'አዱኛው' ግማሽ ትሪሊየን የደረሰለት ኤሎን መስክ

ኤሎን መስክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኢሎን መስክ በዓለም የመጀመሪያው ግማሽ ትሪሊየነር ሆኗል

በየቀኑ የዜና ርዕስ የሚሆን ሰው ማን አለ? ከትራምፕ እና ከኤሎን መስክ ሌላ?

ኤሎን እንደ ቢቢሲ ያለ መደበኛ ሚዲያ መውደም አለበት ይላል። መረጃ በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ እና በኢመደበኛ መንገድ መሠራጨት እንዳለበት ያምናል።

ስለዚህም ኤክስን አዘውትሮ ይጠቀማል።

እርሱ ማለት ልክ እያፏጨ እንደሚውል ሰው ነው። 'ትዊት' ሳያደርግ አይውልም። ለነገሩ ንብረቱም አይደል።

ትዊተርን 'ኤክስ' ብሎ ከሰየመው በኋላ እንደ ፌስቡክ 'ተራ' የሐሳብ መጻፊያ ሰሌዳ አይሆንም ብሎ ዝቶ ነበር። ኤክስን ስልክ መደዋወያ፣ አጭር ጽሑፍ መልዕክት መላላኪያ፣ ዜና መክተቢያ፣ 'ምናለሽ ተራ' አደርገዋለሁ እያለ ነው።

ሰውየው ያለውን ከማድረግ አይቆጠብም።ምናልባት የተደናቀፈው ከትራምፕ ጋር መዋል ከጀመረ ወዲህ ይሆናል።

ኤለን መስክ ትራምፕን ለድል ካበቃ በኋላ የማራላጎ እና የዋይት ሐውስ ቤተኛ ሆነ።

ትራምፕ እና ኤለን መስክ ህዋሶቻቸው የተገነቡት ለራሳቸው ካላቸው ከፍ ያለ አመለካከት ነው። ፍቅራቸው እንዴት ይዘልቃል ያሉ ብዙ ነበሩ።

የተፈራው ደረሰ።

ኤለን መስክ ትራምፕን ተዳፈረ። በወሲባዊ ጥቃት ስሙ ከጠለሸው ኢፕስቲን የቅሌት ማኅደር ውስጥ የትራምፕ ስም አለ ብሎ ከባድ የስም ማጥፋት ጉዳት በፕሬዝዳንቱ ላይ አደረሰ።

ዶናልድ ትራምፕ ያን ሰሞን ያለ ወትሯቸው ዝምታን መርጠው ነበር። ምናልባት ነገሩ እንዳይባባስ ፈርተው ይሆናል። ምናልባት እንደሚባለውም የቅሌት መዝገቡ ላይ ስማቸው ይኖር ይሆናል።

ወደ ኤለን መስክ እንመለስ።

እሱ በፊታውራሪነት ይምራው የተባለው ''የቢሮክራሲ ማሳለጫ ባለሥልጣን" ዶጅ (Doge) መጨረሻው አላማረም።

ያድናል የተባለውን ቢሊዮን ዶላሮችን ቃል በተገባው መጠን አላዳነም። በመላው ዓለም የሚሊዮኖችን ጉሮሮ ግን ዘግቷል።

ከኤለን መስክ ስንብት ወዲህ ስለ 'ዶጅ' ብዙ አይወራም።

እሱ በዚህ መሥሪያ ቤት ስሙ ከፍ እያለ ሲሄድ የኤሎን ኩባንያዎች ገቢ ዝቅ እያለ ሄዷል።

በተለይ ቴስላ ቁልቁለቱን ተያይዞት ነበር። እርሱ ሥራ ያስለቀቃቸው ዜጎች ቂማቸውን የተወጡት ቴስላ መኪና ላይ እሳት በመልቀቅ ነበር።

