የአሜሪካ ምርጫ፡ ማን እየመራ ነው? ትራምፕ ወይስ ካማላ?

አሜሪካዊያን በሚመጣው ኅዳር 5 መሪያቸውን ለመምረጥ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ያመራሉ።

የ2024 ምርጫ በፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና ዶናልድ ትራምፕ መካከል ነበር እንዲካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት። ነገር ግን ባይደን ባደረባቸው የጤና እክል ምክንያት ራሳቸውን አግልለው ምክትላቸው ካማላ ሀሪስን አጭተዋል።

አሁን አሜሪካዊያን እየጠየቁ ያሉት ትልቁ ጥያቄ ሀገራቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት መሪ ይኖራታል ወይስ ዶናልድ ትራምፕ ድጋሚ ይመረጣሉ? የሚለው ነው።

የድምፅ መስጫው ቀን ተቃርቧል። በጎን የሚሰበሰቡ ድምፆች ምን ያመለክታሉ? የዕጩዎቹ የምርጫ ዘመቻስ እንዴት እየሄደ ነው?

በቅድመ ምርጫው ማን እየመራ ነው?

ከዋናው የድምፅ መስጫ ቀን በፊት በለተያዩ ተቋማት የሚሰበሰቡ ድምፆች አሉ። በመላው ሀገሪቱ በሚሰበሰበው ድምፅ መሠረት ወርሐ ሐምሌ ፉክክሩን የተቀላቀሉት ካማላ ሀሪስ እየመሩ ነው።

ዲሞክራቷ ካማላ ሀሪስ በጠባብ ድምፅ ተቀናቃኛቸው ዶናልድት ትራምፕን እየመሩ እንደሆነ እስከ ጥቅምት 5፤ 2024 የተሰበሰቡ ድምፆች ያሳያሉ።

ባለፈው መስከረም አጋማሽ ሁለቱ ዕጩዎች ያደረጉትን ፕሬዝደንታዊ ሙግት ከ67 ሚሊዮን በላይ ሰው በቀጥታ የቴሌቪዠን ሥርጭት ተከታትሎታል።

ከዚህ ክርክር በኋላ የተሰበሰቡ ድምፆች እንደሚጠቁሙት ካማላ ሀሪስ ተቀናቃኛቸው ዶናልድ ትራምፕን በጠባብ ልዩነት መምራት ጀምረዋል። ካማላ በወቅቱ ልዩነታቸውን ከ2.5 ወደ 3.3 ከፍ ማጥበብ ችለዋል። ምክትል ፕሬዝደንቷ በምርጫ ክርክሩ ተሽለው እንደተገኙ ብዙዎች ያምናሉ።

ዶናልድ ትራምፕ በተቃራኒው ከምርጫ ክርክሩ በፊት የነበራቸው ተቀባይነት በጥቂት መውረዱን ቁጥሮች ይጠቁማሉ።

ምንም እንኳ ከዋናው ድምፅ መስጫ ቀን በፊት የሚሰበሰቡበት ድምፆች የዕጩዎችን ተቀባይነት የሚያንፀባርቁ ቢሆኑም የምርጫውን ውጤት ያሳያሉ ማለት ግን አይቻልም።

ምክንያቱም አሜሪካ ፕሬዝደንቷን የምትመርጠው ኢሌክቶራል ኮሌጅ በተባለ መንገድ ነው። ይህ ማለት እያንዳንዱ ግዛት እንዳለው የሕዝብ ብዛት መጠን ድምፅ ይሰጠዋል ማለት ነው።

በጠቅላላው 538 ኢሌክቶራል ኮሌጅ የሚባሉ ድምፆች አሉ። ዕጩዎች ዋይት ሐውስ ለመግባት ቢያንስ 270 ኢሌክቶራል ኮሌጅ ማግኘት አለባቸው።

በዩናይትድ ስቴትስ 50 ግዛቶች አሉ። አብዛኛውን ጊዜ እኒህ ግዛቶች ድምፃቸውን ለማን እንደሚሰጡ የታወቀ ነው። ዕጩዎች ድምፅ ማግኘት ያለባቸው ‘ስዊንግ ስቴት’ በተባሉ እና የትኛውን ዕጩ እንደሚመርጡ በማይታወቁ ግዛቶች ነው።

በማያዳሉት ግዛቶች ማን እየመራ ነው?

ሰባት ግዛቶች ድምፃቸውን ለማን እንደሚሰጡ እስካሁን አልለየም። በእነዚህ ግዛቶች በካማላ እና ትራምፕ መካከል ያለው ልዩነት እጅግ ጠባብ ነው።

በጣም ብዙ ኢሌክቶራል ኮሌጅ ያላት ፔንሲልቬኒያ ግዛት ናት። በዚህችም ግዛት ቢሆን ማን አሸናፊ ይሆናል የሚለውን መለየት አዳጋች ሆኗል።

ሰባቱ ወሳኝ ግዛቶች ፔንሲልቬኒያ፣ ኖርዝ ካሮላይና፣ ኔቫዳ፣ አሪዞና፣ ጆርጂያ፣ ሚሺጋን እና ዊስኮንሲን ናቸው።

ካማላ ሀሪስ የምርጫ ዘመቻውን ከተቀላቀሉ በኋላ በበርካታ ግዛቶች ጠንከር ብለው መገኘታቸው እየታየ ነው። በለተይ በሚሺጋን፣ ፔንሲልቬኒያ እና ዊስኮንሲን ሀሪስ እየመሩ መሆኑን የቁጥር መለኪያዎች ያሳያሉ። ቢሆንም ልዩነቱ አሁንም ጠባብ ነው።

እኒህ ግዛቶች ለወትሮው ለዲሞክራቲክ ፓርቲው ነበር ድምፃቸውን የሚሰጡት። ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 2016 ዶናልድ ትራምፕ ምርጫ ሲያሸንፉ ሁኔታዎች ተቀየሩ።

ባይደን ደግሞ በ2020 ዶናልድ ትራምፕን ሲረቱ እኒህ ግዛቶች መልሰው ሰማያዊ [የዲሞክራቶች መለያ ቀለም] ሆኑ። ሀሪስ እኒህን ግዛቶች የሚያሸንፉ ከሆነ ቀጣይዋ ፕሬዝደንት የመሆን ዕድላቸው ይሰፋል።

ኤቢሲ የተሰኘው የአሜሪካ ቴሌቪዥን ጣቢያ ድምፅ መሰብሰቢያ የሆነው 538 የተባለው ድረ-ገፅ ነው ድምፅ የሚሰበስበው።

አሁን በካማላ ሀሪስ እና በዶናልድ ትራምፕ መካከል ያለው ልዩነት እጅግ ጠባብ ስለሆነ አሸናፊውን መገመት ያዳግታል።

በ2016 ምርጫ ከምርጫው በፊት የተሰበሰቡ ድምፆች ዶናልድ ትራምፕ ይሸነፋሉ የሚሉ ነበሩ። በ2020 ምርጫም እንዲሁ በተመሳሳይ ዶናልድ በተቀናቃኛቸው ተቀድመው ነበር።