በአማራ ክልል ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ የግእዝ ቋንቋ ትምህርትን መስጠት ለምን አስፈለገ?

ፈገግ ያሉ ሦስት ታዳጊ ሴት ተማሪዎች ክፍል ውስጥ ደብተራቸው ተከፍቶ እስክሪብቶ ይዞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአማራ ክልል በመጪው የትምህርት ዘመን ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የግእዝ ቋንቋ መሰጠት ሊጀምር ነው።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለሁሉም የዞን እና ከተማ አስተዳዳር ትምህርት መምሪያዎች በጻፈው ደብዳቤ ትምህርቱን ለመስጠት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግ አሳስቧል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ የትምህርት ዝግጅት እና ትግበራ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ይገርማል አያሌው ይህንኑ ለቢቢሲ አረጋግጠው፤ በመጪው የትምህርት ዘመን በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የግእዝ ቋንቋ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የግእዝ ቋንቋ ትምህርት በሙሉ ትግበራ ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ መሰጠት የተጀመረው ባለፈው ዓመት [2017 ዓ.ም.] መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በክልሉ 16 ዞኖች እና በ45 ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ የአንደኛ ደረጃ እና በመለስተኛ ትምህርት ቤቶች በመደበኛነት ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል።

ነገር ግን በመምህራን እጥረት ምክንያት በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ማዳረስ ሳይቻል ቀርቷል ብለዋል።

ትምህርቱ ባለፈው ዓመት በሙሉ ትግበራ ደረጃ ሲሰጥ የቆየው ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ በሙከራ ደረጃ ሲሰጥ ከቆየ በኋላ ነው።

"ያን ጊዜ የጀመሩት ተማሪዎች በዚህ ዓመት ስድስተኛ ክፍል ደርሰዋል። ሙከራ እየተደረገ እና በተማሪዎቹ ላይ ግምገማ እየተካሄደ ሥርዓተ ትምህርቱ እየዳበረ እና እየተዘጋጀ ነው የመጣው" ብለዋል ዳይሬክተሩ።

በመሆኑም ከሙከራ ፕሮግራሙ እና ባለፈው ዓመት ከተጀመረው መደበኛ የትግበራ ግምገማ በመነሳት በመጪው ዓመት በስፋት እንዲሰጥ መታቀዱን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በትምህርት ፖሊሲ መሠረት ተማሪዎች ተጨማሪ ቋንቋ ወይም ሁለተኛ ቋንቋ እንዲማሩ የሚፈቀደው ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ በመሆኑ ትምህርቱ ከዚህ የክፍል ደረጃ መሰጠት እንዲጀምር መደረጉንም አመልክተዋል።

ግእዝ ቋንቋ በዓለማችን ረጅም ዕድሜ ካስቆጠሩ ጥንታዊ ቋንቋዎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ለሚነገሩ በርካታ ቋንቋዎች መሠረት እንደሆነ ይነገራል።

በግእዝ ቋንቋ ከጥንታዊው ዘመን አንስቶ በተለያዩ የዕውቀት ዘርፎች የተዘጋጁ ጽሁፎች እና እውቀቶች ያሉ ሲሆን፣ በበርካታ የዓለማችን ዩኒቨረስቲዎች እና የምርምር ተቋማት ውስጥ ይገኛሉ።

ከጊዜ ወደ ጊዜ የቋንቋው ተናጋሪዎች ቁጥር እየቀነሰ በመምጣቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስተ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ውስጥ ብቻ የተገደበ ሆኗል።

በመሆኑም ይህንን ጥንታዊ ቋንቋ ለትውልድ ለማስተላለፍ እንዲሁም ጥንታዊ መጽሐፍን እና መዛግብትን ለመረዳት ይደረጉ የነበሩ ጥረቶች በአሁኑ ወቅት እየቀነሱ መጥተዋል።

በዚህም ምክንያት አልፎ አልፎም ቢሆን የግእዝ ቋንቋ በትምህርት ቤት ደረጃ እንዲሰጥ ምሁራን እንዲሁም ሃይማኖት አባቶች ጥያቄዎች ሲያነሱ ቆይተዋል።

አቶ ይገርማል እንደሚሉትም የግእዝ ቋንቋ ቤተሰብ የሆነው የአማርኛ ቋንቋ በሚነገርበት የአማራ ክልል ኅብረሰብም ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቷል።

ይህንንም ተከትሎ የሥርዓተ ትምህርት ጥናት ከተደረገ በኋላ በ2015 ዓ.ም. የግእዝ ቋንቋ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት በሙከራ ደረጃ እንዲሰጥ መወሰኑን አስታውሰዋል።

"ሕብረሰተሰቡ በተደጋጋሚ በነባሩ ትምህርት እና ሥልጠና ላይ ሲያነሳቸው ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል አንዱ አገር በቀል እውቀት ነበር" የሚሉት አቶ ይገርማል፤ ቀደምት ሰነዶችን ለመረዳት እና ዕውቀትን ለትውልድ ለማሸጋገር የግእዝ ቋንቋ ቁልፍ መሆኑ ስለታመነበት ወደዚህ እርምጃ መገባቱን ገልጸዋል።

ከሕብረሰተሰቡ ጥያቄ በተጨማሪም በሥርዓተ ትምህርት ባለሙያዎች በተደረገ ጥናት እና የፍላጎት ዳሰሳ ተካሂዶ ቋንቋው ለተማሪዎች እንዲሰጥ መወሰኑን አስታውቀዋል።

በመሆኑም በመጪው የትምህርት ዘመን በተሻለ ዝግጅት እና በሰፊው ከሦስተኛ ክፍል እንዲጀመር ታቅዷል። ለዚህም በቂ እና ብቁ መምህራንን ለመመደብ እና መጽሐፍትን ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን አቶ ይገርማል ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በነበሩት ፕሮግራሞች በቋንቋ የተመረቁ እና ነባር የግእዝ እውቀት ያላቸውን መምህራን የሥርዓተ ትምህርት ሥልጠና ከተሰጣቸው በኋላ እንዲያስተምሩ መመደባቸውን በመጥቀስም፤ የመምህራን እጥረት እንዳይኖር በመጪው የትምህርት ዘመን የግእዝ ትምህርት በኮሌጆች ደረጃ እንዲሰጥ የቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።

"አሁን እየተጠቀምነው ያለነው ነባር የግእዝ እውቀት ያላቸው እና ሌሎች ተቋማት ከዚህ በፊት ያስመረቋቸውን የግእዝ መምህራንን ነው። የመምህራን ሥልጠና እና ስምሪት አሁንም በጥናት እና በዕቅድ መመለስ ያለበት ነው። በዚህ ላይ እየተሠራ ነው" ሲሉም አክለዋል።

የማስተማሪያ እና መማሪያ መጽሐፍትን በተመለከተም ሥርዓተ ትምህርቱ እስከ 6ኛ ክፍል ተሰናድቶ ለሕትመት መዘጋጀቱንም ጨምረው ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም መምህራን 'በሶፍት ኮፒ' ተሰጥቶ እርሱን እያባዙ ሲያስተምሩ መቆየታቸውንም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

ዳይሬክተሩ ጨምረውም የግእዝ ቋንቋ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት የሚሰጥ ቢሆንም፣ በስምንተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ውስጥ ለጊዜው እንደማይካተት አስረድተዋል።

"በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ተማሪዎች ትምህርቱን መቅሰማቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነው በሚኒስትሪ ፈተና ይካተት አይካተት የሚለውን መወሰን የሚቻለው።"

በአማራ ክልል ከዘጠኝ ሺህ በላይ አንደኛ እና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።