በሕንድ የመረጃ መንታፊዎች ከእናቶች ሆስፒታል የደኅንነት ካሜራ ያገኙትን ቪዲዮ ለሽያጭ አቀረቡ

ከኮምፒውተር ፊት ለፊት የተቀመጠ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፖሊስ በመረጃ ምንተፋ ላይ የተሰማሩ በርካታ ሰዎችን ማግኘቱን ገልጿል

በሕንድ ከሚገኝ የእናቶች ሆስፒታል የተሰረቁ የደኅንነት ካሜራዎች ላይ የተወሰዱ ቪዲዮዎች በቴሌግራም ላይ መሸጣቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

የደኅንነት ካሜራዎች በየቦታው የሚገኙባት ሕንድ ይህ የመረጃ መንታፊዎቹ ተግባር የግላዊነት እና የደኅንነት ስጋቶችን ቀስቅሷል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በጉጃራት ግዛት ውስጥ ፖሊስ በዩቲዩብ ላይ ከተለቀቁ ቪዲዮዎች ጋር በተገናኘ ከመገናኛ ብዙኃን ጥቆማ ደርሶታል።

ከአንድ የእናቶች ሆስፒታል የተወሰዱት ቪዲዮዎች ላይ ነፍሰ ጡር እናቶች የሕክምና ምርመራ ሲያደርጉ እና መርፌ ሲወጉ ይታያሉ።

ረዥም ያሉ ቪዲዮዎችን ለመግዛት የሚፈልጉ ተመልካቾችን ወደ ቴሌግራም ቻናሎች የሚመራ ማስፈንጠሪያዎችም አብሯቸው ይገኛል።

የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ለቢቢሲ እንደተናገሩት ካሜራዎቹ የተቀመጡት ለዶክተሮች ደኅንነት ሲባል ነው።

ቢቢሲ በቪዲዮዎቹ ውስጥ ለሚታዩት ሴቶች ደኅነንነት ሲል የከተማዋን ወይም የሆስፒታሉን ስም ላለመጠቀም ወስኗል።

ሆስፒታሉም ሆኑ ግለሰቦቹ እስካሁን ድረስ ጉዳዩን በሚመለከት ለፖሊስ ቅሬታ አላቀረቡም።

ፖሊስ ባደረገው ምርመራ በመላው አገሪቱ 50 ሺህ ያህል የደህንነት ካሜራዎች የተወሰዱ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በመረጃ መንታፊዎች ተሰርቀው በበይነ መረብ ላይ ተሸጠው ማገኘቱን ገልጿል።

የደኅንነት ካሜራዎች በሕንድ ውስጥ በተለይም በከተማ አካባቢዎች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተገጥመው ይገኛሉ።

እነዚህ ካሜራዎች በገበያ ማዕከሎች፣ በቢሮዎች፣ በሆስፒታሎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በመኖሪያ አፓርትመንቶች እና በግለሰቦች ቤት ውስጥ ተገጥመዋል።

ባለሙያዎች እነዚህ ካሜራዎች ደኅንነትን ቢጨምሩም በሚገባ ካልተያዙ ግን ግላዊነትን አደጋ ላይ ሊጥሉ እንደሚችሉ ያስጠነቅቃሉ።

በሕንድ ካሜራዎች ብዙ ጊዜ የሳይበር ደኅንነት ሥልጠና ባልወሰዱ ሠራተኞች ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሲሆን፣ አንዳንድ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ሞዴሎች ደግሞ በቀላሉ በመረጃ መንታፊዎች ሊመዘበሩ እንደሚችሉ ይነገራል።

በአውሮፓውያኑ 2018 በቤንጋሉሩ ከተማ የሚኖረው የቴክኖሎጂ ባለሙያ በኢንተርኔት የሚጠቀምበት ካሜራው (ዌብካም) ተጠልፎ እንደነበረ እና ጠላፊው የግል ቪዲዮዎቹን ላለማጋራት ክፍያ እንደጠየቀው ተናግሯል።

በ2023 አንድ ዩቲዩበር የግል ቪዲዮዎች በስፋት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከተሠረጨ በኋላ የቤቱ የደኅንነት ካሜራ እንደተጠለፈ ማወቁ ተዘግቧል።

ባለፈው ዓመት የፌደራል መንግሥት ክልሎች የደኅንነት እና የመረጃ ጥሰት ታሪክ ካላቸው አቅራቢዎች የደኅንነት ካሜራዎችን እንዳይገዙ ጠይቋል።

እንዲሁም የደኅንነት ካሜራዎችን የሳይበር ደኅንነት ለማሻሻል አዳዲስ ሕጎችን አውጥቷል። ነገር ግን እንደነዚህ ያሉት የመረጃ ምንተፋ ድርጊቶች አሁንም ቀጥለዋል።

