የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የትምህርት ቋንቋ አማርኛ እንዲሆን ተወሰነ

የፎቶው ባለመብት, Benishangul Gumuz Education Bureau
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ከዘንድሮ ዓመት ጀምሮ የክልሉ የትምህርት ቋንቋ አማርኛ እንዲሆን እና ሰባት የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች "እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት" እየተሰጡ እንዲቀጥሉ ወሰነ።
"ጊዜያዊ ነው" የተባለው ይህ አሠራር በዚህ ዓመት በቅድመ መደበኛ (ኬጂ) እና በአንደኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ የሚተገበር ሲሆን በየዓመቱ ወደ ሌሎች የክፍል ደረጃዎች እያደገ እንደሚሄድ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገልጿል።
የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ የሆነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፤ በክልሉ በሚነገሩ አፍ መፍቻ ቋንቋዎች ትምህርት መስጠት የጀመረው በ2001 ዓ. ም. ነበር።
የመማር ማስተማሪያ ቋንቋ ሆነው ከሚያገለግሉት አፍ መፍቻዎች መካከል ቤኒሻንጉልኛ፣ ጉምዝኛ፣ ሽናሽኛ እና ማኦኛ ይገኙበታል። ኮሞኛ፣ ጓምኛ፣ ኦሮምኛ እና አማርኛም ትምህርት ይሰጥባቸው ከነበሩ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች መካከል ናቸው።
በክልሉ የሚገኙ ተማሪዎች ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ሒሳብ እና የሳይንስ ትምህርት አይነቶችን በእነዚህ ቋንቋዎች የሚማሩ ሲሆን ሰባተኛ ክፍል ላይ የመማር ማስተማሪያ ቋንቋው እንግሊዘኛ ይሆናል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ትምህርት ቢሮ በክልሉ ላሉ የወረዳ፣ ልዩ ወረዳ ከተማ አስተዳደር መዋቅሮች በጻፈው ደብዳቤ ከዘንድሮ የ2018 ትምህርት ዘመን አንስቶ ይህ አሠራር መቀየሩን አስታውቋል። የቢሮው ኃላፊ ዶ/ር ተመስገን ዲሳሳ ውሳኔው መተላለፉን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በቢሮ ኃላፊው የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው ላለፉት 17 ዓመታት ተግባራዊ ሲሆን የቆየው አሠራር የተቀየረው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ካቢኔ ባለፈው ወር መስከረም 10/2018 ዓ. ም. ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነው።
ከሁለት ሳምንት በፊት በመስከረም 21 ለክልሉ ትምህርት ቢሮ የደረሰው የካቢኔው ውሳኔ የተመሠረተው፤ በ2017 ዓ. ም. በተደረገ ጥናት ላይ እንደሆነ ተጠቅሷል።
ደብዳቤው፤ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎቹ በመማሪያ ማስተማሪያነት ጥቅም ላይ በሚውሉበት ጊዜ "የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ" ይገልጻል።
ይህ የሆነውም "ከሚያስፈልገው የመምህራን ቁጥር እና ብቃት፣ ከግብአት እና ከሌሎች ችግሮች" ጋር በተያያዘ እንደሆነ ይገልጻል።
ይህንን ሐሳብ የሚያጠናክሩት የትምህርት ቢሮው ኃላፊው ዶ/ር ተመስገን፤ "[መምህራን] በቂ አይደሉም፤ እንደውም የሉም ማለት ይቻላል። ያሉትም [ላይ] የአቅም ማነስ አለ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሕጻናት "በራሳቸው ቋንቋ በሚማሩበት ጊዜ አካባቢውን በአግባቡ ይረዳሉ፣ የትምህርት ይዘቱንም ይረዳሉ" ተብሎ እንደሚታሰብ የገለጹት ዶ/ር ተመስገን፤ "ይህ ሊሆን የሚችለው [ግን] ሊያስተምር የሚችል፣ በራሱ ብቁ የሆነ መምህር ሲኖር ነው" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Benishangul Gumuz Region Communication
ቋንቋዎቹን እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ለመስጠት የሚሆን የመምህር እጥረት አለመኖሩን የሚናገሩት ኃላፊው፤ ሒሳብ እና ሌሎች የሳይንስ ትምህርቶችን በአፍ መፍቻ ለማስተማር "የተመረቀ መምህር" ግን አለመገኘቱን ገልጸዋል።
