የተፈጥሮ ጋዝ የሚጠቀሙ ከባድ መኪኖች ከቀረጥ ነፃ ሆነው ወደ አገር እንዲገቡ ተፈቀደ

በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ ማናቸውም ዓይነት የደረቅና የፈሳሽ ጭነት እንዲሁም የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከጉምሩክ ቀረጥ ነጻ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መፈቀዱን የገንዘብ ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ ማንኛውም በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰራ መኪና ከመስከረም 30/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ መፈቀዱን ይፋ አድርጓል።

ኢትዮጵያ ለነዳጅ ግዢ ታወጣ የነበረውን የውጪ ምንዛሬ የሚያስቀር ነው ያለውን የተፈጥሮ ጋዝ፣ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማበረታታት መወሰኑን ገልጿል።

ስለዚህ መመርያው ከወጣበት ከመስከረም 30/2018 ዓ.ም. ጀምሮ "በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ ማናቸውም አይነት የደረቅ እና የፈሳሽ ጭነት እና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከጉምሩክ ቀረጥ ነጻ ወደ አገር እንዲገቡ ተፈቅዷል" ሲል አሳውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሶማሌ ክልል የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክትን ባስመረቁበት ወቅት ነዳጅ የሚጠቀሙ ከባድ መኪኖችን ከመስከረም 22/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ማስገባት መከልከሉን አስታውቀው ነበር።

በሶማሌ ክልል ካሉብ በዓመት 111 ሚሊዮን ሊትር ማምረት የሚችለው የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የተመረቀ ሲሆን፤ 1.3 ቢሊዮን ሊትር በዓመት ያመርታል የተባለውን የፕሮጀክቱን ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ ደግሞ ተጀምሯል።

የገንዘብ ሚኒስቴር አስመጪዎች እንዲያውቁት ባወጣው በዚህ ማስታወቂያ በቀጣይ በተፈጥሮ ጋዝ የሚንቀሳቀሱ ከባድ ተሽከርካሪዎች ብቻ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ እንደሚፈቀድ አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሶማሌ ክልል ፕሮጀክቱን ባስመረቁበት ወቅት "ትላልቅ መኪና ወይም ትራክ ወደ ኢትዮጵያ ስታስገቡ የነበራችሁ ዜጎች ከዛሬ ጀምሮ [መስከረም 22/2018 ዓ.ም.] ልክ ትናንሽ መኪኖች ከኤሌትሪክ ውጪ ማስገባት ታግዶ እንደቆየው ከዛሬ ጀምሮ ነዳጅ የሚጠቀሙ ማንኛውም ትራክ ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት የተከለከለ ነው" ነበር ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንጻሩ ጋዝ የሚጠቀሙ ከባድ ተሽከርካሪዎች ለሚያስገቡ ባለሃብቶች ከሆነ ከቀረጥ ነጻን ጨምሮ መንግሥታቸው አስተማማኝ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴርም ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የተፈጥሮ ጋዛ ክምችት ሳትጠቀም ለዘመናት መቆየቷን አስታውቆ፣ በቅርቡ በካሉብ አካባቢ የሚገኘው የተፈጥሮ ጋዝ ማምረት መጀመሩን አስታውሷል።

አክሎም "ይህን ምርት ለአገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ቤንዚንና ናፍጣ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን የተፈጥሮ ጋዝ በሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች መተካት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል" ብሏል።

የተፈጥሮ ጋዝ የሚያመነጨው በካይ አየር እጅግ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን የጠቀሰው ሚኒስቴሩ "ለተለያየ የኃይል ምንጭ አገልግሎት ሊውል የሚችል፤ በኃይል አጠቃቀም ረገድ ውጤታማነት ያለው ነው " ብሏል።

ሚኒስቴሩ መመሪያውን ካወጣበት ቀን በፊት በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እና በሌሎች ተቋማት ወደ አገር እንዲገቡ ከተፈቀደላቸውና በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ወደ አገር ከሚገቡት በስተቀር በቤንዚን እና በናፍጣ የሚሰሩ የጭነት እና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር እንዳይገቡ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ ሚኒስቴሩ አዟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በ2018 ዓ.ም. ውስጥ ሁለት ሺህ የሚጠጉ የአዲስ አበባ ከተማ እና ወደ ክልል የሚሄዱ አውቶቡሶች "ከነዳጅ ወደ ጋዝ እንቀይራለን" ብለው ተናግረዋል።

"ቢበዛ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁለት ሺህ የሚጠጉ የአዲስ አበባ ከተማ እና ወደ ክልል የሚሄዱ ባሶች አሁን ከሚጠቀሙት ነዳጅ ወደ ጋዝ እንቀይራለን።"

እነዚህ ሁለት ሺህ አውቶብሶች ሲቀየሩ በ2019 ዓ.ም. የትራንስፖርት ዋጋ ቢያንስ በ50 በመቶ እንደሚቀንስም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ለግል ጥቅም የሚውሉ ነዳጅ የሚጠቀሙ አውቶሞቢሎችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት አግዳለች።