በረሃብ የተጠቁ ሰዎች በሚገኙባቸው የሱዳን ካምፖች ላይ በተነሰዘረ ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገደሉ

በሱዳን ምዕራብ ዳርፉር ክልል ካለፈው ሳምንት መገባደጃ ጀምሮ በተከታታይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ከ100 በላይ ንፁኃን ዜጎች ተገደሉ።

ከሟቾቹ መካከል 20 ያህል የሚሆኑት ሕጻናት እና የሕክምና ባለሙያዎች መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

ጥቃቱ በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተሰደዱ ሰዎችን በምታስተናግደው በኤል ፋሸር ከተማ እና በአቅራቢያው ባሉ ሁለት መጠለያ ካምፖች ላይ የተፈጸመ ሲሆን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉም (አርኤስኤፍ) ተጠያቂ ሆኗል።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በበኩሉ ውንጀላዎቹን የተቀነባበሩ ናቸው ሲል ውድቅ አድርጓል።

ዘምዘም እና አቡ ሹክ የተባሉት ካምፖች ከ700 ሺህ በላይ የሚሆኑ ስደተኞችን ያስተናግዳሉ።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ረሃብ ተጋርጦባቸዋል።

የጥቃቶቹ ዜና የተሰማው በአርኤስኤፍ እና በአገሪቱ ሠራዊቱ መካከል የተጀመረው የእርስ በርስ ጦርነት ሁለተኛ ዓመቱ በተቃረበበት ዋዜማ ላይ ነው።

በሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ክሌመንት ንክዌታ ሳላሚ በተፈጠረው ነገር "በጣም መደናገጣቸው" ተናግረዋል።

"ይህ በተፈናቀሉ ሰዎች እና በእርዳታ ሰጭ ሠራተኞች ላይ የደረሰ ተከታታይ እና አሰቃቂ ጥቃት ተቀባይነት የሌለው ነው" ብለዋል በመግለጫቸው።

የእርዳታ ድርጅቱ ሪሊፍ ኢንተርናሽናል በዘምዘም በደረሰው ጥቃት ዶክተሮች፣ አሽከርካሪዎች እና የቡድን መሪን ጨምሮ ዘጠኝ ሠራተኞቹ መገደላቸውን አስታውቋል።

በካምፑ ውስጥ የመጨረሻው የጤና አገልግሎት አቅራቢ መሆኑን የገለጸው የበጎ አድራጎት ድርጅቱ የአርኤስኤፍ ተዋጊዎች ተጠያቂ ናቸው ብሏል።

ሪሊፍ ኢንተርናሽናል "ይህ በክልሉ ውስጥ ባሉ ሁሉም የጤና መሠረተ ልማት አውታሮች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መሆኑን ተረድተናል። ይህም የተፈናቀሉ ዜጎችን የጤና አገልግሎት እንዳያገኙ ለማድርግ ያለመ ነው" ብሏል።

አክሎም "ከእኛ ክሊኒኮች አንዱ የዚህ ጥቃት አካል መሆኑ አስደንጋጭ ሲሆን በኤል-ፋሸር የሚገኙ የጤና ተቋማትም ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል።"

አርኤስኤፍ ቅዳሜ ዕለት በሰጠው መግለጫ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ተጠያቂ እንዳልሆነ እና በዘምዘም የተገደሉ ሰዎች የወታደራዊ ኃይሉን ስም ለማጠልሸት የተደረጉ ናቸው ብሏል።

እሑድ ጧት ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረገ እና በካምፑ ውስጥ ላሉ ሰዎች ምግብ በማዘጋጀት የሚሠራ የዘምዘም ነዋሪ ሁኔታው ​​​​እጅግ በጣም አስከፊ ነው ብሏል።

የ34 ዓመቱ ሙስጠፋ በዋትስአፕ በላከው የድምጽ መልዕክት "ብዙ ወጣቶችን አጥተናል፤ በማኅበረሰብ መመገብያ ውስጥ ይሠሩ የነበሩም ተገድለዋል። ሆስፒታሉን ለመክፈት ሲሯሯጡ የነበሩ ሐኪሞችም ተገድለዋል" ብሏል።

"አጎቴ እና የአጎቴ ልጅ ተገድለዋል።ሰዎች ቆስለዋል፣ እናም እነሱን ለማዳን መድሃኒት ወይም ሆስፒታል ባለመኖሩ በደም መፍሰስ ምክንያት እየሞቱ ነው።"

"ጥቃቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው።ጠዋትም ተጨማሪ ጥቃቶች እንደሚኖሩ እየጠበቅን ነው።"

ወደካምፑ የሚያመሩ መንገዶች በሙሉ ተዘግተው "ከአራቱም አቅጣጫ የተከበበ ነው" ሲል አክሏል።

የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ዋሲር በበኩላቸው ነገሮች "እጅግ በጣም አስከፊ ናቸው" ብለዋል።

በዘምዘም ምንም የቀረ ነገር የለም። ብዙ ሰላማዊ ዜጎች ተሰድደዋል። አሁንም ለመልቀቅ እየሞከርን ቢሆንም ግን ሁሉም መንገዶች ተዘግተውብናል፤ ልጆችም ይዘናል።"

"ግድያ በየቦታው አለ። አሁን ሳናግራችሁ እንኳን ከምሽግ ውስጥ ጥይት እየተተኮሰ ነው።"

በሠራዊቱ እና በአርኤስኤፍ መካከል ያለው የሥልጣን ሽኩቻ የወለደው ጦርነት በዓለም ላይ ትልቁን የሰብአዊ ቀውስ ፈጠሯል።

ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከመኖርኣ ቤታቸው እንዲፈናቀሉ እና ማኅበረሰቦችን ለረሃብ እንዲጋለጡ አድርጓል።

ጦርነቱ የጀመረው የሱዳን ሠራዊት እና የአርኤስኤፍ መሪዎች በአገሪቱ የወደፊት ፖለቲካዊ እጣ ፈንታ ላይ ባለመግባባታቸው ነው።

ኤል-ፋሸር በዳርፉር ውስጥ በጦር ኃይሎች ቁጥጥር ስር ያለች የመጨረሻዋ ትልቅ ከተማ ስትሆን በአርኤስኤፍ ለአንድ ዓመት ያህል ከበባ ውስጥ ቆይታለች።