ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“የአማራ ክልል ችግር በውይይት እና በድርድር የሚፈታበት መንገድ ዝግ አይደለም” መንግሥት
በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲደነገግ ምክንያት የሆነውን በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት መፍትሔ እንዲያገኝ ውይይት እና ድርድር ሊደረግ እንደሚችል መንግሥት አስታወቀ።
ይህ የተመለከተው የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት በዚህ ዓመት ያከናወናቸውን ሥራዎች በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ ሲሆን ችግሩን ለመፍታት ጥረቶች እንደሚደረጉም ገልጿል።
የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎች ህልውና አብቅቶ ወደ ተለያዩ የፀጥታ እና የመከላከያ መዋቅሮች እንዲካተቱ መወሰኑን ተከትሎ፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን መፍረስን በመቃውም የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እና ግጭት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ክልሉን ቀውስ ውስጥ ከትቶታል።
በፀጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ሲካሄድ የቆየው ግጭት እና የተኩስ ልውውጥ ከክልሉ አቅም በላይ ሆኖ የፌደራል መንግሥቱን ድጋፍ በመጠየቁ፣ ባለፈው ሳምንት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል።
የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አግልግሎት ዳይሬክትር እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ዋና ሰብሳቢ አቶ ተመስገን ጥሩነህ እሁድ ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ ታጣቂው ኃይል የዞን እና የወረዳ ከተሞችን መቆጣጠሩን እና የክልል እና የፌደራል መንግሥትን የመጣል ዓላማ አለው ብለው ነበር።
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅመው ዕዝን የሚያስተባብረው የደኅንነት ተቋሙ ሰኞ ነሐሴ 01/2015 ዓ.ም. ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ፣ አስፈላጊውን ሁሉ ተግባር እያከናወነ መሆኑን አመልክቶ “ችግሩ በውይይት እና በድርድር የሚፈታበት መንገድ ዝግ ባለመሆኑ ተከታታይ ጥረቶች ይደረጋሉ” ብሏል።
ከዚህ መንገድ በማፈንገጥ ለዝርፊያ ከተደራጁ ቡድኖች ጋር የሚንቀሳቀሱ አካላት ካሉ በሚጠናቀሩ መረጃዎች መሠረት አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድባቸው እና ሕግ የማስከበር ሂደቱም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ጨምሮም ከድርድር እና ከውይይት ይልቅ መንግሥታዊ ሥልጣንን በኃይል ለመያዝ የሚጥሩ፣ እንዲሁም አጋጣሚዎችን በመጠቀም ዝርፊያ ለመፈጸም የሚፈልጉ “የታጠቁ ቡድኖች፣ ጽንፈኛ እና አክራሪ ኃይሎች ከውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የፀጥታ ሥጋት ለመደቀን ሙከራ እያደረጉ ነው” በማለት የደረሰበትን ድምዳሜ የደኅንነት ተቋሙ ጠቅሷል።
በአማራ ክልል የተከሰቱ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ከዚህ ቀደም ከመንግሥታዊ ተቋማት፣ ከአገር ሽማግሌዎች እና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ተከታታይ ጥረቶች መደረጋቸውን የጠቀሰው የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎቱ፣ ቢሆንም ግን ለችግሩ መፍትሔ ማግኘት እንዳልተቻለ ገልጿል።
“ለዘረፋ የተደራጁ ጥቂት ኃይሎች” ያላቸውም በአሁኑ ወቅት መንግሥታዊ መዋቅሮችን እንዲፈርሱ፣ የገንዘብ ተቋማት አገልግሎት እንዲቋረጥ፣ የመንገድ መሠረት ልማቶች እንዲዘጉ በማድረግ፤ ሕዝቡ ላይ ዘርፈ ብዙ ጫና ለመፍጠር ሙከራ እያደረጉ ይገኛሉ ብሏል።
የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት በአማራ ክልል ያጋጠመውን ችግር በድርድር እና በውይይት ለመፍታት መንግሥት ፍላጎት እንዳለው ቢገልጽም፣ ዝርዝር ሁኔታዎች ከመግለጽ ግን ተቆጥቧል።
በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ችግር መባባሱን ተከትሎ የሃይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪል ማኅበራት ጉዳዩ በውይይት እንዲፈታ መግለጫዎችን በማውጣወት ለሁሉም ወገኖች ጥሪ ሲያርቡ ቆይተዋል።
በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ሲካሄድ የሰነበተው ግጭት እና የተኩስ ልውውጥ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች፣ በተለይም በከተሞች ውስጥ እንደቀጠለ መሆኑን ሰኞ ዕለት ቢቢሲ ያናገራቸው በዋና ዋና ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ካለፈው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ እየተባባሰ የሄደው ግጭት የአማራ ክልል ዋና ከተማ የሆነችውን ባሕር ዳርን ጨምሮ የዞን ዋና ከተሞችን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ አስተጓጉሎታል።
መንገዶች በመዘጋታቸው የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች የተስተጓጎሉ ሲሆን፣ ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ወዲህ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በክልሉ መደበኛ በረራ የሚያደርግባቸው ቢያንስ የሦስት ከተሞች በረራዎች ተሰርዘዋል።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የታወጀውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ለማስፈጸም የተዋቀረው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ሕግ እና ሥርዓትን የማስከበር ሥራውን በማከናወን ክልሉ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው በአጭር ጊዜ እንዲመለስ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
የአማራ ክልል፣ የመላከያ ሠራዊት፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አግልግሎት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የብልጽግና ፓርቲ እና ከኮምዩኒኬሽን አግልግሎት የሚገኙበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ፣ በክልሉ ሕግ እና ሥርዓትን ማስከበር እንዲሁም የመንግሥት እና የፓርቲ መዋቅርን መልሶ የማጠናከር ሥራዎችን እንደሚያከናውን ተገልጿል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለስድስት ወራት ተግባራዊ ይሆናል ብሎ ባለፈው አርብ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. የደነገገረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።