ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ግድግዳ ላይ በፕላስተር የተጣበቀው ሙዝ 6.2 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ
ማውሪዚዮ ካቴላን የተባለው ጣሊያናዊ የጥበብ ሰው በፕላስተር ከግድግዳ ያጣበቀው ሙዝ ኒው ዮርክ ውስጥ በተካሄደ ጨረታ በ6.2 ሚሊዮን ዶላር ተሽጧል።
ይህ ዋጋ ግድግዳ ላይ ለተጣበቀው ሙዝ መጀመሪያ ከተሰጠው ግምት በአራት እጥፍ ከፍ የሚል ነው።
አጫራቹ ድርጅት ይፋ እንዳደረገው በክሪፕቶከረንሲ ንግድ የበለፀገው ቻይናዊ ጀስቲን ሱን የተባለ ግለሰብ ሌሎች ተጫራቾችን አሸንፎ “ኮሜዲያን” የተባለውን የጥበብ ሥራ ረቡዕ ዕለት ሸምቶታል።
ጨረታውን ያሸነፈው ሱን “በሚቀጥሉት ቀናት እኔው ራሴው ሙዙን በመብላት የዚህ ልዩ የጥበብ ማዕድ ተቋዳሽ እሆናለሁ” ማለቱ ተሰምቷል።
በፕላስተር የተጣበቀው ሙዝ እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ የተሸጠ ፍራፍሬ ሆኗል።
ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው በጨረታው የተሸጠው ሙዝ ከጨረታው ቀን በፊት በ0.35 ዶላር ከገበያ የተገዛ ነው።
“ኮሜዲያን” የተባለው የጥበበ ሥራ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ ያለው በአውሮፓውያኑ 2019 ነበር። በወቅቱ ግድግዳ ላይ የተጣበቀው ሙዝ መነጋገሪያ ከመሆን አልፎ ጥበብ ምንድናት የሚል የበይነ መረብ ክርክር አስነስቶ እንደነበር አይዘነጋም።
ከግድግዳ የተጣበቀው ሙዝ በመላው ዓለም ተዘዋውሮ ለዕይታ ቀርቧል። የተጣበቀው ሙዝ መበስበስ ሲጀምር እንዴት መቀየር እንዳለበት የሚያትት መመሪያም አብሮት ይዞራል።
በፕላስተር የተጣበቀው ሙዝ ከአንድም ሁለት ጊዜ ተበልቷል።
በ2023 ይህ ሙዝ በሴኡል የጥበብ ሙዚየም ተሰቅሎ ሳለ ደቡብ ኮሪያዊው የጥበብ ተማሪ ከግድግዳ አውርዶ እንደበላው ይታወሳል።
ሙዚየሙ በተባለው ፈንታ ሌላ ሙዝ ገዝቶ መቀየሩን የኮሪያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ከአራት ዓመታት በኋላ ግድግዳ ላይ በፕላስተር የተጣበቀው ሙዝ በአሜሪካዋ የባህር ዳርቻ ከተማ ማያሚ በ120 ሺህ ዶላር ተሽጧል። ይህ ከሆነ በኋላ አንድ የጥበብ ሰው ነኝ የሚል ግለሰብ ሙዙን ከግድግዳው ላይ ማንሳቱ ቁጣ ቀስቅሶ ነበር።
ነገር ግን ሙዙ በጥንቃቄ ቦታው ላይ እንዲተካ ተደርጓል።
6.2 ሚሊዮን ዶላር አውጥቶ በፕላስተር ከግድግዳ የተጣበቀውን ሙዝ የገዛው የክሪፕቶከረንሲ ቱጃር የዲጂታል ከረንሲ ማጭበርበር ፈፅሟልተ የሚል ክስ ባለፈው ዓመት በአሜሪካ መንግሥት ቀርቦበታል። ግለሰቡ የሚቀርቡበትን ክሶች ያስተባብላል።