ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስለሽግግር ወቅት ፍትህ የምናውቃቸው አምስት ነጥቦች
ከግጭቶች በኋላ ሠላማዊ ሁኔታዎች መፈጠር ሲጀምሩ ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ እንደ ዘላቂ የግጭት ማቆሚያ መንገድ የሚወሰደው ያጋጠሙ የመብት ጥሰቶች እና ወንጀሎች በምን መልኩ ምላሽ ይሰጣቸው የሚለው ነው።
በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተካሄደውን ጦርነት በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ሁለቱ ወገኖች ፕሪቶሪያ ላይ ከስምምነት ደርሰዋል። በግጭቱ ወቅት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሽግግር ወቅት ፍትህ እልባት እንደሚያገኙም ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተካሄደው ጦርነት ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲበጅለት ሲጠይቅ መቆየቱ የሚገልጹት ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፣ የሽግግር ጊዜ ፍትህ አስተዳደር ማቋቋም ሌላኛው ያቀረቡት ምክረ ሀሳብ እንደነበር ያስረዳሉ።
“የተፈጸሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በሚመለከት የተሟላ ምርመራ እና ተጠያቂነት ለማረጋገጥ እንዲቻል የሽግግር ወቅት ፍትህ እንዲቋቋም ምክረ ሀሳብ አቅርበን ነበረ።
“አሁን ባለንበት ሁኔታ እንደሚታወቀው የሰላም ስምምነቱ ተፈርሞ ተግባራዊ መሆን መጀመሩ እንዲሁም የሰላም ስምምነቱ ውስጥ የሽግግር ወቅት ፍትህ አስተዳደር እንዲቋቋም ስምምነት የተደረገ መሆኑ በጣም ጥሩ እና ትክክለኛ እርምጃዎች ናቸው” ይላሉ።
የሽግግር ወቅት ፍትህ ምንነት
የሽግግር ወቅት ፍትህ አስከፊ ግጭት፣ ጭቆና እና የመብት ጥሰትን ተከትሎ ተጠያቂነት፣ ፍትህ እና እርቅ በማረጋገጥ ዘላቂ ሠላም የሚፍጥሩ ሥራዎችን የሚያጠቃልል ሂደት መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ይገልጻል።
አንዳንድ ሰዎች ተጠያቂነት የሚስያገኘው ፍትህ የተሻለ ሠላም ያመጣል ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ የሽግግር ወቅት ፍትህን እንደ አማራጭ ያቀርባሉ።
አቶ ያሬድ ኃይለማርያም የሕግ ባለሙያ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ናቸው። እንደ አቶ ያሬድ ከሆነ የሽግግር ወቅት ፍትህ ሂደት ነው።
“በአንድ አገር በግጭትም ሆነ በሌላ አጋጣሚ አስከፊ የሆነ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸም ከነበረ [ለአጭርም ሆነ ለረዥም ጊዜ] ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ወደ ሚገነባበት ሠላማዊ ሁኔታ ለመሸጋገር የሚደረግ ሂደት ነው” ይላሉ።
የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ይኖራሉ። የሕግ እና የመብት ጥሰት የፈጸሙም ስለሚኖሩ “የተበደሉ ሰዎች ከዚህ አስቸጋሪ ወቅት የሚያልፉበት መንገድ ነው።”
ለሽግግር ወቅት ፍትህ መሠረት የሆኑ ጉዳዮችም መኖራቸውን ያነሳሉ አቶ ያሬድ ያነሳሉ፣ መጀመሪያ ላይ የሚቀመጠው ደግሞ “ፍትህ እና ተጠያቂነትን ማስፈን ነው።”
እርቅ ማውረድ ቀጥሎ ይመጣል። የተፈጸሙ ጥሰቶች በአግባቡ ተሰንደው በመልክ በመልክ እንዲታወቁም ይደረጋል።
“የተበደሉ አካላት በዋናነት አንድም ለጉዳታቸው ተመጣጣኝ ካሳ የሚያገኙበት፣ ሁለትም በአጥፊዎች ይቅርታ እንዲጠየቁ የሚደረግበት ሂደት” መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ።
