በዓለም 'ትልቁን' የክሪፕቶከረንሲ ምዝበራ የፈጸመችው ሴት እንዴት በሺዎች የሚቆጠሩ ጡረተኞችን አጭበረበረች?

በሺዎች ከሚቆጠሩ ቻይናውያን ጡረተኞች ገንዘብ በመስረቅ 6 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ክሪፕቶከረንሲ የገዛችው ሴት በዚህ ሳምንት ይፈረድባታል።
ከቻይና ሸሽታ በሰሜን ለንደን ትኖር የነበረችው ሴት ሕገ ወጥ ገንዘብን በሕጋዊ መስመር በማስገባት ተከሳለች። የመዘበረችው ገንዘብ በዓለም ክሪፕቶከረንሲ ታሪክ ከፍተኛው ነው ተብሏል።
በቴክኖሎጂ የታገዘ የሕክምና መሣሪያ የሚያመርት እና ክሪፕቶከረንሲ 'ማይኒንግ' ላይ የተሠማራ ተቋም እንዳላት ካስተዋወቀች በኋላ ከ100,000 በላይ ቻይናውያን በተቋሙ ኢንቨስት አድርገዋል።
ግለሰቧ የፍርድ ቤት ውሳኔን እየተጠባበቀች ትገኛለች። ገንዘባቸውን የተጭበረበሩ ሰዎችም የተወሰነውን መልሰው ለማግኘት ተስፋ ሰንቀዋል።
ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ካዋለው ሃብት መካከል ባለቤት ያልተገኘለት ገንዘብ በቀጥታ ለዩናይትድ ኪንግደም ግምጃ ቤት ገቢ ይደረጋል።
ዐቃቤ ሕግ "ሁሉንም ማስረጃ እናሰባስባለን። ፍርድ ቤቱ [ለተጎጂዎች] ርህራሄ ያሳያል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ብሏል።
ዩ የተባሉ ተጎጂ እንደተናገሩት በደረሰባቸው ማጭበርበር ምክንያት ትዳራቸው ተበትኗል።
"ካጣነው ገንዘብ ጥቂቱን በቢትኮይን ብናስመልስ ቀላል አይደለም" ይላሉ።
ከማጭበርበሩ ጀርባ ያለችው የ47 ዓመቷ ኩዊን ዢሚን ናት። የቻይና መንግሥት ምርመራ ሲከፍትባት እአአ በ2017 በሐሰተኛ ፓስፖርት ዩኬ ገብታለች።

የፎቶው ባለመብት, Metropolitan Police
በለንደን ትኖርበት ለነበረው ቅንጡ ቤት በወር 22,700 ዶላር ትከፍል ነበር።
በቢትኮይን የመዘበረችውን ገንዘብ ወደ ዶላር ለውጣ ከዕንቁ የተሠሩ ጌጣጌጦች ሸምታለች። የግል ጉዳዮቿን የምታስፈጽምላት ሠራተኛም ቀጥራለች።
የክሪፕቶከረንሲ ሃብቷን በገንዘብ እንዲሁም በቋሚ ንብረት ለውጣለች። በተለይም የቢትኮይን ዋጋ ሲንር የምታተርፈው ገንዘብ መጠንም ጨምሯል።
"ተኝታችሁ ሃብታም ትሆናላችሁ" ስትል ለኢንቨስተሮች ቃል ትገባ ነበር።
የግል ጉዳዮቿን እንድታስፈጽም የቀጠረቻት ዌን ጂን የስድስት ዓመት እስራት ተፈርዶባታል።
ለፍርድ ቤት በሰጠችው ምስክርነት "ኩዊን አብዛኛውን ጊዜ የምታሳልፈው አልጋ ውስጥ ሆና ጌም በመጫወት እና በበይነ መረብ ዕቃ በመሸመት ነው" ብላለች።
የኩዊን ዕለታዊ ውሎ መዝገብ እንደሚያሳየው ለስድስት ዓመታት የሚዘልቅ የማጭበርበር ዕቅድ ስታወጣ ነበር።
ዓለም አቀፍ ባንክ ለመመሥረት፣ ስዊድን ውስጥ ቤተ መንግሥት ለመገንባት እና ከእንግሊዝ ልዑል ጋር ለመጣመርም እንደምታስብ ጽፋለች።
እአአ በ2022 በክሮኤሽያ እና ሰርቢያ ድንበር ላይ የሚገኝ ንዑስ ግዛት ንግሥት መሆን እንደምትፈልግ ተናግራለች። ይህ ዕውቅና የሌለው ንዑስ ግዛት ሊበርላንድ ይባላል።
የዚህ ንዑስ ግዛት ንግሥት እስከምትሆን ድረስ ሠራተኛዋ ዌን ጂን በለንደን ቤቶች እንድታፈላልግላት አዝዛለች።

