ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሊቨርፑል ከ አርሰናል፡ 'በውጥረት የተሞላ፣ ትርምስ የታከለበት' ምሽት
በውድድር ዓመቱ እስካሁን ከታዩት ጨዋታዎች የትናንት ምሽቱ ጨዋታ ‘በውጥረት የተሞላ፣ ትርምስ የታከለበት አስጨናቂ’ ጨዋታ ነበር ስትል የቢቢሲዋ የስፖርት ጋዜጠኛ ኤማ ሳንድረስ የሊቨርፑል እና አርሰናል ግጥሚያ ገልጸዋለች።
የትናንት ምሽቱ ጨዋታ የሊቨርፑል እና የአርሰናል ግጥሚያ ብቻ አልነበረም። የሁለቱ ቡድኖች ውጤትን በአንክሮ የሚጠብቁ ሌሎች ክለቦች አሉ።
የሊጉን መሪ የሆኑትን መድፈኖቹን እግር በእግር እየተከተሉ ያሉት ሲቲዎች የአርሰናልን ነጥብ መጣልን በጉጉት ነው የሚጠብቁት። በአውሮፓ ሊግ የመጫወት ዓላማን ሰንቀው እየተፋለሙ ያሉት አስቶን ቪላ እና ብራይተን የሊቨርፑልን ነጥብ መጣል ይናፍቃሉ።
አርሰናል ቀድሞ 2ለ0 መምራት ቢችልም በ87ኛ ደቂቃ በተቆጠረበት ጎል ከሊቨርፑል ጋር አቻ ተለያይቷል። ይህ የክለቦቹን ነጥብ መጣል ለሚመኙ የተመቸ ነው።
ጊዜው ደርሶ ሲጠበቅ የነበረው ጨዋታ ሲጀምር አርሰናል የበላይነት ይዞ በማርቲኔሊ እና በጄሱስ ሁለት ጎሎችን አከታትሎ አስቆጥሮ በአንፊልድ ሊቨርፑልን 2ለ0 በመምራት ታሪክ ሊቀየር ነው ተባለ። አርሰናል በሊጉ ወደ ሊቨርፑል ሜዳ ሄዶ ቀያዮቹን ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈው ከ10 ዓመት በፊት ነበር።
የክሎፕ ልጆች ግን እጅ የሚሰጡ አልነበሩም። ሳላ ከእረፍት በፊት ጎል አስቆጥሮ ቡድኑን ወደ ጨዋታ መለሰ። የመድፈኞችን ልብ የሰበረችውን የአቻነት ጎል የተቆጠረችው በ87ኛው ደቂቃ ነበር። አርሰናል ላይ ጎል ማስቆጠር ልምዱ ያደረገው ሮበርት ፍርሚኒዮ ተቀይሮ ገብቶ ለሊቨርፑል ውድ የሆነች አንድ ነጥብን አስገኝቷል።
ድራማዊ ክስተቶች
ለአርሰናሉ ግብ ጠባቂ አረን ራምስዴል ምስጋና ይሁን እንጂ መድፈኞቹ አንድ ነጥብ እንኳ ከአንፊልድ ይዘው አይመለሱም ነበር። ራምስዴል አስደናቂ የሆኑ ከአንድም ሁለት ኳሶችን በመጨረሻ ደቂቃዎች ከግብ ክልሉ በማራቅ ለቡድኑ ውለታን ውሏል።
ክሎፕ ሳይቀርሩ በግብ ጠባቂው ብቃት መደነቃቸውን አልሸሸጉም። “በመጨረሻ ደቂቃዎች ጨዋታው አስደናቂ ነበር። እነዚያን ዕድሎች አግኝተን እንዴት አላሸነፍንም?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ክሎፕ በውጤቱ አለመደሰታቸውን እንዲሁም አለመከፋታቸውን ገልጸው፤ “አርሰናል ጥሩ ነበር ግን ይህን ጨዋታ ሊሸነፉ ይችሉ ነበር። እንደውም መሸነፍ ነበረባቸው። አንድ ነጥብ ማግኘታቸው ለእነርሱ ጥሩ ነው። ድንገት ይህን በእብደት የተሞላ ጨዋታ መቆጣጠር ችለን ነበር” ብለዋል የሊርፑል አሰልጣኝ ክሎፕ ከጫዋታው በኋላ በሰጡት አስተያየት።
ግራኒት ዣካ እና ትሬንት አሌክሳንደር-አርኖልድ ግብግብ፣ የሊቨርፑል ተከላካይ አንዲ ሮበርትሰን እና ረዳት ዳኛው ፍጥጫ፣ ሁለቱም ቡድን አባላት የተሰጡ 8 ቢጫ ካርዶች የትናንት ምሽቱ ጨዋታ ውጥረት ማሳያዎች ነበሩ።
ሳላ የሳተው ፍጹም ቅጣት ሳይዘነጋ።
"ካየኋቸው ምርጥ ጨዋታዎች መካከል አንዱ ይህ ነው። እያጋነንኩ አይደለም” ሲል የቀድሞ እንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ ሚካህ ሪቻርድ ለስካይ ስፖርት ተናግሯል።
የቢቢሲ ስፖርት አቅራቢያ ሪክ ኤድዋርድስ ደግሞ “የውድድር ዘመኑን ምርጥ ጨዋታ ነው የተመለከትኩት፤ በጨዋታ ጥራት ሳይሆን ባየናቸው ድራማዊ ክስተቶች። አቻ መለያየታቸው ትክክለኛ ውጤት ነው። እንዴት ያለ ትዕይን ነው!”
ሚኬል አርቴታ ደግሞ ቡድናቸው 2ለ0 ሲመራ ቆይቶ 2አቻ ከተለያየ በኋላ ጨዋታው እንዴት ነበር ተብለው ሲጠየቁ “ዋው” ሲሉ መልሰዋል።
“ጨዋታውን በቁጥጥራችን ስር ነበር። ግን የመጀመሪያውን ጎል ካስቆጠሩ በኋላ ጨዋታው መልክ ቀየረ። ከዛ መቆጣጠር አቃተን። . . . ሊቨርፑል ሦስት ወይም አራት ማስቆጠር ይችሉ ነበር። እኛም ተጨማሪ ጎሎችን ማስቆጠር የምንችልበት አጋጣሚ ነበር። ስለዚህ ውጤቱ ፍትሃዊ ነው” ብለዋል አርቴታ።