ኢትዮጵያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወዳጅነት ምን አተረፈች?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን በመጡ ማግስት ከጎበኟቸው አገራት መካከል የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከቀዳሚዎቹ አንዷ ናት።

በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሦስት ቀናት ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝታቸው የተጀመረው ወዳጅነት እስካሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወራት ልዩነት ተመልሰው ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ያቀኑ ሲሆን፣ የኤምሬቶችም ልዑካኗን በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ ልካለች።

እአአ በ2018 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን ወደ አዲስ አበባ በመላክ ከኢትዮጵያ ጋር በበርካታ ዘርፎች የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርማለች።

በወራት ልዩነት ደግሞ በወቅቱ የአቡ ዳቢ ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ዛይድ አዲስ አበባ መግባታቸውም የአገራቱን ትብብር የማሳደግ ፍላጎትን ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።

የቀድሞው አልጋ ወራሽ የአሁኑ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት መሐመድ ቢን ዛይድ ባለፈው ሳምንትም በድጋሚ ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል።

የሠላም ስምምነት

ኤርትራዊው የፖለቲካ ተንታኝ አብዱራህማን ሰኢድ አቡ ሓሽም ሁለቱ መሪዎች በተለያዩ ጊዜያት ያደረጓቸውን ጉብኝቶችን በመጥቀስ፣ ፕሬዝዳንቱ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳላቸው ያነሳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን በመጡ ማግስት ከኤርትራ ጋር የሠላም ስምምነት እንዲፈራረሙ ማገዛቸውን አንስተዋል።

የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሠላም እንዲወርድ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የአገሪቱን ከፍተኛ የክብር ሽልማት አበርክታለች።

ኤምሬቶች ከኤርትራ በተጨማሪ ኢትዮጵያ፣ ከሱዳን እና ከግብፅ ጋር ያላትን አለመግባባት ለመፍታትም በተደጋጋሚ ሙከራ አድርጋለች።

ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ከስምምነት እንዲደርሱ የተለያዩ ጥረቶችን ማድረጓም አይዘነጋም።

አቡ ዳቢ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ ለማድረግ ጥረት አድርጋለች።

ውስጣዊ ችግሮች እና ኤርትራ

የአሁኑ የመሐመድ ቢን ዛይድ ጉብኝት ዓላማ ትኩረቱን በአገር ውስጥ ጉዳይ ላይ ያደረገ ሊሆን እንደሚችል አቡ ሓሽም ያምናሉ።

“በአማራ (ክልል) ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየታዩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተቀባይነት እያሽቆለቆለ መሄዱም የሚታይ ነገር ነው” ይላሉ።

“የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውስጣዊ ድክመት እየታየ ነው። አስተዳደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሌላም ሌላም ችግሮች ተጨማምረው ብዙ ድክመት ይታያል። ችግሩ የመፈንዳቱ ነገር የጊዜ ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል” ብለዋል።

የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት አገራቸው ከእነዚህ ችግሮች የመውጫ መንገዶችን ለማሳየት ሊሆን እንደሚችል አቡ ሓሽም ይገምታሉ።

ሌላኛው ግምታቸው ደግሞ ከኢትዮ-ኤርትራ ግንኙት ጋር የተያያዘ ነው።

የሁለቱን አገራት መሪዎች ለሽልማት ያበቃቸው የሠላም ስምምነት ‘እየሻከረ’ ይገኛል የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ፣ በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተካሄደው ጦርነት የተቋጨበት መንገድ ፕሬዝዳንት ኢሳያስን የሚያስደስት እንደማይሆን ይገልጻሉ።

በጦርነቱ ወቅት ከሁለቱ መንግሥታት ጎን የቆሙት ፋኖዎች እና የአማራ ክልል ሚሊሻዎች ትጥቅ እንዲፈቱ መጠየቁ፣ የተለያዩ ጥያቄዎቻቸው አለመመለሳቸው እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ውግንናቸው ከአሜሪካ እና ከህወሓት ጋር ያደረጉ መስሎ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ‘ሊታያቸው’ ይችላል ይላሉ።

