የአሜሪካ እና የካናዳ የፍለጋ ቡድኖች ታይታኒክን ስትጎበኝ የጠፋችውን የቱሪስት ሰርጓጅ መርከብ እየፈለጉ ነው

የታይታኒክ መርከብ ፍርስራሽ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የታይታኒክ መርከብ ቅሪት በአትላንቲክ ውቅያኖስ ግርጌ በ3 ሺህ 800 ሜትር ጥልቀት ላይ ይገኛል።

የአሜሪካ እና የካናዳ የአሰሳ ቡድኖች እሁድ እለት የታይታኒክ መርከብን ቅሪት ለመጎብኘት ጠልቆ በገባበት ወቅት የጠፋውን የቱሪስት ሰርጓጅ መርከብ ለማግኘት ከሰዓት ጋር እየተሽቀዳደሙ ነው።

በመጠን አነስተኛው ባህር ሰርጓጁ ወደ ውቅያኖሱ ጠልቆ በገባ በ1፡45 ደቂቃ ውስጥ ግንኙነቱ ሲቋረጥ አምስት ሰዎችን አሳፍሮ ነበር ተብሏል።

ነፍስ የማዳን ሥራው በመሃል አትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ ሌሊቱን የቀጠለ ሲሆን እስካሁን የሰርጓጅ መርከቧ ዳና አልተገኘም።

የመንግሥት ተቋማት፣የሁለቱ አገራት የባህር ኃይሎችና የንግድ የባህር ጠላቂ ድርጅቶች ነፍስ የማዳኑን ሥራ እየረዱ ነው።

እስከ ሰኞ ከሰዓት ድረስ በመርከቧ የተሳፈሩት ግለሰቦች የቀራቸው ኦክስጅ አራት ቀናት የሚያቆይ እንደሆነ ተነግሯል።

ሰርጓጅ መርከቧ ላይ ከነበሩ ግለሰቦች ውስጥ እንግሊዛዊው ቢሊየነር የንግድ ሰው እና ጎብኝ ሃሚሽ ሃርዲንግ ይገኝበታል።

የአሜሪካ የባህር ጠረፍ ጠባቂ ባልደረባ ሪየር አድም ጆን ማውገር፣“ አሁን ላይ ትኩረታችን እስከምንችለው ድረስ በአካባቢው ፍለጋችንን መቀጠል ነው” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

መርከቧን ለመፈለግ የጦር አውሮፕላኖች፣ ሰርጓጅ መርከቦች እና በውሃ ውስጥ ያለ ድምጽን የሚያነፈንፍ እና የራዲዮ ሞገድ የሚልክ ሶናር ቦይስ መሣሪያ ጥቅም ላይ ውለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የታይታኒክ መርከብ ፍርስራሽ ያረፈው ከደቡባዊ ሴንት ጆን ኒውፋውንድላንድ በ700 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ነው። ይሁን እንጂ የነፍስ ማዳኑ ተልዕኮ እየተካሄደ ያለው ከአሜሪካ ማሳቹሴትስ ቦስተን ነው።

የአሜሪካ የባህር ዳርቻ ጠባቂ እንዳለው ዘ ፖላር ፕሪንስ የተባለችው የምርምር መርከብ የጠፋችውን ሰርጓጅ መርከብ ለመፈለግ ሰኞ ምሽት የባህሩ የላይኛው ክፍል ላይ አሰሳ አድርጋለች።

የጠፋችው ሰርጓጅ መርከብ ባለቤትነቷ የቱሪዝም ድርጅቱ ኦሽንጌትስ እንደሆነ ይታመናል።

የሲቢኤስ ጋዜጠኛው ዴቪድ ፖግ ባለፈው ዓመት ይህንኑ ድርጅት በመጠቀም የታይታኒክ መርከብ ቅሪት ያለበት ቦታ ተጉዞ ነበር።

ጋዜጠኛው ለቢቢሲ እንደተናገረው ረዳት መርከቡ ከሰርጓጅ መርከቡ በቀጥታ ከላይ ሲሆን ሁለቱ መርከቦች የጽሑፍ መልዕክት መለዋወጥ ይችላሉ።

ይህ ካልሆነ ግን ጂፒኤስም ሆነ የራዲዮ መገናኛ ሥርዓት ውሃ ውስጥ ስለማይሰሩ መገናኘት የማይቻል ነው ብሏል።

ፖግ እንዳለው ሰርጓጅ መርከቧ ላይ የተሳፈሩት ሰዎችም ያሉበት መርከብ ዝግ በመሆኑ በራሳቸው ጥረት ማምለጥ ወይም መውጣት አይችሉም።

ሪየር አድም ማውገርም በበኩላቸው ፍለጋው እየተካሄደበት ያለው አካባቢ በጣም ሩቅ በመሆኑ የነፍስ ማዳን ኦፕሬሽኑን አስቸጋሪ እንዳደረገው ተናግረዋል።