ማወዛገብ የሚወደው ኤሎን

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኤሎን አሜሪካዊ የሆነው በ2002 ነበር።

ያኔ ምንድነህ ሲባል "ግማሽ ዲሞክራት፣ ግማሽ ሪፐብሊካን" ይል ነበር።

ድሮ ለባራክ ኦባማ እና ለሂላሪ ክሊንተን ድምጽ መስጠቱን እያመነታም ቢሆን አምኗ፤ ለጆ ባይደን ጭምር።

ከዚያ ግን ድንገት ዲሞክራቶችን ጠላ። በተለይ ዲሞክራቶች በስደተኞች ላይ ያላቸው መለሳለስ አስቆጣው።

ዶናልድ ትራምፕ ጋር ተጣበቀ።ከዚያም ተላቀቀ።

ከትራምፕ ጋር ሆድ እና ጀርባ ከሆኑ ወዲህ ኤሎን መስክ አዲስ የ'ትዊተር' ፓርቲ እስከመፍጠር ደርሶ ነበር።

ትራምፕ ካስቀየሙት በኋላ፣ በመዳረሻ ምርጫ 'ሪፐብሊካኖችን' ለመበቀል ዝቶም ነበር።ያደርገዋል-አያደርገውም በቀጣይ የምናየው ይሆናል።

አሁንም ግን በስደተኞች ጉዳይ የትራምፕ ቀንደኛ ደጋፊ ነው።

የኤሎን መስክ ወላጆች ከደቡብ አፍሪካው የአፓርታይድ ሥርዓት ያተረፉ ናቸው። በተለይ አባቱ በቀድሞ ዘመን በዝባዥ እንደነበሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የባህሪ ውርስ በሚመስል ሁኔታ እሱም በመላው ዓለም አክራሪ ብሔርተኞችን 'ግፋበለው' በማለት ይታወቃል።

የጀርመን መጤ ጠል ፓርቲን (ኤኤፍዲ) በሚችለው ሁሉ ያግዛል።

በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የጠቅላይ ሚኒስተር ኪር ስታመር ቀንደኛ ተቺ ነው። ሰውየው 'ለመጤዎች' ልስሉስ ናቸው እያለ ቀን ተሌት ይዘልፋቸዋል።

ድምጽ ለማግኘት ሲሉ በጅምላ በመጤ ፓኪስታናዊያን የተፈጸመን የመድፈር ወንጀል ምርመራ እንዳይደረግ ሸፋፍነዋል እያለ ይከሳቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ስታመር በበኩላቸው ኤለን መስክ ስሜን ያጠለሻል፤በማያገባው ይገባል ይሉታል።

ያም ሆኖ በዩኬ እና በጀርመን በተሠራ የዳሰሳ ጥናት 71 ከመቶ የሚሆነው ሕዝብ ስለ ኤሎን መስክ በጎ አመለካከት እንደሌለው አረጋግጧል።

ያም ሆኖ እጁ ረዥም ነው። በአውሮፓ አገራት ተራው ሕዝብ ላይ የሚያደርሰው ተጽእኖ ጥልቅና ጥብቅ ነው። በተለይ ነጭ አክራሪ ብሔርተኞችን ወደፊት እያመጣቸው፣ ወንበርም እያስያዛቸው ነው።

ኤለን መስክ የነጭ ዘር የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል ብሎ ያስባል።ነጮች ''ብዙ ተባዙ-ምድርንም ሙሏት'' እያለ ይሰብካል።

አርአያ ለመሆን ይመስላል እርሱ ራሱ ከተለያዩ ሴቶች 14 ልጆችን አፍርቷል። ይሄ ታዲያ በይፋ የሚታወቀው ነው።ቁጥሩ ከዚህም ሊልቅ ይችላል።

የት ነው የተወለደው?