የሽግግር ወቅት ፍትህ ዓላማዎች እና ዓይነቶች
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የሽግግር ወቅት ፍትህ አራት ዓላማዎች እንዳሉት ያብራራሉ።
“እውነትን መፈለግ እና ማወቅ ቀዳሚው ነው። ሁለተኛው የተጎዱት ሰዎችን መልሶ ማቋቋም ሲሆን፣ ሦስተኛው የወንጀል ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ነው።”
የመጨረሻው ዓላማ ደግሞ ተመሳሳይ ነገር ዳግም እንዳይከሰት ምን አይነት ለውጥ እና ማሻሻያ ያስፈልጋል? የሚለውን መመርመር እና ተግባራዊ ማድረግ ነው።
“ይህም የሕግ ማሻሻያ ወይም የፖሊሲ ለውጥ ሊሆን ይችላል፤ ለችግሩ ምክንያት የሆነውን ማወቅ እና ዘለቄታዊ መፍትሄ መፈለግ ነው” በዚሁ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው ይላሉ።
ሁለት ዓይነት የሽግግር ወቅት ፍትህ መኖሩን የሚጠቅሱት አቶ ያሬድ “አንዳንድ አገሮች የሽግግር ጊዜ ሂደቱን የወንጀል ክስ ላይ የሚያተኩር ሊያደርጉት ይችላሉ። አጥፊዎች በወንጀል ብቻ እንዲጠየቁ አድርገው፣ ይቅርታ አውርደው የሚሄዱበት የሽግግር ጊዜ ፍትህ ሂደት አለ” ይላሉ።
ሁለተኛው ደግሞ በአንዳንድ አገራት የተሞከረ ነው። ይኼኛው ምንም ዓይነት ክስ ሳይመሠረት ጥፋቱ እንዲታወቅ፤ አጥፊዎች ይቅርታ እንዲጠይቁ እና ተበዳዮችም ይቅርታውን ተቀብለው እንዲሄዱ የሚደረግበት ነው።
በተለይ ሁለተኛው የሚከሰተው ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ራሳቸውም በወንጀሉ ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ ውስጥ ያሉ ከሆኑ ነው።
ይህ አይነቱ ሂደት አጥፊዎቹ በወንጀል የማይጠየቁበት፤ ነገሮች ተደባብሰው የሚያልፉበት እና ወንጀል ፈጻሚዎች ከተጠያቂነት እንዲያመልጡ ሽፋን የመስጠት ዕድል አለው።
እንደ አቶ ያሬድ ከሆነ “አደባባይ ላይ ወጥተው ይቅርታ ምናምን ይሉና ተጠያቂነት ሳይኖር አጥቂዎች እንዲያመልጡ ይደረጋል።”
የሽግግር ወቅት ፍትህ ባይሆንም አቶ ያሬድ በምሳሌነት አንድ አጋጣሚን ያነሳሉ።
“ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ሲመጡ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር ሽብርተኞቹ እኛ ነን፤ ሰቆቃ (ቶርቸር) ፈጽመናል፣ ዜጎችን አሰቃይተናል . . . ይቅርታ አድርጉልን ብለው ነበር። ተጠያቂ የሆነ አካል [ግን] የለም” ሲሉ ያስታውሳሉ።
የሽግግር ወቅት ፍትህ የረዥም ጊዜ ሂደት ነው።
በተለይ ደግሞ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ሰፊ ከሆኑ፤ ብዙ ማኅበረሰቦች ከተጎዱ እና ብዙ ታሪካዊ ዳራ ካለው ወደ ኋላ በመሄድ የሚጣራም ይሆናል።
የት ጋር እንጀመር? የእነማን ጉዳይ ይታይ? እና በምን ጉዳይ ላይ የተፈጸሙ ጉዳዮች ይታዩ? የሚለው በጣም የረዥም ጊዜ ሊወስድ ይችላል።
“ምናልባትም ዓመታት ሊወስድ ይችላል። ኮሚሽንም ሊያስፈልገው ይችላል። አጣሪ አካላት መዋቀር አለባቸው። በሂደቱ ማዕቀፍ ላይ መስማማትም ያስፈልጋል። አንዳንዴ ሂደቱ ከመርዘሙ የተነሳ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያላቸው አገራት ናቸው ሂደቱን በአግባቡ የሚጨርሱት” ይላሉ አቶ ያሬድ።
የአንዳንድ የሽግግር ወቅት ፍትህ ሂደት መሃል ላይ በሌላ ችግር ሊጠለፍ ወይም እየደበዘዘ ሊሄድ ይሄዳል።
ረዥም ጊዜ መውሰዱ አንዱ የሽግግር ወቅት ፍትህ ሂደት ደካማ ጎን ተደርጎም ይወሰዳል። ከመንዛዛት ባለፈ የተጎዱ እና ፍትህ የሚፈልጉ ተጎጂዎችን ተስፋ ሊያስቆርጥም ይችላል።
ሩዋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቺሊ. . .
