ሞት እንኳን ሊቋጨው ያልቻለው የሁለቱ ፕሬዚዳንቶች የከረረ ጠብ

የአሁኑ የዛምቢያ ፕሬዚዳንት ሃኪንዴ ሂቼሌማ እና በቅርቡ ያረፉት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ

የፎቶው ባለመብት, EPA / AFP

የምስሉ መግለጫ, የአሁኑ የዛምቢያ ፕሬዚዳንት ሃኪንዴ ሂቼሌማ እና በቅርቡ ያረፉት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ

ከሳምንታት በፊት ያረፉት የዛምቢያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው የት ይፈጸም የሚለው አወዛጋቢ ሆኗል።

ከአሁኑ ፕሬዚዳንት ሃኪንዴ ሂቼሌማ ጋር የከረረ ጸብ የነበራቸው የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሉንጉ "ቀብሬ ላይ እንዳይገኝ ብለው ተናዘው ነው" የሞቱት።

የሁለቱ ፕሬዚዳንቶች ጸብ ሞት እንኳን ሊቋጨው አልቻለም በሚል መነጋገሪያ መሆኑ አልቀረም።

ሉንጉ ከመሞታቸው በፊት "አስከሬኔ አጠገብ" ፕሬዚዳንት ሂቼሌማ "ዝር እንዳይሉ" ያሏቸው ቤተሰቦቻቸውም ያንኑ የመጨረሻ ቃላቸውን እናከብራለን አሉ።

የአገር መሪዎች ሲያልፉ የሚደረግላቸው ክብሩን በጠበቀ ሥርዓት ለመቅበር የአሁኑ መንግሥት ያሰበው ዕቅድም ሳንካ ሆኖበታል።

በአገሪቱ ውስጥ ይህን ያህል አሳዛኝ መቃቃር እንዴት ሊፈጠር ቻለ? የሚል ጥያቄም ዛምቢያውያን እንዲያነሱ አድረጓል።

ዛምቢያን ከአውሮፓውያኑ 2015 ጀምሮ ለስድስት ዓመት ያስተዳደሩት የ68 ዓመቱ የኤድጋር ሉንጉ ብሔራዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት መፈጸም የነበረበት ባለፈው እሁድ የነበረ ቢሆንም በተነሳው ውዝግብ ተሰረዘ።

ሆኖም ከዚያ በፊት የቀብራቸው ሁኔታ አወዛጋቢ ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ የታዩ ፍንጮች ነበሩ።

ሉንጉ ማለፋቸውን ግንቦት 28/2017 ዓ.ም. ልጃቸው ታሲላ ሉንጉ በገለጸችበት ወቅት አባቷ በደቡብ አፍሪካ በሚገኝ ሆስፒታል "ክብራቸው ተጠበቆ" ሲታከሙ ከቆዩ በኋላ መሞታቸውን እንባዋን እየታገለች በፌስቡክ ላይ ተናገረች።

አንድ ደቂቃ በፈጀ ንግግሯም "በዚህ የሐዘን ወቅት ፕሬዚዳንት ሉንጉ አገራቸውን ባገለገሉበት ወቅት ዘመን የማይሽረው መገለጫቸው የ'አንድ ዛምቢያ፣ አንድ አገር' መንፈስ እንዲሰፍን እንጠይቃለን" አለች።

የአንድ አገር መሪ ሳይሆን ሐዘን ሰዎችን የማሰባሰቢያ ባህላዊ ሁነት ከመሆኑ አንጻር ልጃቸው የአንድነትን አስፋላጊነት ማጉላቷ አንድ ችግር እንዳለ ማሳያ ነበር።

ሞታቸው አስቀድሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲነገር የነበረ ሲሆን፣ የልጃቸው የፌስቡክ ፖስት ሁኔታውን አረጋገጠ። ከዚያም የኬንያን ፕሬዚዳንት ጨምሮ የሐዘን መግለጫዎች ይወጡ ጀመር። ሆኖም ፕሬዚዳንት ሃኪንዴ ሂቼሌማ ዝምታን መረጡ።

የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የቀድሞውን መሪ ሞት ሲዘግቡ የዛምቢያ ብሔራዊ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ስለ ህልፈታቸው ምንም ዓይነት ዘገባ ሳይሰራ ቀረ።

ልጃቸው ሞታቸውን ከተናገረች ከሦስት ሰዓታት በኋላ የዛምቢያ ፕሬዚዳንት ዝምታቸውን ሰብረው "የዛምቢያዊነታችን መገለጫ የሆኑት የሰላም፣ የክብር እና የአንድነት እሴቶችን እንጠብቅ" ሲሉ በጋራ የእንቁም ጥሪ አቀረቡ።

 የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ ባለቤት

የፎቶው ባለመብት, PF

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ ባለቤት
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዛምቢያ የማስታወቂያ ሚኒስትር ኮርኔሊየስ ምዌትዋ የፕሬዚዳንቱ የሐዘን መግለጫ መዘግየትን አጣጥለው ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ህልፈተ ሕይወታቸውን ማወጅ የፕሬዚዳንቱ ሚና አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

