ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሠርጓ ዕለት ተኩስ የከፈተችው ሙሽሪት በፖሊስ እየተፈለገች ነው
በሰሜናዊ ሕንድ ኡታር ፕራዴሽ ግዛት በሠርጓ ሥነ ሥርዓትቷ ላይ ተኩስ የከፈተችው ሙሽሪት በፖሊስ እየተፈለገች ነው።
በማኅበራዊ ሚዲያ የተሰራጫ ቪዲዮ ከባለቤቷ አጠገብ የተቀመጠችው ሙሽሪት አራት ጊዜ ወደ ሰማይ ስትተኩስ ያሳያል።
የአካባቢው ፖሊስ ከዚያ ክስተት በኋላ በተሰወረችው ሴት ላይ ተኩስ በመክፈት ድርጊት የክስ መዝገብ ከፍቷል።
የሠርግ ሥነ ሥርዓትን ለማድመቅ በሰሜናዊ የሕንድ ግዛት ጦር መሳሪያ መተኮስ የተለመደ ክስተት ሲሆን፣ ብዙ ጊዜም በሰዎች ላይ ጉዳት አልፎም ሞትን ያስከትሏል።
በሕንድ ሕግ በቸልተኝነት ወይም የተለያዩ ሥነ ሥርዓቶችን ለማድማቅ በሚል፣ ሌሎችን አደጋ ላይ በሚጥል ሁኔታ የጦር መሳሪያ የሚተኩስ ማንኛውም ሰው ለእስር ሊዳረግ እንደሚችል ተደንግጓል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2016 ጀምሮ በኡታር ፕራዴሽ ግዛት ዋና ከተማ ሉክናው ውስጥ የሠርግ ሥነ ሥርዓትን ለማድመቅ የሚደረግ ተኩስን በተመለከተ ከሳሽ ባይኖር እንኳን ፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንዲከፈት ታዟል።
ኢንዲያን ታይምስ ጋዜጣ እንደገለጸው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሙሽሪት ስትተኩስ የሚያሳየው ቪዲዩ ተቀርጾ የተለቀቀው በዘመዷ ነው።
ይህንንም ተከትሎ ሙሽሪት ሊያጋጥማት የሚችለውን እስር በመፍራት መሰወሯን ፖሊስ ለጋዜጣው ገልጿል።
በሌላ ክስተት ደግሞ ባለፈው ሳምንት የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ ፎቶ ለማድመቅ በሚል ፍንጥቅጣቂ እሳት የሚያወጣ መሳሪያ ለመተኮስ የሞከረች ሙሽራ ፊትቷ ላይ ሲፈናጠር የሚያሳይ ቪዲዩ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ተጋርቶ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
በተለያዩ በዓላት እና ሥነ ሥርዓቶች በተለይ ደግሞ በሠርግ ዝግጅቶች ላይ የጦር መሳሪያዎችን እና የሚፈነዱ ነገሮችን መተኮስ በብዙ አገራት ውስጥ የሚስተዋል ነው።
በዚህም ምክንያት በሚደርሱ ያልታሰቡ አደጋዎች እና ሞቶች ለደስታ የተዘጋጁት ሥነ ሥርዓቶችን ወደ ሐዘን መለወጣቸው በተደጋጋሚ ተዘግቧል።