ሚኒስትሩ ላይ ከባድ ክስ አቅርበው በደቡብ አፍሪካ ነውጥ የፈጠሩት ፖሊስ

በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ክብርን ማግኘት የቻሉት የፖሊስ መኮንን ከሰሞኑ የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች በፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ አስተዳደር የላይኛው የሥልጣን እርከን ሰርገው ገብተዋል የሚል ክስ አቀረቡ።

የፖሊስ መኮንኑ በዚህ ንግግራቸው አስተዳደሩን ሲያናውጡ ከበርካታ ደቡብ አፍሪካውያን ዘንድ አድናቆት ተችሯቸዋል።

ጄነራል ንህላንህላ ምክዋንዚ የወታደራዊ መለዮቻውን ለብሰው፣ ጭንብል ባጠለቁ እና አውቶማቲክ መሳሪያ ባነገቡ የፖሊስ አባላት ተከበው ነው ከሰሞኑ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት።

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ጄነራሉ በድፍረት የአገሪቱ ፖሊስ ሚኒስትር ሴንዞ ምቹኑ ከወንጀለኞች ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ሲሉ ተናገሩ።

አለቃቸው የፖለቲካ ግድያዎችን እየመረመረ የነበረ ልዩ የምርመራ ክፍልን ዘግተዋል አሉ። ይህ የምርመራ ክፍል የአደንዛዥ ዕጽ ሕገወጥ መረብ በንግዱ ዘርፍ፣ በማረሚያ ቤቶች፣ በዐቃቢያነ ሕግ እና በፍትህ አካላት የዘረጋውን ሰንሰለት ያጋለጠ እንደሆነ ጠቀሱ።

"በፍልሚያ ላይ ነን፤ እኔ ራሱ በቀጥታ ነው ከወንጀለኞች ጋር እየተጋፈጥኩ ያለሁት" ሲሉ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ላይ በቀጥታ በተላለፈ ሥርጭት ተናግረዋል።

ለደቡብ አፍሪካውያን የተደራጁ ወንጀሎች የረጅም ጊዜ ስጋቶች ሆነው ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅትም "በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ" መድረሳቸውን የወንጀል ዋና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ዮሐንስ በርገር ይናገራሉ።

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ከወንጀል ቡድን ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ ሲወነጀል ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

በደቡብ አፍሪካ የፖሊስ ኃላፊ ሆነው ለረጅም ዘመናት ያገለገሉት ጃኪ ሴሌቢ ከጣሊያናዊው የአደንዛዥ ዕጽ ንጉሥ ተብሎ ከሚጠራው ግሌን አግሊዮቲ ሙስና ተቀብለዋል በሚል ክስ በአውሮፓውያኑ 2010 የአስራ አምስት ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል።

ጃኪ ሙስናውን የተቀበሉት የአደንዛዥ ዕጽ ንጉሡን የወንጀል እንቅስቃሴዎች እንዳላዩ ለመሆን በመስማማት ነበር ተብሏል።

ሆኖም ጄነራል ምክዋንዚ የፓርላማ አባል የሆኑትን እንዲሁም የፖሊስ ኃላፊውን ከወንጀለኛ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ በይፋ መክሰስ በደቡብ አፍሪካ ታይቶ አይታወቅም።

ለመጀመሪያ ጊዜም ነው አንድ ፖሊስ የፓርላማ አባልን እና ሚኒስትርን በዚህ መልኩ ሲወነጅል። ሚኒስትሩ ምላሽ የሰጡት ወዲያውኑ ሲሆን "መሠረተ ቢስ እና የማይጨበጥ" ሲሉ ነው ክሱን ውድቅ ያደረጉት።

"ለክሱ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ" ቢሉም ሕዝቡ በክዋዙሉ ናታል ግዛት የፖሊስ ኮሚሽነር ለሆኑት ጄነራል ምክዋንዚ ድጋፉን ችሯቸዋል ።

የ52 ዓመቱን የፖሊስ መኮንን መንግሥት እንዳይነካው በሚል በርካቶች እጃችሁን ከሳቸው ላይ አንሱ በሚል "ሃንድስ ኦፍ ንህላንህላ ምክዋንዚ" በሚል ሃሽታግ በርካቶች በኤክስ ገጽ አጋርተዋል።