የደህንነት ካሜራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፖሊስ በጉጅራት "በመላው አገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የመረጃ መንታፊዎች ቡድን" ማግኘቱን ተናግሯል።

ጉዳዩን እየመረመረ የሚገኘው የአህመዳባድ የሳይበር ወንጀል ክፍል ኃላፊ ላቪና ሲንሃ "የመረጃ መንታፊዎቹ የቪዲዮ ክትትል ሥርዓቶችን፣ ወይም የደኅንነት ካሜራ ሥርዓቶችን፣ የሆስፒታሎችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ኮሌጆችን፣ የድርጅት ቢሮዎችን እና በተለያዩ ግዛቶች ውስጥ ያሉ የግለሰቦች መኝታ ቤቶችን ሳይቀር እየጠለፉ ነበር" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

በጉጃራት ከፍተኛ የሳይበር ወንጀል ባለሙያ የሆኑት ሃርዲክ ማካዲያ፣ ቪዲዮዎች የተሸጡት ከ9 እስከ 22 ዶላር መሆኑን ተናግረው፣ የቴሌግራም ቻናሎቹ በቀጥታ ከደኅንነት ካሜራዎች የሚመጡ ምሥሎችን በክፍያ ለደንበኞቻቸው ሲሸጡ ነበር ብለዋል።

ፖሊስ የተለያዩ የሕግ ጥሰቶችን በመጥቀስ በወንጀለኞቹ ላይ የክስ መዝገብ ማደራጀቱን ገልጿል።

ከእነዚህም መካከል የሴት ታካሚዎችን ግላዊነት መጣስ፣ አፀያፊ ምሥሎችን ማሠራጨት፣ እርቃናቸውን የሆኑ ሰዎች ያለ ፈቃዳቸው ቀርጾ ለወሲብ ማነሳሻነት መጠቀም እና የሳይበር ሽብርተኝነትን ናቸው።

የተወሰኑት የተጠቀሱት ወንጀሎች የዋስትና መብት የሚያስከለክሉ ናቸው ተብሏል።

በቴሌግራም እና ዩቲዩብ ላይ የተለቀቁትን ቪዲዮዎች ከኩባንያዎቹ ጋር በመነጋገር እንዲወርዱ መደረጉን ተገልጿል።

ከየካቲት ወር ጀምሮ ፖሊስ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን ስምንት ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል።

የሳይበር ወንጀል መርማሪ የሆኑት ሪትሽ ብሃቲያ ደካማ ጥበቃ የሚደረግላቸው የደኅንነት ካሜራዎች እና የቤት ውስጥ ኔትወርኮች በመረጃ መንታፊዎች በቀላሉ ዒላማ ስለሚሆኑ ተገቢው ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ያስጠነቅቃሉ።

"ገመድ አልባ የደኅንነት ካሜራዎች በስማርት ስልክዎ ወይም ላፕቶፕዎ ምስሎች በርቀት እንዲደርሱዎት ያደርጋሉ። ነገር ግን ሥርዓቱ አንዴ ከበይነ መረብ ጋር ከተገናኘ፣ የመረጃ መንታፊዎች የአይፒ አድራሻውን እና የይለፍ ቃሉን ሰብረው ለመግባት ይቀላቸዋል። እና አንዴ ወደ ሥርዓቱ ከገቡ የቀጥታ ቀረጻዎችን ማየት ወይም መቅዳት፣ ማውረድ ወይም ሥርዓቱን መዝጋት ይችላሉ" ሲል ባቲያ ይናገራሉ።

የክትትል ሥርዓቶችን ለመጠበቅ አንዱ መንገድ የአይፒ አድራሻዎችን እና የይለፍ ቃሉን መቀየር ነው ብለዋል።

ባቲያ ፊደሎችን፣ ቁጥሮችን እና ምልክቶችን የሚቀላቀል እና በመዝገበ-ቃላት ውስጥ የማይገኝ ጠንካራ የይለፍ ቃል መጠቀምን ይመክራሉ እንዲሁም በሳይበር ደኅንነት ባለሙያ በየጊዜው ፍተሻ ማድረግን ይመክራሉ።

የሲሲቲቪ አምራቾችም ኃላፊነት እንዳለባቸው በመግለጽ ማሸጊያቸው ላይ ተጠቃሚዎች የይለፍ ቃሎችን በጠንካራ ቃላቶች እንዲተኩ በግልፅ ማስጠንቀቅ አለባቸው ይላሉ።

ማካዲያ ለቢቢሲ አንደተናገሩት በመረጃ መንታፊዎቹ ምዝበራ የደረሰባቸው አብዛኛዎቹ የደኅንነት ካሜራዎች ይለፍ ቃላቸው 'Admin123' ወይንም ደካማ ነበር።