ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አንድ ኪሎ ቡና ከ47 ሺህ ብር በላይ የሸጠው ኢትዮጵያዊ
ለገሠ በጦሳ 2014 ዕድል ፊቷን ካዞረችላቸው ኢትዮጵያውያን አንዱ ሆኗል።
ነዋሪነቱ አዲስ በተቋቋመው ሲዳማ ክልል ነው።
ሲዳማ ክልል አርቤጎና ወረዳ ቡርሳ ቀበሌ።
ቡርሳ ከክልሉ ዋና መዲና ሐዋሳ 80 ኪሎ ሜትር ያህል ትርቃለች።
እድገቱና ውልደቱም በዚያ ነው።
በሠላሳዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ለገሠ የሚተዳደረው በግብርና ነው።
“ከቀድሞ ጀምሮ በግብርና ነው የምተዳደረው” የሚለው ለገሠ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ገብስ እና የመሳሰሉትን እያመረትኩ ነበር የምንኖረው” ሲል ያክላል።
እንሰት ከጓሮው እና እንስሳት ከደጁ አይጠፉም።
የእሱ፣ የባለቤቱ እና የአራት ልጆቻቸው መተዳደሪያም ይህ ነው።
በቅርቡ ግን ፊቱን ወደ ሌላ ዘርፍ አዞረ፤ ቡና ወደ ማብቀሉ።
ቡና አዲሱ መተዳደሪያው ከሆነ አምስት ዓመት ሆነው።
በፊት ለምን ቡና አታመርቱም ነበር ሲባል “ቀዬው ቡና እንደሚያመርት አናውቅም ነበር” ይላል።
እውነትም አካባቢው ለቡና ምቹ መሆኑን ሳያውቁ ቆይተዋል።
አሁንም በአካባቢው ቡና በስፋት እየተመረተ አይደለም።
ጥቂቶች ናቸው ቡና የሚያመርቱት።
ለገሠ ፊቱን ወደ ቡና ሲያዞርም ከሌላው ይልቅ ቡና ውጤታማ ሆነለት።
“ከሌላው እርሻ የቡናው በገቢ የተሻለ ነው” ሲል ለገሠ ይገልጻል።
ግማሽ ሔክታር መሬት ላይ ከአንድ ሺህ ኪሎ በላይ ቡና በየዓመቱ ይሰበስባል።
የሚያመርተውን ቡና በአካባቢው ለሚገኙ ቡና ነጋዴዎች ይሸጣል።
በዓመት ‘ከ70 እስከ 100 ሺህ ብር’ ያገኝ ነበር።
በዚህ መካከል ደግሞ ቡና ለዓለም አቀፍ ገበያ በውድድር እንደሚቀርብ ይሰማል።
ሌሎች ከእነሱ አካባቢ ያመረቱትን እና የገዙትን ቡና 'ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ' አቅርበው በዓለም አቀፍ ገበያ እንደሚሸጥ ሰምቷል።
ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ የቡና የጥራት ውድድር ነው።
ባለፉት 20 ዓመታት የጥራት ውድድር በዋና ዋና የቡና አብቃይ አገራት ውስጥ ይካሄድ ነበር።
በኢትዮጵያ ውድድሩ የተጀመረው ከሁለት ዓመት በፊት ነው።
ዓላማው ከቡናዎች መካከል የተሻለውን መርጦ በዓለም አቀፍ ጨረታ ለታላላቅ ገዢዎች መሸጥ ነው።
በተጨማሪም ገበሬዎችን እንዲሁም ልዩ ጣዕም ያላቸውን ቡናዎች እና አምራቾችን ማስተዋወቅም ሌላኛው ዓላማው ነው።
በዚህ ውድድር አሸናፊ የሆኑ ሻጮች ቡናቸው በከፍተኛ ዋጋ ይቸበቸባል።
ለገሠ ይህንን ሰምቶ ‘እኔስ ለምን በግሌ አልወዳደርም?’ አለ።
በአካባቢያቸው ለሚገኙ ነጋዴዎች ቡናውን ማስረከብ አቆመ።
“የማውቃቸው ሰዎች ከዚህ ቀደም [በውድድሩ] ቡናቸው እየሸጡ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ሲወጡ ተመልክቻለሁ” ይላል።
