመጣው ግን ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ እአአ በ2019 ነው።

የቼስትት እና የሕግ ቡድኑ ያላሰለሰ ጥረት ምስጋና ይግባውና የባልቲሞር ዐቃቤ ሕግ ቢሮ የፈጸመውን ከባድ ስህተት ከተረዳ በኋላ አዲስ ምርመራ ጀመረ።

ቢሾፕ ዳግም ሲጠራ የመጀመርያ ምላሹ በድንጋጤ መርበትበት ነበር።

"እኔ የተጠረጠርኩ መሰለኝ። ይህ በአንድ ወቅት ዋሽትሃል ብሎ የወነጀለኝ ተቋም ነው። የድሮ ስሜቶች በፍጥነት ክልብስ ብለው መጡብኝ። ይህን በእኔ ላይ በድጋሚ ሊያላክኩ ነው? ለምን አሁን?"

ያም ሆኖ ወሰነ።

"ሄድኩኝ፤ አሁን ወደ እስር ቤት መወርመርም ቢሆን እውነት እናገራለሁ ስል ለራሴ ቃል ገባሁ።"

ለዐቃብያነ ሕጎቹ የቢሾፕ ምስክርነት የጎደለው ነገር ነበር። የእሱ ምስክርነት ሌሎች ሦስት ምስክሮችን ለማግኘት ረድቷቸዋል። እነሱም የሰጡትን ምስክርነት የተሳሳተ መሆኑን ተናግረዋል።

በምርመራው መሠረት ፖሊስ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ታዳጊዎችን በማስገደድ እና በማሰልጠን የሐሰት ምስክርነት እንዲሰጡ ማድረጉ ተደረሰበት።

በተጨማሪም በሦስት ወንጀለኞች ንድፈ ሐሳብ ምክንያት ሁለተኛ መላምት በፍፁም አለመመርመሩ ተረጋግጧል።

አንድ ምስክር መጀመሪያ ላይ ሌላ ማይክል ዊልስን የሚባል ግለሰብ መኖሩን ተናግሮ ነበር።

ግለሰቡ በትምህርት ቤቱ አቅራቢያ የነበረ ሲሆን በኋላ ላይም የጆርጅታውን ጃኬት ለብሶ ታይቷል።

ዊልሰን እንደ አውሮፓውያኑ በ2002 በጥይት ተገድሏል። በመሞቱ የዱኬት ግድያ እስካሁን መፍትሄ አላገኘም።

በአራት ሳምንታት ውስጥ የባልቲሞር አቃቤ ሕግ ቢሮ ጉዳዩን የሚመለከተው ክፍል ቼስትነት፣ ስቲዋርት እና ዋትኪንስ በስህተት እንደተፈረደባቸው ገለፀ።

እአአ ኅዳር 25/2019 በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ከ36 ዓመታት በኋላ ሦስቱም ከእስር ተለቀቁ።

እአአ በጥቅምት 2023 የባልቲሞር ከተማ ለተፈጠረው ከባድ የፍትህ ስህተት ከግለሰቦቹ ጋር የ48 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ላይ ደረሰ።

ለቢሾፕ መፈታታቸው የተወሰነ እፎይታን ሰጥቶታል። ነገር ግን ሰላም አላመጣለትም።

እና እነሱን ማነጋገር ከቻለ ይቅርታ እንደሚጠይቃቸው ያስባል።

"በየቀኑ ስለእነርሱ አስባለሁ" የሚለው ቢሾፕ "ቤተሰብ መመስረት፣ የራሳቸው ልጆች ወልደው ማሳደግ ባይችሉም… እና እኔ እንደ ነፃ ሰው ሆነው የሰመረ ሕይወት እንዳይኖሩ በመከላከል ረገድ የበኩሌን ሚና እንደተጫወትኩ ስለማውቅ አዝናለሁ።"

"ይህንን በየቀኑ አስባለሁ።"