"ምንም ማወላወል የማያውቅ በድፍረት የሚጋፈጥ ሰው እንደሆነ እየታየ ነው" ሲሉ በደቡብ አፍሪካ የጆሃንስበርግ ዩኒቨርስቲ የወንጀል ባለሙያ የሆኑት ካልቪል ራፋዲ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጄነራሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ አድናቆትን ያተረፉት ከዛሬ 15 ዓመት ገደማ ነበር።

በወቅቱ የአገሪቱ ተጠባባቂ ፖሊስ አዛዥ የነበሩት ጄነራሉ የወንጀል መረጃ ኃላፊ የነበሩት ሪቻርድ ምድሉሊን በማገዳቸው ነበር።

ኃላፊው በወቅቱ አገሪቱን ይመሩ የነበሩት የፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ የቅርብ አጋር መሆናቸው ነው በርካቶችን ያስገረመው።

ኃላፊው በአፈና፣ ጥቃት እና በማስፈራራት የአምስት ዓመት እስራት የተፈረደባቸው ሲሆን፣ የጄነራሉንም በፖሊስ ተቋም ውስጥ "የበሰበሰ አፕል" ነው የሚለውን አስተያየታቸውን ያረጋገጠ ነው ተብሏል።

በወቅቱ 38 ዓመታቸው የነበሩት ጄነራሉ ከበላይ ኃላፊዎቻቸው ከፍተኛ ጫና ገጥሟቸው እንደነበርና ከዕድሜያቸው አንጻር "በቀላሉ ይታለላሉ የሚል አስተሳሰብ ነበር፤ ነገር ግን በጣም ተሳስተዋል" ሲሉ ዶክተር በርገር ያስረዳሉ።

ኃላፊው እንዲታገዱ ያሳለፉትን ውሳኔ መግፋት ብቻ ሳይሆን ጄነራሉ በፓርላማ ቀርበው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እየደረሰብኝ ነው ሲሉ ተጋፈጡ።

ይህ ሥልጣንን መጋፈጣቸው በሕዝቡ ዘንድ አድናቆትን ቢያተርፍላቸውም ድፍረታቸው በባለሥልጣናቱ ስላልተወደደላቸው በዓመቱ ከሥልጣን እንዲወርዱ ተደረጉ።

እንዲሁም ለዓመታትም ወደ ኃላፊነት እንዳይመጡ ተደረጉ።

ሆኖም በአውሮፓውያኑ 2018 የያኔው የፖሊስ ሚኒስትር ብሄኪ ሴሌ የክልል ፖሊስ አዛዥ ሹመት መስጠታቸውን ተከትሎ ጄነራሉም ወደ አደባባይ ተመለሱ።

በዚህም ዋነኛ ኃላፊነት የተሰጣቸው የፖለቲካ ሥልጣን ፉክክር እና አትራፊ የመንግሥት ጨረታዎች ብርቱ በሆነባት በዚህች ክልል የሚፈጸሙ ግድያዎችን መመርመር ነው።

ለጄነራሉም ጋዜጣዊ መግለጫ መነሻ የሆነውም ይህ የምርመራ ክፍል በሚኒስትሩ በመበተኑ ነው። ጄነራሉ እንዳሉት 121 ክሶች በብሔራዊ ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት "አቧራ እየጠጡ ነው" በማለት ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

"ለዚሀ ለፖሊስ ባጅ እሞታለሁ፤ ወደ ኋላ አልልም" ሲሉ ነበር በሙስና በተዘፈቁ የፖለቲካ እና የንግድ ኃያላን ሊታለሉ እንደማይችሉ ማሳየት የቻሉት ደፋሩ ፖሊስ ጄነራል ምክዋንዚ።

የአገሪቱ ሰብዓዊ ጥናት እና ምርምር ካውንስል የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ በፖሊስ ላይ ያለው አመኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ እንደሆነ ያሳየ ሲሆን፣ ከምንጊዜውም በላይ ዝቅተኛ በመሆን 22 በመቶ መድረሱን አሳይቷል።

የፖሊስ ተቋም በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት፣ በሙስና እና ከፍተኛ ወንጀሎችን ባለመቅረፍ የብቃት ማነስ ጉዳዮች ሲታመስ ቆይቷል።