የተለያዩ አገራት የሽግግር ወቅት ፍትህን ተግባራዊ አድርገዋል። ሩዋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዩጎዝላቪያ እና ቺሊ ለዚህ ይጠቀሳሉ።
የሩዋንዳው የዘር ፍጅት በሽግግር ወቅት ፍትህ ነው የተቋጨው። ተበዳዮች በደላቸው እንዲታወቅ ተደርጓል፤ አጥፊዎችም ለፍርድ ቀርበዋል። ጉዳዩም ለማስተማሪያነት በሙዚየም ጭምር ተቀመጧል።
ደቡብ አፍሪካም ተመሳሳይ እርምጃ ወስዳለች። ብዙ ጥያቄዎች እና ቅሬታዎች ቢነሱበትም የአፓርታይድ ሥርዓት የተቋጨው በእውነት አፈላላጊ እና የእርቅ (ትሩዝ ኤንድ ሪኮንሲሌሽን) ኮሚሽን ነው።
በዩጎዝላቪያም አጥፊዎች በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የቀረቡበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ለጥፋቶች “ይቅርታ ጠይቀናል ብለው እንደማምለጫ የተጠቀሙባቸው አገራትም አሉ” ይላሉ አቶ ያሬድ ኃይለማርያም።
ቺሊ እና አንዳንድ የላቲን አሜሪካ አገራት ደግሞ ይኼኛውን መንገድ መርጠዋል።
የተጠያቂነት ጉዳይ
የሽግግር ወቅት ፍትህ ሲነሳ አብሮ የሚነሳው ተጠያቂነት ነው።
በርካታ ጊዜ የሽግግር ወቅት ፍትህ ሂደቶች በተጠያቂነት ምክንያት የማይሳኩበት ወይም የሚጨናገፉበት ዕድል አላቸው።
“የተጠያቂነት (አካውንተብሊቲ) ጉዳይ በመንግሥታት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ላይ የሚወሰን ነው” የሚሉት አቶ ያሬድ፤ አንዳንዴ አጥፊዎች እንዳይጠይቁ ‘የፖለቲካ ሽፋን እና ከለላ’ ሊሰጥ ይችላል።
ተጠያቂነት የሚያስከትሉ ጥፋቶችን መለየትም በሂደቱ ውስጥ የሚታይ ጉዳይ በመሆኑ “በትናንሽ ወንጀሎች ሰዎች ላይጠየቁ ይችላሉ” የሚሉት አቶ ያሬድ፣ የትኞቹ ይጠየቁ የሚለውም በሂደቱ ውስጥ የሚመለስ እንደሚሆን ያስረዳሉ።
ቢሆንም እንደ ሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች እና እንደ ማሰቃት (ቶርቸር) ያሉት ድርጊቶች “በእኛም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕግ በይርጋ እንኳን ቢሆን ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርጉ የጥፋት አይነቶች አይደሉም።”
ለዚህ ሁሉ ግን የፖለቲካ ቁርጠኝነት ከአመራሮች እንደሚጠበቅ የመብት እና የሕግ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ያነሳሉ።
“በኢትዮጵያ የመንግሥት ተጠያቂነት በተለይም በሰብዓዊ መብት ጥሰት ዙሪያ አፌን ሞልቼ ከዜሮ በታች ነው ማለት እችላለሁ” የሚሉት የመብት ተሟጋቹ አቶ ያሬድ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል ተብለው ስለሚጠየቁ ባለሥልጣናት ተሰምቶ አይታወቅም ይላሉ።
“ብዙ ጊዜ ባለሥልጣናት የሚጠየቁት ከሙስና እና ከተያያዥ ጉዳዮች ጋር ነው። ስለዚህ የሽግግር ወቅት ፍትህ ትልቁ ፈተና እና ማነቆ የሚሆነው አጥፊዎችን ተጠያቂ የማድረጉ ሂደት ነው።”
በምሳሌነት ደግሞ ትግራዩን ጦርነት ያነሳሉ። በጦርነቱ በርካታ ጥሰቶች ተፈጽመዋል። በዚህ በኩል “በትግራይ ክልልም ይሁን በፌደራል መንግሥት በኩል ያሉ ባለሥልጣናት በአንድ ወይንም በሌላ መንገድ ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ አለ። የጦር ጄነራሎቹን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት አካላትን ተጠያቂ የሚያደርግ መንግሥታዊ አስተዳደር ሊኖር ይገባል” ይላሉ።
የሽግግር ወቅት ፍትህ ተስፋ እና ስጋት
የሽግግር ወቅት ፍትህ አስተዳደር ተአማኒ፣ ተቀባይነት ያለው፣ ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ እንዲከናወን ማድረግ እንደሚያስፈልግ አቶ ያሬድ እና ዶ/ር ዳንኤል አጽንኦት የሚሰጡት ጉዳይ ነው።
