የእስራኤል የፀጥታ ካቢኔ የኔታንያሁ የጋዛ ከተማ ወረራ ዕቅድን አጸደቀ

የእስራኤል የፀጥታ ካቢኔ የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የጋዛ ከተማ ወረራ ዕቅድን አጸደቀ።

ሐማስን ትጥቅ ማስፈታት እና ከጋዛ አስተዳዳሪነቱ ማስወገድን ጨምሮ አምስት መርሆዎችን ይዟል የተባለው ጦርነቱን የመቋጨት እንዲሁም የጋዛ ከተማ ወረራ ዕቅድ የጸደቀው አርብ ዕለት ነው።

ውሳኔው የተላለፈው "ከፍተኛ አብላጫ ያላቸው የካቢኔ ሚኒስትሮች ለአማራጭነት የቀረበላቸው ሌላኛው ዕቅድ የሐማስን መሸነፍ ወይም ታጋቾችን መመለስ ማሳካት እንደማይቻል ካመኑ በኋላ መሆኑን" የወጣው መግለጫ ያስረዳል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት በካቢኔው በአብላጫ ድምጽ የጸደቁ የጋዛ ከተማን ለመውረር እንዲሁም ጦርነቱን የመቋጨት አምስት መርሆዎችን ዕቅዶችን ዘርዘር ያለ መግለጫ አውጥቷል።

"የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር የጋዛን ከተማ ለመቆጣጠር እና ከጦርነቱ ቀጣና ውጪ ላሉ ሰላማዊ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታም ለመስጠት ይዘጋጃል" ብሏል።

የእስራኤል መከላከያ ጦርነቱን ለመቋጫት መርሆዎች ያላቸውንም ዘርዝሯል።

አምስቱ ተብለው የተዘረዘሩት ሐማስን ትጥቅ ማስፈታት፣ ሁሉንም ታጋቾች መመለስ (በሕይወት ያሉ እንዲሁም የሞቱትን አስከሬኖቻቸውን)፣ የጋዛ ሰርጥን ከወታደራዊ ትጥቅ ነጻ ማድረግ፣ ጋዛን የሚያስተዳድረውን ሐማስን በማስወገድ እንዲሁም ዌስት ባንክን ከሚያስተዳድረው የፍልስጤም አስተዳደር ውጪ የሆነ አማራጭ የሲቪል መንግሥት ምሥረታን ያካተተ ነው።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የጋዛ ወረራ ዕቅዶቻቸውን በተመለከተ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ "ደኅንነታችንን ለማረጋገጥ፣ ሐማስን ለማስወገድ እንዲሁም ሕዝቡ ነጻ እንዲሆን የጋዛን አስተዳደር ለሲቪል መንግሥት የማስተላለፍ ዕቅድ አለን። ይህንን አስተዳደር የሚረከበው ሐማስ ወይም የእስራኤልን መጥፋት የሚደግፍ አይሆንም" ብለዋል።

"ራሳችንን ነጻ አውጥተን የጋዛን ሕዝብ ከሐማስ አስከፊ ሽብር ነጻ ማውጣት እንፈልጋለን" ሲሉ የተናገሩት ኔታንያሁ ሆኖም እስራኤል ጋዛን "ጠቅልላ ማቆየትም ሆነ እንደ አስተዳዳሪ መቆየት እንደማትፈልግ" ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የጋዛ ወረራ ዕቅድ ከፍተኛ ስጋት እንዳሳደረባቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ ባለሥልጣን ገልጸዋል።

"ይህ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን አሰቃቂ መዘዞችን የሚያስከትል እንዲሁም በጋዛ የቀሩት ታጋቾችን ሕይወት የበለጠ አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል" ሲሉ የተመድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሚሮስላቭ ጄንካ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ማክሰኞ በነበረ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።

እስራኤል አብዛኛውን የጋዛ ሰርጥን ተቆጣጥራ የምትገኝ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት 87 በመቶ የሚሆነው የጋዛ ሰርጥ ወታደራዊ ቀጣና ወይም ጋዛውያን በአስገዳጅ የሚፈናቀሉባቸው ቦታዎች እንደሆኑ አስታውቋል።

ለጥቂት ጊዜ የቆየው የተኩስ አቁም መጋቢት ወር ላይ መፍረሱን ተከትሎ እስራኤል ሁሉንም የድንበር አካባቢዎች "አደገኛ የውጊያ ቀጣና" በሚል ፈርጃ በቀጣዮቹ ወራት እነዚህ ቀጣናዎች እየሰፉ መጥተዋል።