ቀውስ በተቋሙ ከፍተኛ መዋቅር ላይ የታየ ሲሆን፣ ከአውሮፓውያኑ 2000 ጀምሮ ወደ 10 የሚጠጉ የፖሊስ ኃላፊዎች በንክኪዎች ተወንጅለዋል። አንደኛው በሙስና ሲከሰሱ ሌላቸው ደግሞ የወንጀል ክሶችን እየጠበቁ ነው።

"ቀውሱ በሁሉም ደረጃዎች ላይ ነው። መምጣት ያለባቸው በርካታ ለውጦች አሉ" ሲሉ በፕሪቶሪያ የሚገኘው የፀጥታ ጥናት ተቋም ባልደረባ ጋሬዝ ኒውሃም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጄነራሉም በፖሊስነት ባገለገሉበት ዘመናቸው ውዝግብ አላጣቸውም። በአንድ ማረሚያ ቤት ከፍተኛ ባለሥልጣን የወንጀል ምርመራ ጣልቃ ገብተዋል በሚል ቅሬታ ቀርቦባቸው የፖሊስ ተቆጣጣሪ ተቋም ምርመራ ከፍቶባቸው ነበር።

ነገር ግን ባለፈው ወር ከቀረበባቸው ክስ ነጻ ሆነዋል። በጁሊየስ ማሌማ የሚመራው የኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተር (ኢኤፍኤፍ) ፓርቲ በጄነራሉ ላይ የቀረበው ውንጀላ "ወንጀልን እና ሙስናን ለመዋጋት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ያለውን ቁርጠኛ መኮንን ለማደናቀፍ የተደረገ ነው" ሲል መግለጫ አውጥቷል።

ጄነራሉ እና ቡድናቸው ሌላ የሚተቹበት ጉዳይ ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ላይ ኃይል መጠቀማቸው ነው። በእሳቸው ስር በሚገኙ መኮንኖች እና በተጠርጣሪዎች መካከል ባሉ ፍጥጫዎች አንዳንድ ጊዜ ተጠርጣሪዎች በጥይት ይገደላሉ።

ጄነራሉ ከሁሉም ፖሊሶች በላይ ተደርገው ስለሚታዩም መኮንኖቻቸው እየፈጸሟቸው ያሉ ጥሰቶችን ማኅበረሰቡ በዝምታ ያልፋል ሲሉ ነውሃም ይናገራሉ። እንደ ምክንያትነትም የሚጠቅሱት "በፖሊስ ተቋም ውሰጥ ጀግና እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ" ብለዋል።

ሚኒስትሩ መታገዳቸው ተከትሎን ፊሮዝ ካቻሊያ ተጠባባቂ የፖሊስ ሚኒስትር ይሆናሉ። የሕግ ፕሮፈሰሩ ፊሮዝ ከታዋቂ የፀረ-አፓርታይድ አራማጆች ቤተሰብ የተወለዱ ሲሆን፣ በደቡብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማዕከል በሆነችው ጋውቴንግ የማኅበረሰብ ደኅንነት ሚኒስትር በመሆን ከአውሮፓውያኑ 2004 እስከ 2009 ድረስ አገልግለዋል።

ካቻሊያ ጄነራል ምክዋንዚ በዚህ መልኩ ውንጀላቸውን ለሕዝብ ይፋ ማድረጋቸው እጅግ ያልተለመደ እንደሆነ ከአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ 'ኒውዝሩም አፍሪካ 'ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

ሆኖም ይላሉ የሕግ ፕሮፌሰሩ "እውነት ሆኖ ከተገኘ ይህንን ማድረጉ ምክንያታዊ መሆኑን መለስ ብለን ለማየት እንችላለን" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የጄነራል ምክዋንዚ ተዓማኒነታቸው አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። የወነጀሏቸውን ሚኒስትር ማስረጃ አቅርበው መረጋገጥ ይጠበቅበታል።

በአሁኑ ወቅት ግን የፖለቲካ ኃላፊዎቹን ሁለት ጊዜ በመጋፈጥ ደፋርነታቸውን ያስመሰከሩ በሚል ስማቸው ከፍ እንዳለ ነው።