ለዚህም “ራሱን የቻለ ተቋም መመስረት ወይም በአንዳንድ አገሮች እንደታየው የተወሰነ ልምድ ካላቸው እና አሁን በሥራ ላይ ካሉ ልዩ ልዩ ተቋሞች ውስጥ የተውጣጣ አካል በበላይነት የሚመራው አስፈጻሚ አካል ማቋቋምን” የሚጠውሱት ዶ/ር ዳንኤል “ከእነዚህ አማራጮች ውስጥ ለኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የትኛው አሰራር፣ አደረጃጀት፣ አወቃቀር ነው የሚሻለው የሚለውን መመካከር እና መወሰን ያስፈልጋል” ይላሉ።
ከተለያዩ አገራት ተሞክሮ በመነሳት የሽግግር ወቅት ፍትህ ቅራኔዎችን እና ልዩነቶችን በመፍታት ረገድ አዎንታዊ ሚና መጫወቱን የሚገልጸው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ነው።
መሰል ሂደቶች ውሱን አውድ ያላቸው፣ በዜጎች የሚመሩ እና የተጎጂዎችን ፍላጎት ትኩረት ባደረገ መልኩ መሠራት እንዳለባቸውም ያስረዳል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ ለተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በሽግግር ፍትህ ሂደት አማካኝነት መፍትሄ ለማበጀት እና የቁርሾ ምዕራፎችን ለመዝጋት የሽግግር ፍትህ ኮሚሽን እንዲቋቋም ምክረ ሃሳብ ለመንግሥት መቅረቡን መረጃዎች ያሳያሉ።
አቶ ያሬድ እንደሚሉት የሽግግር ወቅት ፍትህ ለኢትዮጵያ “ጠቃሚነቱ ጥያቄ ውስጥ አይገባም ምክንያቱም ኢትዮጵያ እስካሁንም በጣም አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጸምባት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የመብት ጥሰት ሰለባ የሆኑባት፣ የአገር እና የሕዝብ ሃብት የወደመባት፤ ወደ ኋላ ወደ አስርት ዓመታት ብንቆጥር ብዙ ነገር ያለባት ሃገር ነች. . .
“ስለዚህ እንደ ኢትዮጵያ ያለፈውንም ቁስል ለማከም ዛሬም ያለውን አዳዲስ ቁስሎች ለማስቆም እና ወደ ተረጋጋ፣ ሠላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማቅናት ብቸኛው መንገድ የሽግግር ወቅት ፍትህ ሂደት ነው።”
አቶ ያሬድ በውጤቱ ግን እርግጠኛ አይደሉም “በግማሽ ልብ ነው የማየው። ምክንያቱም አሁን እንኳን በመንግሥት ደረጃ ስለአገራዊ እርቅ እና ስለሽግግር ወቅት ፍትህ እየተወራም የመንግሥት የፀጥታ አካላት የዜጎችን መብት ሲጥሱና ግጭቶች በየቦታው ሲበራከቱ ስለሚታይ ጥላውን እንዳያጠላበት እሰጋለሁ” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን በመጡ ማግስት የተቋቋመው እና በአገሪቱ የሚታዩት መሰል ችግሮች ለመፍታት የተቋቋመ የብሔራዊ የእርቅ ኮሚሽን እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ሳያሳካ በቅርብ መፍረሱ የሚታወስ ነው።
በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች ተስፋፍቶ በነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት የተሳተፉ ሁሉም ተፋላሚዎች ከጦር ወንጀሎች ጋር የሚስተካከሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የተባበሩት መንግስታት ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ሲገልጹ ቆይተዋል።
ለሁለት ዓመት የቆየውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በጦርነቱ ወቅት ለተፈጸሙ ጥፋቶች መቋጫ ለማበጀት የሽግግር ፍትህ ሂደት ተግባራዊ እንደሚሆን እየተነገ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም የጥሰት ፈጻሚዎች ወደ ፍርድ እንዲቀርቡ ዓለም አቀፍ ጫና እየተደረገ ሲሆን፣ ይህ ግፊት የሽግግር ፍትህ ሂደቱን ሊያደናቅፍ ስለሚችል፣ በተባበሩት መንግሥታት የተቋቋመው የአጣሪ ኮሚሽን ሥራ እና ሌሎች ጥረቶች እንዲቆሙ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥረት እያደረገ ይገኛል።