ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ በምዕራባውያኑ ፋብሪካ የሶቪየት ኅብረት ዘመን መኪናን መልሳ ማምረት ጀመረች
በዩክሬን ላይ ከተፈጸመው ወረራ በኋላ ተዘግቶ ቆይቶ በኋላ ላይ መንግሥት ቁጥጥር ስር በገባው የቀድሞው የሬኖ መኪና ፋብሪካ የሶቪየት ዘመን ተሽከርካሪን ሩሲያ ማምረት ጀመረች።
ምርት የጀመረው የጭነት ተሽከርካሪ አምራቹ “ካማዝ” እንዳስታወቀው የመጀመሪያዎቹ ምርቶቹ በቀጣይ ታኅሣሥ ወር ለሽያጭ ይቀርባሉ።
ፋብሪካው ዲዛይናቸው የተሻሻሉ በሶቪት ኅብረት ዘመን በስፋት ይታወቁ የነበሩት “ሞስኮቪች” የተሽከርካሪ አይነትን መልሶ በገበያው ላይ እንዲያንሰራራ እንደሚያደርግ ተነግሯል።
የፈረንሳዩ መኪና አምራች ሬኖ ሩሲያን ለቆ የወጣው የዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ ምዕራባውያን ኩባንያዎች በገፍ አገሪቱን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ ነው።
ወረራውን ተከትሎ ከሩሲያ ለቀው ከወጡት ታላላቅ ስም ካላቸው የምዕራቡ ዓለም ተቋማት መካከል ማክዶናልድስ እና ስታርባክስ ይጠቀሳሉ።
ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ ያጣሏቸው ማዕቀቦች አገሪቱ በዩክሬን ላይ ለከፈተችው ወረራ ምላሽ ሲሆን፣ ከቀሪው ዓለም እንድትነጠል በማድረግ ከውጪ የሚገቡ ግብአቶችን እንዳታገኝ ለማድረግ የታለመ ነው።
የመኪና አምራቹ ፋብሪካ የቴክኖሎጂ አጋር ለመሆን ባለፈው ዓመት ሐምሌ ከካማዝ ጋር ስምምነት የፈረመ ሲሆን፣ በተጨማሪም የሩሲያ መንግሥት ከቻይናው የመኪና አምራች ጄኤሲ ጋር እየሰራ መሆኑን ሮይተርስ በስም ካልጠቀሳቸው ምንጮች መረጃ መግኘቱን አመልክቷል።
ካማዝ ባወጣው መግለጫ እንዳለው በሂደት ለተሽከርካሪ ምርቱ የሚያስፈልጉትን ግብአቶች ለማግኘት የአገር ውስጥ አቅራቢዎችን በሂደት ለማጠናከር እንደሚያስብ ገልጾ፣ ለጊዜው ምርቱ ውስን ሊሆን እንደሚችል ጠቅሷል።
ካማዝ በቀጣይ አንድ ወር ውስጥ 600 የሚደርሱ መኪኖችን አመርታለሁ ብሎ እንደሚጠብቅ ገልጿል። በቀጣይ የፈረንጆች ዓመት ውስጥ ደግሞ የምርቱን መጠን ወደ 100,000 ተሽከርካሪዎች እንዲደርስ የሚያደርግ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል የተወሰኑት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ይሆናሉ ብሏል።
በዩክሬን የሚካሄደው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በሩሲያ የሚመረተው የተሽከርካሪዎች አጠቃላይ ቁጥር ቀንሷል። በዚህም ሳቢያ የተሽከርካሪዎች ሽያጭ መጠን ከአንድ ሚሊዮን በታች ሊያሽቆለቁል የሚችል ሲሆን፣ ይህም በዘመናዊው የሩሲያ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያጋጥም ዝቅተኛው ሽያጭ እንደሚሆን ሮይተርስ ዘግቧል።