ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን የጋዛ ጦርነት እንዲቆም እና ታጋቾች እንዲለቀቁ ለመጠየቅ አደባባይ ወጡ
የጋዛ ጦርነት እንዲቆም እና በሐማስ የተያዙ ታጋቾች እንዲለቀቁ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ለመጠየቅ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ወደ አደባባይ ወጡ።
እሁድ እለት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በቴልአቪቭ 'ሆስቴጅ' በተሰኘው አደባባይ የወጡ ሲሆን የአደባባይ ተቃውሞው አዘጋጆች የእስራኤል መንግሥት ጋዛን ለመውረር የያዘው ዕቅድ በሐማስ ተይዘው ያሉ 20 የሚሆኑ ታጋቾችን አደጋ ላይ ይጥላል ብለዋል።
የዚህ የአደባባይ ተቃውሞ አካል በሆነው ብሄራዊ የስራ ማቆም አድማ መንገዶች፣ ቢሮዎች እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ተዘግተዋል። ከዚህ የአደባባይ ተቃውሞ ጋር ተያይዞ ወደ 40 የሚጠጉ ሰዎች ታስረዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የአደባባይ ተቃውሞውን "የሃማስን አቋም የሚያጠናክር" እንዲሁም የታጋቾችን መለቀቅ የሚያጓትት ነው ሲሉ ተችተዋል።
የቀኝ አክራሪ ሚኒስትሩ ቤዛሌል ስሞትሪች በተመሳሳይ አውግዘው "ሃማስን የሚያግዝ ጎጂ ዘመቻ" ሲሉ ፈርጀውታል።
ይህ አገራዊ የስራ ማቆም አድማን ያሰናዱት የታጋቾች ቤተሰቦች እና የጦርነቱን መስፋፋት የተቃወሙ አካላት ናቸው።ኢይናቭ ዛንጋውከር የተሰኙ ልጃቸው የታገተባቸው እናት "ሁሉን አቀፍ እና ተጨባጭ የሆነ ስምምነት እና ጦርነቱ እንዲቆም" እየጠየቅን ነው ብለዋል። ይህ ተቃውሞ የተካሄድ የእስራኤል የጦር ካቢኔ የጋዛን ከተማ ለመውረር እንዲሁም ፍልስጤማውያኑን የማፈናቀል ውሳኔን ካጸደቀ በኋላ ነው። ይህ የእስራኤል እርምጃ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት ጨምሮ በበርካታ አገራት ውግዘት ደርሶበታል።
እስራኤል ዘይቱን የተባለቸውን የጋዛ ከተማ ላይ እየፈጸመ ባለው ለቀናት በቀጠለ ከፍተኛ ጥቃት "አሰቃቂ ሁኔታ መፍጠሩን " እና በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን መፈናቀላቸውን በሐማስ የሚመራው የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ለቢቢሲ ተናግሯል። የእስራኤል ጦር ቅዳሜ ዕለት ብቻ ባደረሰው ጥቃት ቢያንስ 40 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ አስታውቋል።
የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ ምስራቃዊ እና ደቡባዊ ከበባቢዎች በተለይም በዘይቱን ከተማ ያላሰለሰ ጥቃት እያደረሱ መሆኑን ሐማስ በመግለጫው አስታውቀዋል።
የእስራኤል ጦር ድንኳኖች በእርዳታ ኤጀንሲዎች አማካኝነት ወደ ጋዛ እንዲገቡ መፍቀድ እንደሚጀምር አስታውቋል።
"ህዝቡን ከጦርነት ቀጣና አውጥቶ ወደ ደቡባዊ ጋዛ ሰርጥ ለማስፈር በሚደረገው ዝግጀት የድንኳን እና መጠለያዎች አቅርቦት እንደገና ይቀጥላል" ሲል የእሰራኤል ወታደራዊ አካል ኮጋት ገልጿል።
የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን በግዳጅ አፈናቅሎ በደቡባዊ ጋዛ በሚዘጋጅ ካምፕ ለማስገባት ዕቅድ የያዘ ሲሆን ፤ ጦሩ የጋዛ ከተማን የሚወርበት የጊዜ ሰሌላ አላስቀመጠችም።
በራፋህ ከተማ ፍርስራሽ ላይ ይቋቋማል የተባለው ይህ ካምፕ በመጀመሪያ 600 ሺህ ፍልስጤማውያን በመቀጠልም አጠቃላይ የጋዛን ሕዝብ፣ 2.1 ሚሊዮን የሚያኖር እንደሆነ ተገልጾ ፍልስጤማውያኑ ከካምፑ መውጣት እንደማይፈቀድላቸው ተገልጿል።
