ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ባለሥልጣናት ያሉበት የአሜሪካ ልዑካን ሰኞ አዲስ አበባ ይገባል
ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለሥልጣናትን ጨምሮ የተለያዩ የአሜሪካ መንግሥት የባለሥልጣናት ቡድን ከነገ ሰኞ ጀምሮ ለቀናት በአዲስ አበባ እንደሚቆይ ተገለጸ።
ለስድስየአፍሪካ ኅብረት ጉባዔን አስታኮ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣው የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተካተቱበት ልዑክ በቆይታው ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚወያይ ታውቋል።
ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ ሲመላለሱ የነበሩት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ፀሐፊ የሆኑት ሞሊ ፊ እና በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛው አምባሳደር ማይክ ሐመር በልዑኩ ውስጥ ይገኛሉ።
ሞሊ ፊ በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ በሁለትዮሽ እና በቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አመልክቷል።
ሰኞ የካቲት 4/2016 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ የሚገባው እና ለስድስት ቀናት የሚቆየው የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የልዑካን ቡድን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ የጤና እና የአገሪቱ የተራድኦ ድርጅት ተወካዮችን ያካተተ ነው።
የአሜሪካ መንግሥት የከፍተኛ ባለሥልጣናት የልዑካን ቡድን በአዲስ አበባ ውስጥ ከየካቲት 4 አስከ 9/2016 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ ይሆናል።
ልዑኩ በሚቀጥለው ሳምንት በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ላይ ከሚሳተፉ የአገራት መሪዎችን እና ሚኒስትሮች እንዲሁም ከኅብረቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚወያዩ ተነግሯል።
ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ባለሥልጣናት በተጨማሪ በዓለም አቀፍ የጤና ደኅንነት እና ዲፕሎማሲ ከፍተኛ ባለሥልጣን ዶ/ር ጆን ንኬንጋሶንግ፣ የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ ረዳት አስተዳዳሪ ሞንዴ ሙያንግዋን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በልዑኩ ውስጥ ይገኙበታል።
37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በመጪው ቅዳሜ የካቲት 9 እና እሁድ የካቲት 10/2016 ዓ.ም. የሚካሄድ ሲሆን፤ ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ የአባል አገራት የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ረቡዕ የካቲት 6 እና ሐመስ የካቲት 7/2016 ዓ.ም. ይካሄዳል።