ሃኪንዴ ሂቼሌማ የፕሬዚዳንቱን መንበር የተቆጣጠሩት በስድስተኛ የምርጫ ሙከራቸው በአውሮፓውያኑ 2021 በተደረገ ምርጫ ሉንጉን አሸንፈው ነው።

ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች በሦስት አገራዊ ምርጫዎች ተፎካክረዋል።

ሆኖም በሁለቱ መሪዎች መካከል የሰፈነው ጥላቻ ከፉክክርም ያለፈ ነው።

ለዚህ ሁሉ ቁልፉ ነገር የአሁኑ ፕሬዚዳንት በአውሮፓውያኑ 2017 ከ100 ቀናት በላይ በእስር ማሳለፋቸው ነው።

በወቅቱ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የነበሩት ሂቼሌማ በአገር ክህደት ወንጀል ተከሰው ከሦስት ወራት በላይ ፍርድ ሲጠባበቁ ነበር።

የዚያ ወቅት ተቃዋሚ የተከሰሱትም አጃቢዎቻቸው የነበሩ ሞተር ሳይክሎች ለፕሬዚዳንት ሉንጉ ቅድሚያ ባለመስጠት የፕሬዚዳንቱን "ሕይወት አደጋ ላይ ጥለዋል" በሚል ነው።

ክሳቸው የተቋረጠው የኮመንዌልዝ ዋና ፀሐፊ ጣልቃ መግባታቸውን ተከትሎ ነው።

ሂቺሌማ በወቅቱ "ያለ መብራት፣ ውሃ፣ መጸዳጃ ቤት" በአሰቃቂ እና ኢሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ ብቻቸውን ታስረው እንደነበር ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ሉንጉንም ለዚህ ተጠያቂ አደርገው ነበር።

ይህ የሂቼሌማ እስር የመጀመሪያቸው አልነበረም ተቃዋሚው 17 ጊዜ ያህል ታስረዋል።

የፓርቲያቸው 'ዩናይትድ ፓርቲ ፎር ናሺናል ዴቨሎፕመንት' አባላት በገዥው ፓርቲ ደጋፊዎች ወከባ ደርሶባቸዋል።

ሂቺሌማ በአውሮፓውያኑ 2021 ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ የተደጋጋሚ እስራቸው መቋጫ ሆነ።

በሙስና ክሶች እንዲሁም ፀረ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚወነጀሉት ሉንጉ፣ በምርጫ ከተሸነፉ በኋላ ከፖለቲካ ጡረታ ወጥቻለሁ አሉ።

ፕሬዚዳንት ሃኪንዴ ሂቼሌማ በአውሮፓውያኑ 2017 ከእስር ቤት ሲወጡ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዚዳንት ሃኪንዴ ሂቼሌማ በአውሮፓውያኑ 2017 ከእስር ቤት ሲወጡ

ሆኖም በፕሬዚዳንት ሂቺሌማ የአስተዳደር ዘመን ያለው የኑሮ ውድነት እና ምጣኔ ኃብት ፈተና በር የከፈተላቸው የቀድሞው ፕሬዚዳንት ወደ ፖለቲካ እንደሚመለሱ ከሁለት ዓመት በፊት አስታወቁ።

ሉንጉ ይህንን ማሳወቃቸውን ተከትሎ ብዙም ሳይቆይ የጡረታ ጥቅማ ጥቅሞቻቸው እና ልዩ መብቶቻቸው በመንግሥት እንዲነፈጉ ተደረገ።

ከዚህም በተጨማሪም የቀድሞው ፕሬዚዳንት በፖሊስ መዋከብ እየደረሰባቸው እንደሆነ ቅሬታ አቅርበዋል።

በአንድ ወቅትም "በቁም እስር ላይ" እንደሆኑም ገልጸው ነበር።

ከሁለት ዓመታት በፊት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ከአደባባይ ሩጫ እንዲታቀቡ ፖሊስ "ፖለቲካዊ ዘመቻ" በሚል አካላዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ታግደው ነበር።

በተጨማሪም በውጭ አገር ጉባኤ እንዳይሳተፉ እንዲሁም ለሕክምና ከአገር እንዳይወጡ መከልከላቸውን ከዚህ ቀደም ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

የማስታወቂያ ሚኒስትሩ በበኩላቸው የሉንጉ እንቅስቃሴ ታግዶ ነበር የሚባለውን ውድቅ አድርገዋል።

ሚኒስትሩ ምዌትዋ ፕሬዚዳንት ሂቺሌማ ተቃዋሚ በነበሩበት ወቅት አያያዛቸው አግባብ ያልነበረው ቢሆንም እሳቸው ግን በሉንጉ ላይ ተመሳሳይ ነገር አልፈጽምም በሚል ቁርጥ ውሳኔ ነበራቸው ይላሉ።

