ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ሩሲያ የኔቶ አባልነት ክፍያቸውን የማይፈጽሙ አገራትን እንድታጠቃ “አበረታታለሁ” አሉ
ዶናልድ ትራምፕ በምዕራባዊያን ወታደራዊ ጥምረት ሕግ ገንዘብ የማይከፍሉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ትብብር ማኅበር (ኔቶ) አባል አገራትን እንድታጠቃ “እንደሚያበረታቱ” ተናገሩ።
በአንድ ወቅት ለኔቶ ኃላፊ ክፍያቸውን የማይፈጽሙ አባላት በሩሲያ ጥቃት ቢደርስባቸው ጥበቃ አናደርግም ብያቸዋለሁ የሚሉት ትራምፕ ሩሲያ “የፈቀደችውን እንድታደርግ እንደሚያበረታቱ” ተናግረዋል።
የኔቶ ቃለ-መሐላ እንደሚለው አንድ አባል አገር ጥቃት ቢደርስባት ጥምረቱ እርምጃ ይወስዳል።
ዋይታ ሐውስ የቀድሞው ፕሬዝዳንት የሰጡት አስተያየት “አስገራሚ እና አስፈሪ ነው” ብሏል።
ቅዳሜ ዕለት በሳውዝ ካሮላይና ግዛት ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ያሰሙት ትራምፕ፣ ስለኔቶ አስተያየት የሰጡት በጥምረቱ ስብሰባ ላይ እንደሆነ ገልጸዋል።
እሳቸው እንደሚሉት የአንድ “ትልቅ አገር” መሪ ክፍያ መፈጸም ባይችል እና ከሩሲያ ጥቃት ቢፈጸምበብ ምን ሊገጥመን ይችላል ብለው ጥያቄ አቅርበው ነበር።
አክለው እኒህ መሪ ይህ ቢሆን ዩናይትድ ስቴትስ ታግዘናለች ወይ ብለው መጠየቃቸውን አውስተዋል።
“እኔ እንዲህ አልኩ፡ 'መክፈል አትችልም?' 'አቅምህ አይችልም?'፤ እኔ ልጠብቅህ አልችልም፤ እንዲያውም የፈለጉትን እንዲያደርጉ ነው የምገፋፋቸው። መክፈል አለብህ።”
የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ የቀድሞው ፕሬዝዳንት “ጨካኝ አመራሮች አጋሮቻችንን እንዲወሩ እያበረታቱ ነው” ብለው አስተያየታቸው “አስገራሚ እና አስፈሪ ነው” መሆኑን ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም የቀድሞው ፕሬዝዳንት አስተያየት “የአሜሪካን ብሔራዊ ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል፤ ዓለም አቀፍ መረጋጋትን የሚያቃውስ እና ኢኮኖሚያችንን የሚያናጋ ነው” ብለዋል።
ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው በሚቀጥለው ዓመት በሚደረገው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደሚሳተፉ ትልቅ ግምት የተሰጣቸው ትራምፕ የኔቶ ነቃፊ ናቸው።
ኔቶን አሜሪካ የ30 አገራትን ደኅንነት ለመጠበቅ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮች የምትገፈግፍበት ጥምረት ነው ብለው ያስባሉ።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ነው ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2022 በሙሉ ኃይሏ ዩክሬንን የወረረችው።
ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ የኔቶ አባል ላልሆነችው ዩክሬን አሜሪካ የሰጠችው ድጋፍ ከፍተኛ ነው ሲሉ በተጋጋሚ ትችት አሰምተዋል።
አሜሪካ ከየትኛው አገር በላቀ ለዩክሬን ትልቅ የገንዘብ ድጋፍ አድርጋለች።
ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ባለው ጊዜ ብቻ አሜሪካ ለዩክሬን 44 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን ባለፈው ታኅሣሥ ዋይት ሐውስ ያወጣው ዘገባ ያሳያል።
ነገር ግን የአሜሪካ ኮንግረስ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ከያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት ጀምሮ አሜሪካ የምታደርገው ድጋፍ እንዲቋረጥ አድርገዋል።
ትራምፕ በቅዳሜው ንግግራቸው የኮንግረስ አባላት የወሰዱትን እርምጃ አወድሰው የፕሬዝዳንት ባይደን ዕቅድ “ድብልቅልቅ ያለ ነው” ሲሉ ተችተዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሚቀጥለው የአሜሪካ ምርጫ እንደሚፋጠጡ ይጠበቃል።