በዚህ አውዳሚ ጦርነት ከ2.1 ሚሊዮን ከሚሆነው የጋዛ ሕዝብ መካከል 90 በመቶ ወይም 2.1 ሚሊዮን ሕዝብ ተፈናቅሏል። አንዳንዶች በተደጋጋሚ የተናፈናቀሉ ሲሆን በርካታዎቹ በተጨናነቀ እና በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚኖሩት።

የእስራኤል ጦር በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን በሙሉ አፈናቅሎ በደቡባዊ ክፍል በሚዘጋጅ ካምፕ ለማስገባት ዕቅድ እንዲያዘጋጅ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ትዕዛዝ መስጠታቸውን ከዚህ ቀደም ተዘግቦ ነበር።

በራፋህ ከተማ ፍርስራሽ ላይ ይቋቋማል የተባለው ይህ ካምፕ በመጀመሪያ 600 ሺህ ፍልስጤማውያን በመቀጠልም አጠቃላይ የጋዛን ሕዝብ፣ 2.1 ሚሊዮን የሚያኖር እንደሆነ ተገልጾ ፍልስጤማውያኑ ከካምፑ መውጣት እንደማይፈቀድላቸው ተገልጿል።

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ያለውን ሰፈራ በማፍረስ በአውሮፓውያኑ 2005 ጦሯን አስወጥታ ነበር።

ሆኖም ከግብፅ ጋር በጋራ በመሆን የጋዛን ፀጥታ እና መዳረሻ ተቆጣጥራ ትገኛለች።

ይህ የእስራኤል እንደገና የመጠቅለል ዕቅድ የተሰማው ለአስርት ዓመታት የቀጠለውን የእስራኤልና ፍልስጤም ጦርነት እልባት ለመስጠት የሁለት ግዛት መፍትሄ ሃሳቦች እንደገና እየቀረቡ ባሉበት ወቅት ነው።

የፍልስጤም አገር ምሥረታ እስራኤል በኃይል በያዘቻቸው ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን ጨምሮ ጋዛን ያካተተ ዕቅድ ነው።

እስራኤል በአገርነት፣ በአውሮፖውያኑ 1948 ስትመሠረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ያፈናቀለች ሲሆን፣ ይህንንም "ናቅባ" (ታላቁ እልቂት) ሲሉ ይጠሩታል።

በአሁኑ ወቅትም ፍልስጤማውያኑ ይኸው ይደገማል በሚል ፍራቻ ላይ ናቸው።

ከቀያቸው የተፈናቀሉት ፍልስጤማውያኑ አብዛኞቹ በጋዛ ሰፍረዋል።

በአሁኑ ወቅት ካሉ የጋዛ ነዋሪዎች መካከል ሦስት አራተኛውን የሚይዙት በዚያን ወቅት የተፈናቀሉ የልጅ ልጆች ናቸው።

ሌሎች 900 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ አሁን እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ ይኖራሉ።

በተጨማሪም 3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በዮርዳኖስ፣ በሶሪያ እና በሊባኖስ እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።

እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1967 በተደረገው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ነው የፍልስጤማውያኑ ግዛት የሆኑትን ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን የተቆጣጠረችው።

ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ለ700 ሺህ አይሁዳውያን መኖሪያ የሚሆኑ 160 ሰፈራዎችን ገንብታለች። በዌስት ባንክ 3.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ይኖራሉ።

አብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እስራኤል እያደረገችው ያለውን ሰፈራ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ነው ሲል ይኮንናል።

እስራኤል ይህንን አትቀበልም።

በእስራኤል በተከታታይ የመጡ አስተዳደሮች ሰፈራዎች እንዲስፋፉ አድርገዋል።

ይሁን እንጂ ሰፈራን የሚደግፈው የቅኝ ክንፍ አክራሪ ጥምረት የሆነውን መንግሥት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድጋሚ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሰፈራዎች እየተስፋፉ ይገኛሉ።

የጋዛ ጦርነትም እንዲሁ ለእነዚህ ሰፈራዎች መጨመር በር መክፈቱም ተነግሯል። ሰፈራዎች መስፋፋት ብቻ ሳይሆን ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያኑ ላይ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች መባባሱም ተገልጿል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ የጋዛ ጦርነት ከተነሳ ጀምሮ በዌስት ባንክ ቢያንስ 975 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ፀጥታ ኃይሎች እና በእስራኤል ሰፋሪዎች ተገድለዋል።