በዚህ አውዳሚ ጦርነት ከ2.1 ሚሊዮን ከሚሆነው የጋዛ ሕዝብ መካከል 90 በመቶ ወይም 2.1 ሚሊዮን ሕዝብ ተፈናቅሏል። አንዳንዶች በተደጋጋሚ የተናፈናቀሉ ሲሆን በርካታዎቹ በተጨናነቀ እና በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚኖሩት።
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ያለውን ሰፈራ በማፍረስ በአውሮፓውያኑ 2005 ጦሯን አስወጥታ ነበር።
ሆኖም ከግብፅ ጋር በጋራ በመሆን የጋዛን ፀጥታ እና መዳረሻ ተቆጣጥራ ትገኛለች።
ይህ የእስራኤል እንደገና የመጠቅለል ዕቅድ የተሰማው ለአስርት ዓመታት የቀጠለውን የእስራኤልና ፍልስጤም ጦርነት እልባት ለመስጠት የሁለት ግዛት መፍትሄ ሃሳቦች እንደገና እየቀረቡ ባሉበት ወቅት ነው።
የፍልስጤም አገር ምሥረታ እስራኤል በኃይል በያዘቻቸው ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን ጨምሮ ጋዛን ያካተተ ዕቅድ ነው።
እስራኤል በአገርነት፣ በአውሮፖውያኑ 1948 ስትመሠረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ያፈናቀለች ሲሆን፣ ይህንንም "ናቅባ" (ታላቁ እልቂት) ሲሉ ይጠሩታል።
በአሁኑ ወቅትም ፍልስጤማውያኑ ይኸው ይደገማል በሚል ፍራቻ ላይ ናቸው።
ከቀያቸው የተፈናቀሉት ፍልስጤማውያኑ አብዛኞቹ በጋዛ ሰፍረዋል።
በአሁኑ ወቅት ካሉ የጋዛ ነዋሪዎች መካከል ሦስት አራተኛውን የሚይዙት በዚያን ወቅት የተፈናቀሉ የልጅ ልጆች ናቸው።
ሌሎች 900 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ አሁን እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ ይኖራሉ።
በተጨማሪም 3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በዮርዳኖስ፣ በሶሪያ እና በሊባኖስ እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።
ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ለ700 ሺህ አይሁዳውያን መኖሪያ የሚሆኑ 160 ሰፈራዎችን ገንብታለች። በዌስት ባንክ 3.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ይኖራሉ።
አብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እስራኤል እያደረገችው ያለውን ሰፈራ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ነው ሲል ይኮንናል።
እስራኤል ይህንን አትቀበልም።
በእስራኤል በተከታታይ የመጡ አስተዳደሮች ሰፈራዎች እንዲስፋፉ አድርገዋል።
ይሁን እንጂ ሰፈራን የሚደግፈው የቅኝ ክንፍ አክራሪ ጥምረት የሆነውን መንግሥት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድጋሚ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሰፈራዎች እየተስፋፉ ይገኛሉ።
የጋዛ ጦርነትም እንዲሁ ለእነዚህ ሰፈራዎች መጨመር በር መክፈቱም ተነግሯል። ሰፈራዎች መስፋፋት ብቻ ሳይሆን ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያኑ ላይ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች መባባሱም ተገልጿል።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ የጋዛ ጦርነት ከተነሳ ጀምሮ በዌስት ባንክ ቢያንስ 975 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ፀጥታ ኃይሎች እና በእስራኤል ሰፋሪዎች ተገድለዋል።