ሚኒስትሩ ይህንን ቢሉ የፕሬዚዳንቱ የፀረ ሙስና ዘመቻ ከቀድሞው ገዢ ፓርቲ ጋር ቅርበት የነበራቸውን እና የሉንጉ ቤተሰብ ላይ አነጣጥሯል ተብሎ ይወቀሳል።

የሉንጉ ባለቤት ክስ ተመስርቶባቸው ንብረታቸውን አጥተዋል። እንዲሁም ታሲላን ጨምሮ የሉንጉ ልጆችም ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ገጥሟቸዋል ተብሏል።

ሁሉም ምንም ዓይነት ጥፋት አላጠፋንም ይላሉ።

ከዚያም በዘንድሮው ዓመት የአገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ሉንጉ ሕጉ የሚፈቅድላቸውን ሁለት የሥልጣን ዘመን ስላገለገሉ ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር አይችሉም ሲል ከልክሏቸዋል።

 ህይወታቸው በቅርቡ ያለፈው የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ

የፎቶው ባለመብት, Andy Luki Jr

የምስሉ መግለጫ, ህይወታቸው በቅርቡ ያለፈው የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ

የቀድሞው የአገሪቱ መሪ በዚህ ሁሉ ከፍተኛ ቁጣ እንዳደረባቸው ተነግሯል።

"በሁለቱ ሰዎች [መሪዎች] መካከል ምንም ዓይነት ፍቅር አልነበረም። ሉንጉ በሕይወት እያለሁ ምንም ያልመሰልኳቸው በሞትኩ ጊዜ እንዲያስመስሉ አልፈልግም የሚል አመለካከት ነበራቸው" ሲሉ የቤተሰቡ ጠበቃ ማኬቢ ዙሉ ገልጸዋል።

ሉንጉ በመጨረሻም ለሕክምና ጥር ወር ላይ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀኑ ሲሆን፤ ዶክተሮቹ በርካታ ምርመራ ካደረጉላቸው በኋላ ቀደም ብለው ቢመጡ ኖሮ ሕክምናቸው የበለጠ የመሳካት ዕድል ይኖረዋል ተብለው እንደተነገራቸው ጠበቃቸው ያስረዳሉ።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ህመማቸው ምን እንደሆነ አልተገለጸም።

ሉንጉ "ፕሬዚዳንቱ ቀብሬ ላይ እንዲገኝ አልፈልግም" ያሉት በከፊል ጉዟቸው ታግዶ ሕክምናቸው በመከልከሉ እንደሆነ ይነገራል።

ሉንጉ በደቡብ አፍሪካ ሕክምና እንዳያደርጉ ጉዟቸው ተከልክሏል የሚለውን መንግሥት ውድቅ አድርጓል።

የሉንጉን ሞት ተከትሎ ቤተሰቡ የቀብር ሥነ ሥርዓቱን የመምራት ፍላጎት ቢኖራቸውም የዛምቢያ ባለሥልጣናት ይህንን የመቆጣጠር ፍላጎት አላቸው።

ምነም እንኳን መጥፎ ስሜት ቢሰፍንም መግባባት ላይ ተደርሶ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ብሔራዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት ለማዘጋጀት ዕቅድ ተይዞ ነበር።

ነገር ግን መንግሥት ያቀደው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የፕሬዚዳንቱ ተሳትፎ የላቀ መሆኑን የሚያሳይ ፕሮግራም መውጣቱን ተከትሎ የሉንጉ ቤተሰብ አልቀበልም አለ።

በዚህም የተነሳ በዛምቢያ የተያዘው የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዲሰረዝ እንዲሁም ብሔራዊ የሐዘን ጊዜውም ለአጭር ጊዜ ሆነ።

የሉንጉ የቀብር ሥነ ሥርዓት በደቡብ አፍሪካ ሊፈጸም ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ሂቺሌማም የሚታደሙ አይመስልም። ዛምቢያውያንም የቀድሞ ፕሬዚዳንታቸውን አይቀብሩም።

በዚሁ መሠረት ቀብሩ በደቡብ አፍሪካ ሊካሄድ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ከተካሄደ በኋላ የዛምቢያ መንግሥት ለደቡብ አፍሪካ ፍርድ ቤት ባቀረበው አቤቱታ ምክንያት የሉንጉ ቀብር ተሰርዟል።

መንግሥታዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት ማካሄድ የፈለገው የዛምቢያ መንግሥት በመጪው አርብ የውሳኔ ሃሳብ ለፕሪቶሪያ ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ ከሳምንት በኋላ ደግሞ የሟቹ ፕሬዚዳንት ቤተሰቦች ምላሽ እንሚሰጡ ይጠበቃል። በዚህም ቀብሩ እስከ ነሐሴ መጀመሪያ ድረስ ሊዘገይ ይችላል ተብሏል።

የሟች ፕሬዚዳንት ቤተሰቦች በጸሎት ሥነ ሥርዓቱ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Nomsa Maseko / BBC

የምስሉ መግለጫ, ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን የጸሎት ሥነ ሥርዓት ከተካሄደ በኋላ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቀብር እንዳይፈጸም በፍርድ ቤት ታግዷል