የፎቶው ባለመብት, Metropolitan Police
እጅግ የናጠጡ ቱጃሮች የሚኖሩበት 'ቶትሪጅ ኮመን' የተባለ አካባቢ ቤት ለመግዛት ስትጠይቅ ነበር የፖሊስን ትኩረት የሳበችው።
ዌን ጂን የአለቃዋን የባንክ ሒሳብ ለማንቀሳቀስ ስትሞክር ገንዘብ አላገኘችም። ብዙም ሳይቆይ ፖሊስ የኩዊንን ቤት በረበረ።
በመኖሪያዋ የተገኙ ላፕቶፖች ላይ በአሥር ሺዎች የሚቆጠር ቢትኮይን ተይዟል። ይህም በክሪፕቶከረንሲ ታሪክ ትልቁ የማጭበርበር ድርጊት ሆኖ ተመዝግቧል።
ክዊን ቻይና ሳለች በከፈተችው ተቋም ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መዝብራለች።
በተቋሙ ኢንቨስት ያደረጉ ሰዎች በቢትኮይን ትርፍ እንደሚያገኙ ተነግሯቸዋል። ይህ ግን ሐሰተኛ እንደሆነ የዩኬ ፖሊስ ደርሶበታል።

የፎቶው ባለመብት, Metropolitan Police
መርማሪ ፖሊስ ጆይ ራየን "የምዝበራ ሰንሰለቱን ትመራ እንደነበር የሚጠቁም መረጃ አግኝተናል። በጣም አጭበርባሪ እና ሰዎችን በቀላሉ ማሳመን የምትችል ሰው ናት" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኢንቨስት ካደረጉት አንዱ የሆኑት ዩ እንደሚሉት፤ ተቋሙ ሐሰተኛ እንደሆነ አንዳችም ጥርጣሬ አልነበራቸውም። ተቋሙ በየቀኑ 14 ዶላር ትርፍ ይሰጣቸው ነበር።
"ገንዘቡ ሲሰጠን ሁላንችም ጥሩ ስሜት ተሰማን። ብዙ ገንዘብ በተቋሙ እንድናፈስ አበረታታን" ይላሉ።
ዩ እና ባለቤታቸው መጀመሪያ ላይ እያንዳንዳቸው 6,295 ዶላር ኢንቨስት አድርገዋል። በሁለት ዓመት ተኩል 200% ትርፍ እንደሚያገኙም ተነግሯቸዋል።
በተቋሙ ላይ ኢንቨስት የሚያደርጉትን ገንዘብ መጠን ለመጨመር ሲሉ በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ በ8% ወለድ ከባንክ ተበድረዋል።
ዩ በየቀኑ 14 ዶላር ሲሰጣቸው ገንዘቡን መልሰው ኢንቨስት ያደርጉት ነበር።
"ገንዘቡን መልሰን ኢንቨስት የማድረግ ግዴታ አልነበረብንም። ግን ራሳችንን መቆጣጠር አልቻልንም። ትልቅ ሕልም ስለነበረን ሚዛናዊ ሆነን ማሰብ ተሳነን። ሁሉንም ነገር እስከምናጣ ድረስ አልነቃንም" ይላሉ።
ኢንቨስተሮች አዲስ ኢንቨስትር ሲያመጡ በየዕለቱ የሚሰጣቸው የትርፍ መጠን ይጨምራል።
በምዝበራ ሰንሰለቱ ወደ 120,000 ሰዎች ተጭበርብረዋል። በሁሉም የቻይና ግዛቶች ተጎጂዎች እንዳሉ ለማወቅትም ተችሏል።