አክለውም “በዚህ መንገድ ያላቸው መተማመን በጣም ተጎድቷል ሊባል ይችላል። እስከ መጣራጠርም ተደርሷል” ብለዋል።

ምንም እንኳን ከመንግሥት ይፋዊ መንጭ የተጠቀሰ ባይሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደብ ለማግኘት ኃይል ጭምር ሊቀጠቀሙ እንደሚችሉ ተነግሯል ተብሎ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

“የወደቡን ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ ባይገልጹትም እየሻከረ የሚመስለውን ግንኙነት የባሰ ሊያበላሸው የሚችል ነው” ይላሉ ኤርትራዊው የፖለቲካ ተንታኝ።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወደ ኢትዮጵያ ማቅናቷ ይህንን ከግምት አስገብታ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ።

“ኢትዮጵያ ካለ ኤርትራ የሚያጋጥማትን ታላላቅ ችግሮችን ብቻዋን የመፍታትም አቅሟ በአሁኑ ደረጃ አለመኖሩ ሊታያቸው ይችላል። . . . የእነዚህ አገሮች መደጋገፍ ለሁለቱም ዋስትና ነው። በተለይም በቀውስ ውስጥ የምትገኘው ኢትዮጵያ በመሆኗ፣ የኤርትራ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት በማሰብ ይመስላል” ብለዋል።

ጥያቄው ከኢትዮጵያ በኩል ቀርቦ ሊሆን እንደሚችልም አቡ ሓሽም ይገምታሉ።

“ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር አስታርቁን። ያለኝ ውስጣዊ ችግሮችም ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር ለመፍታት እፈልጋለሁ ብለውም ሊሆን ይችላል። በራሳቸው ተገናኝተው ሊፈቱት ያልቻሉትን የጋራ ወዳጅ ጠርቶ ይህን ነገር እንድንፈታ እርዳን ሊሉት ይችላሉ” ብለዋል።

ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ

በዚህ ጉብኝት ሁለቱም አገራት ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚያነሱት የፖለቲካ ተንታኙ፣ “[ጉብኝቱ] የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የተጽዕኖ መድረኳን የምታሰፋበት ይሆናል። ኤርትራ እና ኢትዮጵያ የቅርብ ወዳጆች በመሆናቸው ለውጭ ግንኙነት ፖለሲያቸውም ሆነ ለግንኙነታቸው ሚዛን ይሰጠዋል። እነሱም ተጠቃሚ ናቸው” ብለዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከኢትዮጵያ የምትፈልገው ብዙ ነገር ሊኖር እንደሚችል እና በተለይ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የእርሻ ምርት አቅራቢዎቿ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገልጻሉ።

“[ኢትዮጵያ እና ሱዳን] ብዙ የእርሻ መሬት አላቸው፤ የዝናብ እረጥረት የለባቸውም። በውሃ አቅርቦት ሊደግፏት ይችላሉ። [የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች] የውሃ እጥረት አለባቸው። ኢትዮጵያ የሚጠጣም ይሁን ሌላ ውሃ የማቅረብ ዕድል አላት” ብለዋል።

ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ፣ ለኤምሬቶች ምቹ ኢንቨስትመንት አማራጭ ልትሆንም ትችላለች።

ትልቁ ጉዳይ ደግሞ ዲፕሎማሲ ነው።

አዲስ አበባ አፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ናት። በዓመት ሁለት ጊዜ ከሚካሄዱት የአህጉሪቱ መሪዎች ስብሰባዎች አንደኛው አዲስ አበባ ላይ ይከናወናል።

ይህ ደግሞ ለኤምሬቶች 54 የአፍሪካ አገራትን በቀላሉ ለማግኘት አቋራጭ መንገድ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኙ ይገልጻሉ።