ኤሎን መስክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኤሎን መስክ 2004 ዓመተ ምሕረት

በደቡብ አፍሪካ፣ ፕሪቶሪያ ነው የተወለደው። ገና 12 ዓመት ሳይሞላው ቤት ውስጥ የተሠራ ቼኮሌት በየቤቱ እያዞረ ንግድ ቢጤ ሞካክሯል።

ጎረምሳ ሳይሆን ገና አንዳች የኮምፒውተር ጌም ፈጥሮ ነበር።

ኤሎን መስክ ልጅነቱ በቀውስ የተተበተበ ነበር፤ በሁለት ምክንያት።

አንደኛ አባቱ ሞገደኛ ነበሩ። ከእናቱ ጋር ፍቺ ከፈጸሙ ወዲህ ደግሞ ከኤሎን ጋር ጥሩ ግንኙነት አልነበራቸውም።

ሁለተኛ ኤሎን በትምህርት ቤት በ'ዱርዬ' ተማሪዎች ብዙ ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ይደርስበት ነበር። ለዚህ አንዱ ምክንያት ኤሎን የዕድገት ውስንነት (ኦቲዝም) ተጠቂ ስለነበረ ነው።

እሱ ያለበት ችግር በሕክምና ቋንቋ አስፔረገስ ሲንድረም (Asperger's Syndrome) ይባላል። በዋናነት መቅበዝበዝ፣ የዓይን ብሌኖች መንከራተት፣ ማኅበራዊ ተሳትፎ ላይ መስነፍ፣ ከሰው ጋር ቀና ተግባቦት ለማድረግ መቸገር ይስተዋልበታል።

ምናልባት ከጋዜጠኞች ጋር ሲገናኝ ለጸብ የተቃረበ ቃለ ምልልስ የሚያደርገው በዚህ ባህሪው የተነሳ ይሆናል።

በአንድ ወቅት የኤክስ ማስታወቂያ አስነጋሪዎች አድመውበት "ሲፈልጉ እንጦሮጦስ ይውረዱ" የሚል ጸያፍ ቃል ጭምር ያለበት ምላሽ ሰጥቶ ነበር።

ወደ ወጣትነቱ እንመለስ፡

ኤሎን ከሞገደኛ አባቱ ጋር መግባባት ሲሳነው ደቡብ አፍሪካን ለቀቀ። ለኮሌጅ ትምህርት ካናዳ ተሻገረ። እናቱ ካናዳዊት ናት።

ካናዳ ብዙም ሳይቆይ ወደ አሜሪካ ተሻገረ። ከዚያ ፔንሴልቬኒያ ዩኒቨርስቲ ተመዘገበ። ፊዚክስ እና ኢኮኖሚክስ አጠና።

ኮሌጅ ሳለ ያገኛት የመጀመሪያ ሚስቱ ጀስቲን እንደመሰከረችው፣ ኤሎን መስክ ሚሊዮነር ከመሆኑ በፊትም ቢሆን ''አይሆንም'' የሚል መልስ የሚቀበል ገራገር ሰው አልነበረም።

እርሷ ስለርሱ ከተናገረችው የሚጠቀስላት አንድ ነገር አለ። "ኤሎን እኮ ገና በሰርጋችን ቀን ተቃቅፈን እየደነስን ሳለ 'እኔ ነኝ ንጉሥሽ'፣ ያለኝ ሰው ነው" ትላለች።

በሌላ ቋንቋ 'ያንቺ ድርሻ እኔን መታዘዝ ይሆናል' እያላት ነበር።

ሃብት ያካበተው እንዴት ነው?

ኤሎን መስክ በፊዚክስ የድኅረ ምረቃ መርኅ ግብር ስታንፈርድ ዩኒቨርሰቲ አመለከተ። ተቀበሉት።

ትምህርቱን እንደጀመረ ግን ወዲያው ጥሎት ወጣ። አቋረጠ። ከዚያ ሁለት የቴክኖሎጂ ጅምር ኩባንያዎችን መሠረተ። ይሄ በአውሮፓውያኑ 90ዎቹ አካባቢ የሆነ ነው።

አንዱ ሙከራው የሶፍትዌር ኩባንያ ነበር። ከባንክ ክፍያዎች ጋር የተያያዘ ይህ የሶፍትዌር ኩባንያ በኋላ ፔይፓል (PayPal) የሆነው ነው።

መርጋት ያልፈጠረበት ኤሎን ብዙም ሳይቆይ አውሮፓውያኑ 2002 ይህን ድርጅቱን ለኢቤይ (eBay) በአንድ ሚሊዮን ተኩል ዶላር ሸጠው።