ለገሠ ለውድድሩ አንድ ሺህ ኪሎ ያህል አቀረበ።
ውድድሩ አዘጋጅ ከቀረበለት ቡና የተሻለውን መምረጥ እና ቀንሶ ለውድድሩ የማቅረብ መብት አለው።
ከዚህ ውስጥ ተጣርቶ 480 ኪሎ ያህሉ ለውድድሩ ፍጻሜ ቀረበ።
ውድድሩ ላይ እስከ 40 ባለው ደረጃ ውስጥ ብገባ ሲል ለገሠ ተመኘ።
ውጤቱ ሲመጣ ግን ከተመኘውም በላይ ሆነ።
ቡናው አንደኛ ወጣ።
የአምስት ዓመት ልፋቱ ፍሬ አፈራ። ያውም ጥሩ ፍሬ።
የለገሠ አንድ ኪሎ ቡና በውድድሩ ከፍተኛ በሚባል 884.10 ዶላር ተሸጠ።
47 ሺህ 236 ብር ገደማ ማለት ነው።
አንድ ኪሎ ቡና 47 ሺህ 236 ብር።
ይህም በኢትዮጵያ የቡና ታሪክ በከፍተኛ ዋጋ የተሸጠ ሆኖ ተመዘገበ።
ያቀረበው ቡና አጠቃላይ ዋጋ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አስገኘለት።
ውጤቱን ከሁለት ሳምንት በፊት ገደማ ነበር የሰማው።
“መረጃውን በወንድሜ በኩል ነው የሰማሁት። በጣም ነው ደስ ያለኝ” ብሏል ዜናውን የሰማበትን አጋጣሚ ሲገልጽ።
“ቡናው አንደኛ ይወጣል ብዬ አልጠበቅኩም። ግን ተመረጠ። ሌሎች ሲወዳደሩ እና ሲያሸንፉ አይቼ ቡናውን አጥቤ በሚፈለገው መንገድ ለውድድሩ አቀረብኩ። እስከ 40 ባለው ደረጃ ውስጥ ቢገባ ብዬ ነበር ያሰብኩት” ብሏል።
ለመሆኑ ይህ ቡና ምን ቢሆን ነው እንደዚህ ውድ በሆነ ዋጋ የተሸጠው?
አካባቢው ደጋማ ነው። ቡና ማምረት ያልተለመደበት አካባቢ።
“የቡናው ጥራቱ ለመሬቱ አዲስ በመሆኑ ይመስለናል። መሬቱ ኦርጋኒክ [ተፈጥሯዊ] ሲሆን ከቡና ጋር በተያያዘ ብዙም አልተጠቀምንበትም። ለብዙ ዓመታት ቢታረስም ቡና ግን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ነው የተተከለበት። ስለዚህ ቦታው ኦርጋኒክ ስለሆነ ቡና የሚፈልገውን ነገር ከመሬቱ ያገኘ ይመስለኛል” ሲል ይመልሳል።
ከዚህ ውጪ ይህ ነው ብሎ የሚያቀርበው ሌላ ምክንያትም አለ።
“አማኝ ነን” የሚለው ለገሠ “አማኝ ነን። ቡናውን ምርጥ ያደረገልኝ ፈጣሪ ነው” ይላል።
“እኔ ወደ ቡና ሥራ እንደገባሁ የተሳካላቸው እንዴት እንደሚሠሩ እከታተል ነበር። እኔም ቡናውን አድርቄ ነው የሸጥኩት። 40 ውስጥም እገባለሁ ብዬ አላሳብኩም። እግዚአብሔር ረዳኝ።”
ለገሠ ቡናውን ከመትከል ጀምሮ እስከ መንከባከብ ድረስ ይሳተፋል።
“(አንዳንዴ) ሠራተኛ ቀጥሬ አሠራለሁ። እኔም እየገባሁ እሠራለሁ። ሙሽራው ቡና ሲመጣ ስሩ ማዕድን ይዞ ስለሚመጣ እንዳይነካ እያደረኩ እየኮተኮትኩ እንከባከበዋለሁ። ከማሳዬ አልጠፋም።”
ለገሠ አሁን ሚሊየነር ሆኗል።
ብሩ እስካሁን እጁ ባይገባም፤ ከአሁኑ ግን ዕቅድ ተጀምሯል።
“ቡና ውስጥ ያልገመትኩት ነው የገጠመኝ። ሐዋሳ ከተማ ቤት ገዝቼ ለመግባት አስባለሁ። ሥራውን ማስፋፋትም እፈልጋለሁ። ቡና ዓለም ውስጥ በስፋት እገባለሁ” ይላል።
ጎረቤት፣ ዘመድ . . . በለገሠ ውጤት ማን ያልተደሰተ አለ?