"ያሉትም ቢሆን በሌላ ከተማሩ በኋላ ሁለት ወር ወይም አንድ ወር ቋንቋ ትርጉም እና [ተያያዥ] ሥልጠና የወሰዱ ናቸው" ብለዋል።ይህ ጉዳይ "የተማሪዎች ውጤት ላይም ተጽዕኖ እያሳየ" መምጣቱን አክለዋል።
ዶ/ር ተመስገን ይህንን ጉዳይ በደብዳቤያቸው ላይም ጠቅሰውታል።ቢሮው፤ ይህንን "ችግር ለመፍታት እና የተማሪዎችን የመማር ውጤት ለማሻሻል በ2017 ዓ. ም. ያጠናውን" ጥናት ለክልሉ ካቤኒ እንዳቀረበ ደብዳቤው ያስረዳል።
ካቤኒውም፤ "የክልሉ አቅም እስኪጎለብት እና ያሉ ችግሮች በሂደት እስኪፈቱ ድረስ በክልሉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት መማሪያ ማስተማሪያ ቋንቋ አማርኛ እንዲሆን" ወስኗል ተብሏል።
"የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ደግሞ አንድ አንድ የትምህርት ዓይነት [ሆነው] ብቻ እንዲቀጥል" ካቢኔው እንደወሰነ ደብዳቤው ላይ ሰፍሯል። "የሽግግር ሂደት ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ እየተዘጋጀ" እንደሆነም ይጠቅሳል።
ዶ/ር ተመስገን እንደሚያስረዱት በዚህ ዓመት ይህ ውሳኔ መተግበር የሚጀምረው በቅድመ መደበኛ (ኬጂ) እና በአንደኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ ነው። በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች ይህንን አሠራር መተግበር እንደሚጀምሩ እና በቀጣዮቹ ዓመታት ሌሎቹም የክፍል ደረጃዎች እንደሚቀላቀሉ አብራርተዋል።
ቢሮው ይህንን አካሄድ የመረጠው ከአንደኛ ክፍል አንስቶ በአፍ መፍቻ ቋንቋ እየተማሩ ያሉ ተማሪዎች ላይ አዲስ አሠራር ላለመተግበር በማሰብ መሆኑንም ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Benishangul Gumuz Education Bureau
አማርኛን በክልሉ የትምህርት ቋንቋነት የመጠቀም አሰራር የሚቀጥለው በአፍ መፍቻ ቋንቋዎቹ "ብቁ የሆኑ፣ ፍላጎት ያላቸው ሰልጣኝ እና መምህራን እስከሚዘጋጁ ድረስ" ነው።
አዲሱ አሰራር በሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት ሙሉ በሙሉ ከተተገበረ በኋላ "ውጤቱን አይተን፣ በዚህ በኩል ደግሞ መምህር አምርተን የምንጨርስ ከሆነ ከዛ ደግሞ እንቀይራለን" ሲሉ የክልሉን መንግሥት እቅድ አስረድተዋል።
የካቲት 2015 ዓ. ም. የጸደቀው አዲሱ የትምህርት እና ሥልጠና ፖሊሲ፤ የአፍ መፍቻ ቋንቋ "ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ"፤ "እንደ የትምህርት ዓይነትነት እና እንደ ማስተማሪያ ቋንቋነት" እንደሚሰጥ አስቀምጧል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገ መንግሥትም "በክልሉ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች በራሳቸውና በፈለጉት ቋንቋ የመማር መብት አላቸው" በማለት ደንግጓል።
የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ተመስገን አዲሱ የክልሉ መንግሥት ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ ጋር "አይቃረንም" የሚል አቋም አላቸው።
አዲሱ ውሳኔ "በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማርን የማስቀረት ሥራ አይደለም" የሚሉት ኃላፊው፤ ቋንቋዎቹ አንደ አንድ የትምህርት ዓይነት የመሰጠታቸውን ጉዳይ አጽንኦት ሰጥተውበታል።
"በሳይንስ እና በሒሳብ የሠለጠኑ መምህራን እስከሚገኙ ድረስ ባለው መምህር በዚህኛው የማስተማሪያ ቋንቋ (medium of instruction)፤ 'የአካባቢው ኅብረተሰብ በሚናገረው ቋንቋ እያስተማርን እንቆይ' ነው የተባለው እንጂ ከሕገ መንግሥት የሚቃረን ነገር የለውም" ሲሉም አቋማቸውን አብራርተዋል።






![ባለፉት ዓመታት በ12ኛ ከፍል ብሔራዊ ፈተና በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት ብሩክ ባልካቸው፣ ሰዓዳ ጀማል እና ሃናን ናጂ [ከግራ ወደ ቀኝ]](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/660/cpsprodpb/50d3/live/45d27e20-a061-11f0-b741-177e3e2c2fc7.jpg.webp)








