የአሜሪካ ልዑክ ከኒጀር ወታደራዊ ጁንታ ጋር ጠንከር ያለ ውይይት አካሄደ

ባለፈው ወር የተካሄደውን የኒጀር መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት ከመፈንቅለ መንግሥት መሪዎቹ ጋር የፊት ለፊት ውይይት አካሂደዋል።

የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቪክቶሪያ ኑላንድ እንደተናገሩት “ውይይቱ በጣም ግልጽ ነገር ግን ከባድ ነበር” ብለዋል።

አሜሪካ መፈንቅለ መንግሥቱ በዲፕሎማሲ እንዲጠናቀቅ እና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ባዙም ወደ ሥልጣናቸው እንዲመለሱ ሃሳብ ያቀረበች ሲሆን ለአገሪቱ የምትሰጠውን እርዳታ ለጊዜው አቋርጣለች።

ሰለኒጀር ቀውስ ለመወያየት የምዕራብ አፍሪካ አገራት በቀጣዩ ሐሙስ ቀጠሮ ይዘዋል።

ኢኮዋስ የተሰኘው የምዕራብ አፍሪካ የንግድ ማህበረሰብ እስከ ቀጣዩ እሁድ ድረስ ወታደራዊው መሪ ሥልጣኑን ለቀድሞው ፕሬዝዳንት እንዲያስረክብ የጊዜ ገደብ አስቀምጧል።

በአጸፋው የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ወታደራዊ ማስፈራሪያ በመስጠት ምላሽ ሰጥቷል።

ለሁለት ሰዓት በቆየው የአሜሪካ እና የኒጀር መሪዎች ውይይት ጉዳዩን ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሂደት የሚመልሱ ከሆነ አሜሪካ እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።

ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ እንዳሉት አዲሱን የጦር ኤታማዦር ሹም ሙሳ ሳሉ ባርሙ ያገኙት ሲሆን የአገሪቱ መሪ ሆነው ከተመረጡት ጀኔራል አብዱራህማን ቺያኒን እን ማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባዙም በእስር ላይ ቢሆኑም ከቀናት በፊት ግን ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር በስልክ መገናኘት ችለው ነበር።

ኑላንድ አዲሱ የመፈንቅለ መንግሥት መሪ አገሪቱን ለመቆጣጠር የሩሲያውን ቫግነር ቅጥረኛ ቡድን እርዳታ መጠየቁ እንዳሳሰባቸውም ለጀኔራል ሙሳ አስረድተዋል።

የኒጀር መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደው ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ ነበር። በአገሪቱ የተከሰተውን ሁኔታ ተከትሎ አገራት ዜጎቻቸው ወደ ኒጀር እንዳይጓዙ እያስጠነቀቁ ነው።

የቀድሞ ቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ ዜጎቿ ወደ ኒጀር እንዳያመሩ አስጠንቅቃለች። ኒጀር ውስጥ የሚኖሩትንም ለፈረንሳይ ያለው ጥላቻ እየተስፋፋ በመምጣቱ ተጨማሪ የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንዲወስዱ አሳስባለች።

የኢኮዋስ ወታደራዊ መሪ ኃይል እንደሚጠቀሙ ማስታወቃቸውን ተከትሎ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠሩት ጀኔራል አብዱራህማን “ሊወረን የተዘጋጀ የውጭ ኃይል አለ” ብለዋል።

ባለፈው ሳምንትም የናይጄሪያ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በኒጀር ጉዳይ ስለወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አስላጊነት ላይ ውይይት አድርጓል።

ቢሆንም ግን የምክር ቤት አባላቱ በተለይም ከኒጀር ጋር ረጅም ድንበር ከሚጋሩባቸው የናይጀሪያ አካባቢዎች የተወከሉ ተመራጮች ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቱን በአጽንኦት መቃወማቸውን የአገር ውስጥ ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል።

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ቲኑቡ በኒጄር ላይ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንዲደረግ በብርቱ ይፈልጋሉ። ነገር ግን ይህንን ለማስፈጸም የብሔራዊ ምክር ቤቱ ማጽደቅ ይኖርበታል።

በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የተቆጣጠረው አካል ሂደቱን ወደ ኋላ በመመለስ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት የመመለስ ፍላጎት እንዳለው አላሳየም። እንዲያውም በዋና ከተማዋ ኒያሚ ደጋፊዎቹን ሰልፍ አስወጥቷል።

በምዕራብ አፍሪካ የምትገኘው ኒጀር ከዓለም በድህነት ጅራት ላይ ከሚገኙት አገራት መካከል ነች።

አገሪቱ ያለባትን የጸጥታ ችግር ለመፍታት እና የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ ለማድረግ መፈንቅለ መንግሥት ማድረጋቸውን ወታደራዊ መሪዎቹ ገልጸዋል።

ቢሆንም ግን ከብዙ አገራት ዘንድ ውግዘት እየደረሰባቸው ነው።

ይህንን ተከትሎም ወታደራዊ መሪው አሜሪካ እና ፈረንሳይ በአገሪቱ ያላቸውን ወታደራዊ ይዞታ በማንሳት በምትኩ ሩሲያን ሊጋብዝ ይችላል የሚል ስጋት አለ።