በፊት ‘አቅም ያላቸው ናቸው የሚወዳደሩት’ በሚል ወደ ኋላ ያሉትንም እንዳነቃቃ ለገሠ ያስባል።
“አሁን ሌሎችም ለመወዳደር ፍላጎት አላቸው” ሲል በአካባቢው የፈጠረውን መነሳሳት ይገልጻል።
አልፎ አልፎ የግብርና ባለሙያዎች እየመጡ ‘እንዲህ ብታደርጉ እንዲህ ቢሆን ይህ ቢጨመር ይህ ቢቀነስ ይሏቸዋል።’
በውጤቱም ደስተኞች ሆነዋል።
መሬቱ ‘ለቡና’ አዲስ ስለሆነ ‘በደንብ ሥሩ’ ሲሉ ሌሎችንም እየመከሩ ነው።
አቶ ለገሠ በፊት እርጥብ ቡና ነበር ለገበያ የሚያቀርበው።
አሁን አድርቆ መሸጥ ችሏል።
የሚሸጠውም በአካባቢው ላሉ ነጋዴዎች ነበር።
አሁን በዓለም አቀፍ መድረክ መሸጥ ችሏል።
በዓመት እስከ መቶ ሺህ ብር ብቻ ያገኝ ነበር። በአሁኑ ወቅት ሚሊዮኖችን ማግኘት ችሏል።
አሁን ጉዞውን ጀምሯል። ዓይኑንም በቀጣዩ ውድድር ላይ ጥሏል።
“ከዚህ በሚበልጥ ሁኔታ ከዚህ በተሻለ ሁኔታ ተዘጋጅቼ ለውድድር እቀርባለሁ” ሲል ያጠናቅቃል።
ባለ ልዩ ጣዕም ቡና ውድድር
ይህ የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር ስፔሻሊቲ (ባለ ልዩ ጣዕም ቡና) ብቻ ሳይሆን ለየት ያለ ቡና ገዢዎች የሚገዙበት ነው።
ቡናውም ከመሸጡ በፊት በተለያየ ደረጃ እና አገራት ተቀምሶ፣ ደረጃ ወጥሎት ነው ለሽያጭ የሚቀርበው።
በውድድሩ ማሸነፍ እውቅና ይዞ ይመጣል።
ለገሠ ከዚህ በኋላ በተመሳሳይ ዋጋ ባይሸጥ እንኳን ቡናው ከሌሎች አምራቾች እኩል ዋጋ አይሰጠውም።
ከውድድሩ የሚገዛው ቡናም በተለየ ቡና መሸጫ በድንቅ ባለሙያ ተዘጋጅቶ በውድ ዋጋ ለገበያ ይቀርባል።
ሦስተኛው የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ከአሊያንስ ኮፊ ኤክሰለንስ እና ዩኤስኤይድ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።
በዘንድሮው ውድድር የኢትዮጵያ ቡና በታሪኩ ከፍተኛ በሚባል ዋጋ ተሽጧል።
የለገሠን አንድ ኪሎ ቡና በ884.10 ዶላር (47236 ብር) የገዛው የቻይናው ኤልኤንኬ ኮፊ ትሬዲንግ ነው።
ቀሪው ቡና ደግሞ ሳዛ ኮፊ ለሚባል ድርጅት ተሽጧል።
ዋጋው የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ሽያጭ ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል።
በዘንድሮው ውድድር ከ23 አገራት የተወጣጡ 170 ገዢዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
ከውድድሩ በኋላ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ “አርሶ አደሮቻችን አገራቸውን አኩርተዋል። የዘንድሮው ውድድር በብዙ ስኬት እና አስደናቂ ክብረ ወሰን ተጠናቋል” ብለዋል።
የዩኤስኤይድ ዳይሬክተር ሴን ጆንስ በበኩላቸው “በዚህ በዩኤስኤይድ ድጋፍ በሚካሄደው ውድድር በተለይም የቡናው ዘርፍ እንዲቀየር በማገዛችን ኩራት ይሰማናል። አነስተኛ ቡና አምራቾችን ከቡና ገዢዎች ጋር በማገናኘት አምራቾች ገቢያቸው እንዲያድግ ማድረግ ችለናል” ብለዋል።