ብሩን ይዞ የሮኬት ካምፓኒ ከፈተ። ስፔስ ኤክስ አለው። ይህ ድርጅት ናሳ ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣበትን የህዋ ጉዞ፣ በርካሽ የህዋ ታክሲ መቀየር ነበር። ተሳካለት።

ከዚያ የኤሌክትሪክ መኪና ኩባንያ ቴስላን ጀመረ። በዚህም በጣም ተሳካለት። ዘለግ ላለ ጊዜ የቦርድ ሊቀመንበር ነበር። በ2008 ደግሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሆኖ ተሾመ።

2022 ደግሞ ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር ገዛ። መግዛቱ ሳይሆን ይበልጥ አነጋጋሪ የነበረው ሠራተኞች ቅነሳ ላይ ያሳየው ቆራጥ ውሳኔ ነበር።

ቁልፍ የሚባሉ የሶፍትዌር እና ደኅንነት መሐንዲሶችን ብቻ በማስቀረት የድርጅቱን ብዙዎቹን ሠራተኞች አባረረ። ይህ ክስተት በእንግሊዝኛው ገላጭ ቃል ወጥቶለታል፤ ታላቁ ፍልሰት (The great X-odus) ይሉታል።

አሁን ስሙ ኤክስ የሆነው ይህ ድርጅት 'ሁሉን መተግበሪያ' ይሆናል ቢባልም የዋጋ ተመኑ ክፉኛ ወርዷል። 44 ቢሊዮን ዶላር የተገዛው ይህ ድርጅት አሁን ለገበያ ቢወጣ 10 ቢሊዮንም አያወጣም።

ኤሎን መስክ ኤክስን ከገዛው ወዲህ መድረኩ የጥላቻ ንግግሮች 'ድንጋይ መወራወሪያ ሰፈር' ሆኗል በሚል ይተቻል።

እሱን የሚያውቁት ምን ይላሉ?

ህልሙ አይጨበጥም ይሉታል። ፍላጎቱ ገደብ የለውም ይሉታል። ንቀት አለበት ይሉታል።

ያልተሞከረ ነገር መሞከር ያስፈነድቀዋል ይሉታል። ወደ ሰው ጭንቅላት ስልክ ውስጥ የምትገባ ዓይነት ደቃቅ 'ቺፕስ' በመክተት ቴክኖሎጂ እና የሰው አእምሮን ማጋባት የሚፈልግ ሰው ነው።

ነገሩን ጀምሮታል። ይህን የሚሠራው ድርጅቱ ኒውሮሊንክ ይባላል።በዚህ ሰዓት ሦስት ታካሚዎች ይህ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ጭንቅላት ይዘዋል። ሳይንሳዊ ልቦለድ የሚመስል ነገር ነው።

ሰዎች እግር እና እጅ በአደጋ አጡ እንበል። አርቴፊሻል ይገጠምላቸው እና እንደልባቸው ይራመዳሉ። ይጽፋሉ፣ ይበላሉ ይጨፍራሉ፤ ነገሩን ገና ሲያስቡት ኮምፒወተር ጭንቅላታቸው ላይ የተገጠመው ደቂቅ ቺፕስ ያግዛቸዋል።

ኤሎን መስክን በቅርብ የሚያውቁት እና አብረውት የሠሩ ሰዎች ስለርሱ ብዙ ብለዋል።

ጋዜጠኛ ክሪስ ስቶክልዎከር እንዲህ ይላል፤ "ኤሎን በትክክል ነገ ምን ማድረግ እንደሚፈልግ ያውቃል ብዬ ለማመን እቸገራለሁ፤ ብዙ ውሳኔዎቹ በዚያ ቅጽበት በግብታዊነት የሚፈጸሙ ናቸው።"

የግለ ታሪክ ፀሐፊው አሽሊ ቫነስ ደግሞ ስለ ኤሎን ይህን ይላል፣ "መጋፈጥ የሚወድ፣ ሁሉን አዋቂ ነኝ የሚል፣ የበዛ የራስ መተማመን እና ለራሱ የተጋነነ ግምት የሚሰጥ፣ ወለፈንዲ ዳንስ ያለው፣ አይናፋር የመድረክ ተናጋሪ..."