ጨምረውም መርከቧ በውሃው ውስጥ በፍጥነት ከእይታ ስለተሰወረች ብርሃንም ባህሩን ሰንጥቆ ሩቅ መጓዝ እንደማይችል አስረድተዋል።

ኦሽንጌትስ ድረ ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ ሦስት የውሃ ውስጥ ሰርጓጆች እንዳሉት ጠቅሶ፣ ቲታን የምትባለው ብቻ የታይታኒክ ቅሪት ወዳለበት ጥልቀት መግባት እንደምትችል ገልጿል።

መርከቧ 10 ሺህ 432 ኪሎ ግራም የምትመዝን ሲሆን እንደ ድረ ገጹ ከሆነም እስከ 13 ሺህ 100 ጫማ ጠልቃ መግባት ትችላለች።

እዚያ ለመድረስም ለስምንት ቀናት ጉዞ እና የታይታኒክ ቅሪት ያለበት 3 ሺህ 800 ሜትር ጥልቀት ድረስ ለመግባት 250 ሺህ ዶላር የቲኬት ዋጋ ያስከፍላል።

ቢሊየነሩ ሃርዲንግ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ፣ “ ወደ ታይታኒክ ለመድረስ እንደሚሳፈርና በዚህም ኩራት እንደተሰማው ገልጾ ነበር።

ጨምሮም በ40 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በኒውፋውንድላንድ በታየው አስከፊ ክረምት ሳቢያ ተልዕኮው የመጀመሪያ ሊሆን እንደሚችል እና በአውሮፓውያኑ 2023 በሰዎች ወደ ታይታኒክ የተደረገ ብቸኛው ጉዞ ነው ብሏል።

ከዚያም በኋላ "የአየር ሁኔታው ተከፍቷል።ነገ ወደ ባህሩ እንጠልቃለን" ሲል ጽፎ ነበር።

ኦሽንጌት ከሰርጓጅ መርከቦቹ መካከል ከአንደኛው ጋር መረጃ መለዋወጥ እንዳልቻለ፣ ነገር ግን ሙሉ ትኩረቱን በተሳፈሩ የቡድኑ አባላት ላይ እና ቤተሰቦቻቸው ላይ እንዳደረገ ገልጿል።

“ ከሰርጓጅ መርከቧ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር በምናደርገው ጥረት ከርካታ የመንግሥት ተቋማትና ጥልቅ ባህር ላይ ከሚሰሩ ድርጅቶች ለተደረገልን ድጋፍ እናመሰግናለን” ብሏል ።

ድርጅቱ ኦሽንጌት ከተለመደው አኗኗር ውጭ ለመውጣትና ያልተለመደ ነገርን ለማየት በሚል ለስምንት ቀናት የሰርጓጅ መርከብ ጉዞ ያዘጋጃል።

ጉዞውን የሚያደርጉ ሰዎችም ከኒውፋውንድላንድ ሴንት ጆርጅ ድረስ በመርከብ የሚጓዙ ሲሆን ወደ መርከቧ ቅሪት ድረስ ሙሉ ለመጥለቅ፣ ለመውጣትና ለመውረድ ስምንት ሰዓታት እንደሚወስድ ተነግሯል።

እንደ ድረ ገጹ ከሆነ አንድ ጉዞ በመካሄድ ላይ ሲሆን ሁለት ጉዞዎች ደግሞ ለሰኔ 2024 ታቅደዋል።

በጊዜው ግዙፍ የነበረው የታይታኒክ መርከብ እንደ አውሮፓውያኑ 1912 ከሳውዝ ሃምፕተን ወደ ኒው ዮርክ ባደረገው የመጀመሪያ ጉዞው ከበረዶ ግግር ጋር ተጋጭቶ በመስጠሙ ከ2 ሺህ 200 መንገደኞችና የጉዞ ቡድን አባላት መካከል ከ1 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑት ሞተዋል።

መርከቡ በ1985 ከተገኘ በኋላም ቅሪቱ በስፋትና በጥልቀት ተጎብኝቷል፤ምርምርም ተካሂዶበታል።

የመርከቡ ፍርስራሽ በሁለት የተከፈለ ሲሆን የፊተኛው አካሉ እና የኋለኛው ክፍሉ በ2 ሺህ 600 ጫማ ተለያይተዋል።

ባለፈው ወር ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው ሙሉ መጠን ያለው ዲጂታል ስካን (ምስል) የተደረገው ጥልቅ የባህር ካርታን በመጠቀም ነበር።

ምስሉ የመርከቡን መጠን እና እንደ መለያ (ሲሪያል) ቁጥር ያሉ የተወሰኑ ዝርዝር መረጃዎችን ያሳያል።