በ14 የአፍሪካ አገራት ሐሰተኛ የፍቅር ግንኙነት በመመሥረት ገንዘብ ሲያጭበረብሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ተያዙ

የበይነ መረብ ማጭበርበሪያ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል

የፎቶው ባለመብት, Interpol

የምስሉ መግለጫ, የበይነ መረብ ማጭበርበሪያ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

በ14 የአፍሪካ አገራት ውስጥ በተካሄደ የወንጀል ምርምራና ክትትል ወደ 260 የሚጠጉ በበይነ መረብ ማጭበርበር የተጠረጠሩ ሰዎች መያዛቸው ተገለጸ።

በዩናይትድ ኪንግደም የገንዘብ ድጋፍ ኢንተርፖል ባከናወነው ክትትል፤ በማኅበራዊ ሚዲያና ሌሎችም የበይነ መረብ ገጾች አማካይነት ገንዘብ ሲያጭበረብሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ምዝበራውን ከፈጸሙባቸው ሰዎች ጋር የፍቅር ግንኙነት በመመሥረት ገንዘብ አታለው መውሰዳቸው ተገልጿል። በተጨማሪም የሰዎችን የእርቃን ምሥሎች እንደሚያጋልጡ በማስፈራራት ገንዘብ ሲቀበሉ እንደነበር ተመልክቷል።

የኢንተርፖል የበይነ መረብ ወንጀል ክፍል ኃላፊ ኔአል ጄተን "ከሰዎች ጋር በቀላሉ ትስስር ይፈጥራሉ። ሆኖም እምነታቸውን ለማጉደል ብዙም አይቆዩም" ብለዋል።

በጋና፣ ኬንያ፣ አንጎላና ሌሎችም የአፍሪካ አገራት ከ1,400 በላይ ሰዎች ላይ ወንጀሉን ፈጽመዋል። ተጎጂዎቹ ወደ 2.8 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንደተመዘበሩ ተገልጿል።

አብዛኞቹ ተጎጂዎች አዛውንት ቢሆኑም በተለያየ ዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎች እንደተጭበረበሩ ኃላፊው አስረድተዋል።

ፖሊስ ባደረው ምርመራ የተጠርጣሪዎቹን የማኅበራዊ ሚዲያ እንዲሁም ሌሎች የበይነ መረብ ገጾች በመከተል ከሐምሌ እሰከ ነሐሴ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ሲም ካርድ፣ ሐሰተኛ ሰነዶችና ሌሎችም የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች ተይዘዋል። ኢንተርፖል እንዳለው በመላው አፍሪካ 81 የበይነ መረብ አጭበርባሪዎች ቡድኖች ዒላማ ተደርገዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ሰዎችን በበይነ መረብ ሲመዘብሩ የነበሩ ቡድኖች ተደርሶባቸዋል። በመላው አፍሪካ ሐሰተኛ የፍቅር ግንኙነት በመመሥረትና እርቃን ምሥልን ለማጋለጥ በማስፈራራት የሚፈጸሙ ወንጀሎች ቁጥር ጨምሯል" ሲልም ተቋሙ አስታውቋል።

የኢንተርፖል የበይነ መረብ ወንጀል ክፍል ኃላፊ ኔአል እንዳሉት የበይነ መረብ ገጾች መበራከት ለወንጀለኞች ምቹ ዕድል ፈጥሯል። የገንዘብና የሥነ ልቦና ብዝበዛም ተበራክቷል።

በጋና 68 ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል። 108 ተጎጂዎች የተለዩ ሲሆን፣ 835 የበይነ መረብ ማጭበርበሪያ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ከደረሰው የ450,000 ፓውንድ ጉዳት ውስጥ 70,000 ፓውንዱን ማስመለስ ተችሏል። የተወሰኑት ተጠርጣሪዎች እቃ አድራሽ መስለው ገንዘብ መቀበላቸው ተገልጿል።

የሰዎችን እርቃን ምሥሎች እንዲሁም የወሲብ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ለመልቀቅ በማስፈራራትም ገንዘብ ወስደዋል።

በሴኔጋል 22 ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል። ከ120 ተጎጂዎች 34,000 ፓውንድ ዘርፈዋል ተብሏል።

በአይቮሪ ኮስት 24 ተጠርጣሪዎች ሲያዙ 29፤ የበይነ መረብ ማጭበርበሪያ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። 809 ተጎጂዎችም ተመዝግበዋል።

በአንጎላ ስምንት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ 28 ተጎጂዎች በአገር ውስጥና ከአንጎላ ውጭም ተገኝተዋል።

በቤኒን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ጋምቢያ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኡጋንዳና ዛምቢያ ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል።

የኢንተርፖል የበይነ መረብ ወንጀል ክፍል ኃላፊ ኔአል "አገራት በዋናነት የሚፈተኑት በበይነ መረብ ማጭበርበር ነው። ወንጀሎቹን መግታት ቀላል አይደለም። በየቀኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በሐሰተኛ ኢሜል ይጭበረበራሉ" ብለዋል።