የፎቶው ባለመብት, Metropolitan Police
የቻይና የፍርድ ቤት ሰነዶች እንደሚያሳዩት 5.6 ቢሊዮን ዶላር በተቋሙ ኢንቨስት ተደርጓል።
አዲስ ኢንቨስትር ገንዘብ ሲሰጥ፤ ገንዘቡ ለቀድሞ ኢንቨስተሮች ዕለታዊ ክፍያ ይውላል። ብቸኛ የሆኑ በመካከለኛ ዕድሜ ላይ ያሉ እና አረጋውያን በዋነኛነት ዒላማ ተደርገዋል።
ኩዊን ስለ አዛውንቶች ግጥም በመጻፍ ትታወቃለች። "አረጋውያንን መውደድ ግዴታችን ነው" ብላ የጻፈችው ይጠቀሳል።
ለኢንቨስተሮች የዓውደ ዓመት ሽርሽር በማዘጋጀት ተጨማሪ ኢንቨስተሮችን ታጠምዳለች።
ኩዊን ሌላ የምትታወቅበት ስም ላንቲያን ጉሪ ነው። አገር ወዳድ መሆኗን በተደጋጋሚ ገልጻለች።
"ለቻይና ያለን ብሔርተኛነት ድክመታችን ነው። እኛን ለማማለል የምትጠቀመውም የአገር ፍቅር ስሜታችንን ነው" ይላሉ ዩ።
በ60ዎቹ ዕድሜ ክልል ያሉት ዩ "ቻይናን ከዓለም አንደኛ" ለማድረግ ቃል እንደተገባላቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም።
የቻይና መሥራች ማኦን ልጅ ያገባው ግለሰብ ተቋሙን መደገፉ ብዙዎች በተቋሙ ኢንቨስት እንዲያደርጉ መተማመኛ እንደሰጣቸው ዩ ገልጸዋል።
"የእኛ ትውልድ ሰዎች ማኦን እናከብረዋለን። የልጁ ባል ተቋሙን ካመነው እንዴት እኛ እንጠራጠራለን? ስለ ተቋሙ ማስታወቂያ ሲሠሩ ቀዩን ነጭ ነው ብለው ያሳምናሉ።"
ኩዊን ማንነቷን እምብዛም ይፋ ማድረግ አትፈልግም ነበር። 'ሁሀ' ወይም 'ትንሽ አበባ' በሚል ቅጽል ስም መጠራት ትመርጣለች።
ብዙውን ጊዜ ከኢንቨስተሮች ጋር የምትገናኘው በማኅበራዊ ሚዲያ በምትለጥፋቸው ግጥሞች ነው።
ኩዊን በአካል የምትገናኘው ቢያንስ 842,000 ዶላር ኢንቨስት ካደረጉ ሰዎች ጋር ብቻ እንደሆነ ሌላው ኢንቨስተር ሊ ይናገራሉ።
"እሷን ማየት የቻልነው ሰዎች የሃብት አማልክትን ያገኘን ነበር የምንመስለው። ማየታችንን ማመን አቃተን። ሕልማችሁ ትልቅ ይሁን ብላ አበረታታችን። በሦስት ዓመት ውስጥ ከትውልድ ትውልድ የሚሻገር ሃብት ታካብታላችሁ አለችን።"
ሊ፣ ባለቤታቸው እና ወንድማቸው 1.3 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርገዋል።
በ2017 የቻይና ፖሊስ ምርመራ ሲጀምር ለኢንቨስተሮች ይሰጥ የነበረው ዕለታዊ ክፍያ እንደተቋረጠ ይናገራሉ።
"ድንገት ክፍያውን አቆሙ፤ ፖሊስ እያጣራ ነው አሉን። ክፍያው እንደሚጀመር ነግረውንም ነበር።"
ኢንቨስተሮች ለተወሰነ ጊዜ ዝምታን መረጡ። በዚህ ወቅት ኩዊን ከፍተኛ ገንዘብ ኢንቨስት ያደረጉ ሰዎች ከበታች ያሉትን ንዑስ ኢንቨስተሮች እንዲያረጋጉ ገንዘብ ከፍላ ወደ ዩኬ ሸሸች።
የዕለታዊ ውሎ መዝገቧ ላይ እንደጻፈችው፤ የቢትኮይን ዋጋ 50,000 ዩሮ ሲደርስ በቻይና ያለባትን ዕዳ መክፈል ትፈልጋለች።
ዕዳዋን ከመክፈል በፊት ቅድሚያ የምትሰጠው ግን የሊበርላንድ ንግሥት መሆንን ነው።
ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ሲያውላት የሸመታ፣ የጽዳት እና የጥበቃ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሠራተኞች ተገኝተዋል።
ኩዊን እንደተያዘች ሰሞን ክሶቹን በአጠቃላይ አስተባብላለች። ከቻይና የሸሸችው መንግሥት የክሪፕቶከረንሲ ነጋዴዎችን በማሳደዱ እንደሆነ ገልጻለች።
ፍርድ ቤት ስትቀርብ ግን በሕገ ወጥ መንገድ ክሪፕቶከረንሲ በማከማቸት ጥፋተኛ ነኝ ብላ አምናለች።
ፍርድ ቤት መቅረቧ "ተስፋ ፈንጥቆልናል" ይላሉ ሊ።
በሺዎች የሚቆጠሩ ቻይናውያን ኢንቨስተሮች ገንዘባቸውን ለማስመለስ እየጠበቁ ይገኛሉ።
ገንዘባቸውን በቀጥታ ወደ ኩዊን የባንክ ቁጥር ሳይሆን ለተቀጣሪዎቿ ያስገቡ ሰዎች ገንዘባቸውን ለማስመለስ ውጣ ውረድ ይጠብቃቸዋል።
ገንዘባቸው የሚመለስላቸው ከሆነ ኢንቨስት ያደረጉት ገንዘብ መጠን ይሰጣቸዋል? ወይስ ዋጋው በጨመረው የክሪፕቶከረንሲ ክፍያ ይሰላል? የሚለው ግልጽ አይደለም።
አብዛኞቹ ተጎጂዎች ምግብ እና መድኃኒት ለመግዛት የሚሆን ገንዘብ እንኳን አልተረፋቸውም።
ዩ እንደሚሉት አንዲት ኢንቨስተር የጡት ካንሰር ሕክምናዋን መከታተል ተስኗት ሞታለች።
"ሞት በራፏ ላይ ነበረች። ኑዛዜዋን የጻፍኩላት እኔ ነኝ። በሕይወት የተረፍነው ሰዎች ፍትሕ እንዲሰፍን እንድንታገል ተናዛለች።"