ሌሎች ደግሞ ባለ ምጡቅ አእምሮ እንደሆነ ይመሰክራሉ።

አግብቶ መፍታት እና አብዝቶ መውለድ

ኤሎን እስከ ዛሬ ሦስት ጊዜ አግብቶ ፈቷል። እንግሊዛዊቷን ተዋናይት ታሉላ ራይሊን አግብቶ ፈታት እና ደግሞ አግብቶ ፈትቷታል።አንዳንዴ ትንሽ እንደ እብደት እንደሚቃጣው እሱም ያምናል።

"ወንጀሎቼ በአንድ ማኅደር ቢዘረዘሩ በምድር ላይ መጥፎው ሰው እኔ እሆናለሁ" ብሎ ነበር ቴድቶክ ላይ ከሦስት ዓመት በፊት።

ቀጠለና ግን እንዲህ አለ፡ "ነገር ግን ከጥፋቶቼ ትይዩ ትክክል ያደረኳቸውን ብትዘረዝሩ፣ የበለጠ ስሜት የሚሰጥ ነገር ታገኛላችሁ።"

እሱ ባመነው አጠቃላይ የልጆቹ ቁጥር 14 ደርሷል።

ሃብቱ ስንት ደረሰ? የመጀመሪያው ትሪሊየነር?

የቢሊየነሮችን ንብረት እየሰነደ ደረጃ የሚያወጣው ብሎምበርግ እንደሚለው በሃብት ኤሎን ከቢሊየነሮች ሁሉ ቁንጮው ነው።

አሁን ለጊዜው ጠቅላላ ሃብቱ 500 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሆነ የመጀመርያው ሰው ሆኗል።

ኢሎን መስክ በዓለም የመጀመሪያው ግማሽ ትሪሊየነር ሆኗል።

ይህ አሃዝ በዋናነት ከቴስላ ያካበተው ነው። ዛሬ ላይ በቴስላ ኩባንያ 13 በመቶ ድርሻ አለው።

በትንንሽ የዲጂታል ግብይት ኩባንያዎችም ድርሻ ይይዛል።ለርሱ ነው ትንንሽ።

ቦሪንግ የሚባል ኩባንያ ውስጥም እጁ አለበት። ይህ ኩባንያ የአሜሪካ ትራንስፖርትን ለማዘመን የተነሳ ነው። በዚህ ኩባንያ ሥር ምድር ለምድር የሚሽሎኮሎክ የባቡር መንገድ ለመፍጠር እየተሞከረ ነው።

ሉፕ (loop) የሚባለው የምድር ውስጥ ትራንስፖርት እጅግ ፈጣን፣ ከብክለት ነጻ የሆነ እና ከመነሻ እስከ መድረሻ ወደ ምድር ወለል ብቅ የማይል የባቡር መኪና ነው።

የሥራ ሱሰኛ እንደሆነ የሚነገርለት መስክ "እኔ ኩባንያዎችን የምፈጥረው ገንዘብ ስለሚያስገኙልኝ ብቻ አይደለም" ይላል።

"ለሰው ልጅ የሚጠቅም ከመሰለው ወደኋላ አይልም" ሲሉ በቴስላ ኢንቨስተር እና የእርሱ ወዳጅ ሮስ ገርበር ይመሰክራሉ።

ኤሎን መስክ መሬት እየማሰ፣ ሰማይ እያረሰ፣ ሃብት እያጋበሰ ቀጥሏል። የሰው ልጅ ማርስን መቆጣጠሩ ቢዘገይ እንጂ አይቀርም ብሎ ያምናል።

የኤለን ሃብት በመጪዎቹ ዓመታት በዚሁ ከቀጠለ ምናልባት የዓለማችን የመጀመሪያው ትሪሊየነር ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

የቴስላ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆነው ኤሎን መስክ ኩባንያው የያዛቸውን ዕቅዶች ካሳካ የአንድ ትሪሊየን ዶላር የጉርሻ እንደሚያገኝ የኩባንያው ቦርድ አስታውቋል።