አፍሪካ ቀንድ ደግሞ ኃያላን አገራት ቀልባቸውን ከጣሉባቸው አካባቢዎች ቀዳሚው ነው።

ኢትዮጵያ በአካባቢው በተለያዩ መስፈርቶች ‘ከባድ ሚዛን’ መሆኗን አንስተው ኤምሬቶች “በኤርትራም ሆነ በጅቡቲ የሚፈልጉትን ለመፈጸም ኢትዮጵያን ይዘው በቀላሉ ሊያራምዱት ይችላሉ” ብለዋል።

ይህ ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳው ደግሞ ከሁሉም በላቀ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና አገራቸው ከዚህ ጉብኝት እንደሚያተርፉ ይገልጻሉ።

“ግንኙነቶች ከኤርትራ ወይም ከአጎራባች አገራት ጋር ሲሻክር የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የመርዳት እና የመደገፍ አቅም ሊኖራት ይችላል” ብለዋል።

ወታደራዊ ስምምነቶች

በተለያዩ ጊዜያቶች ወታደራዊ ስምምነቶችን የተፈራርሙት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ኢትዮጵያ በወታደራዊ መስክም ግንኙነታቸው እየጠነከረ ያለ ነው።

16ኛው የጦር አውሮፕላኖች ትርዒት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በ2012 ዓ.ም. ተከናውኗል።

በዚያ ወቅትም ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በመካከላቸው ወታደራዊ ትብብርን ለማጠናከር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው ተገልጾ ነበር።

ከዚያ በኋላም ለሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት የሁለቱ አገራት ስም አብሮ ተደጋግሞ ተነስቷል።

በጦርነቱ ወቅት መቀመጫቸውን በኤርትራ ያደረጉ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወታደራዊ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወይንም ድሮኖችን ተጠቅመዋል የሚል ክስ ተሰምቶ ነበር።

በወቅቱ በትግራይ የፌደራል መንግሥቱ ላይ ነፍጥ ያነሱት ኃይሎች “. . .አሰብ የሚገኙ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖችን) ድጋፍ እየጠየቁ ነው” ሲሉ ቅሬታ አሰምተው ነበር።

ለዚህ ክስ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በወቅቱ፣ አየር ኃይሉ በጦር አውሮፕላኖች፣ ሚሳኤሎች እና ድሮኖች ጥቃት እየፈጸመ መሆኑን አረጋግጠው “ራሳችንን አሰልጥነን አስታጥቀናል። . . .ሌሎቹ መግለጫዎች ውሸት ናቸው። ራሳችንን በገነባነው ኃይል ጠላትን እያጠፋን ነው” ብለው ነበር።

የውጭ ምንዛሪ

በኢትዮጵያ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለዓመታት በመንከባለል ላይ ይገኛል።

ይህ ደግሞ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ማስከተሉ ተደጋግሞ ተነስቷል።

“በዚህም ደረጃም [ኤምሬቶች] ሊረዷት ይችላሉ። አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ብዙ ሊጠቅሟት ይችላሉ። ከዚህ በፊትም ረድተዋል” ብለዋል አቡ ሓሽም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን እንደመጡ በአቡ ዳቢ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በቀጥታ ወደ ማዕከላዊ ባንክ የሚገባ፤ እንዲሁም በውጭ የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መልክ ለኢትዮጵያ በጥቅሉ 3 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት መስማማቷ ይታወሳል።

ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ሲደርሱ ሞቅ ያለ አቀባበል የጠበቃቸው ፕሬዚዳንት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸው ተገልጿል።

መሪዎቹ በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ እንደመጣ መናገራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መረጃ አመላክቷል።

በጉብኝቱ ወቅትም በሁለቱ አገራት መካከል ኢንዱስትሪን፣ ግብርናን፣ ኢንቨስትመንትን እና ፋይናንስን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች 17 ስምምነቶች መፈረማቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ይህም ሁለቱ አገራት በውስን መስኮች ላይ ሳይሆን በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር እና ግንኙነት የሚያጠናክር እንደሚሆን ይታመናል።