ቴስላ፤ ኢሎን መስክ እቅዱን ካሳካ የአንድ ትሪሊዮን ዶላር ሽልማት እንደሚሰጥ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቴስላ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢሎን መስክ በሚቀጥለው አስር ዓመታት እቅዶቹን ከግብ ካደረሰ የአንድ ትሪሊዮን ዶላር የጉርሻ ማዕቀፍ እንደሚሸልም የኩባንያው ቦርድ አስታውቋል።
የዓለማችን ባለሀብት የሆነው መስክ ሽልማቱን ለማግኘት የቴስላን የኩባንያ ዋጋ በስምንት እጥፍ ማሳደግ፣ አንድ ሚሊዮን የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሮቦቶችን መሸጥ፣ ተጨማሪ 12 ሚሊዮን የቴስላ ተሽከርካሪዎችን መሸጥ እንዲሁም ሌሎችንም ከባድ ግቦች ማሳካት አለበት።
መስክ በቀጥታ ደሞዝ አሊያም ጉርሻ የማያገኝ ሲሆን፤ ይልቁንም ግቡን ካሳካ ቀስ በቀስ አንድ ትሪሊዮን ዶላር የሚያወጡ ድርሻዎችን እንደሚሸለም ተነግሯል።
የኩባንያው ቦርድ ነዋይ አፍሳሾች ይህን የሽልማት ማዕቀፍ ደግፈው ድምፅ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሮበን ዴንሆልም "ዛሬ የማይታሰብ የሚመስል እድገት በአዲስ ሀሳብ፣ በተሻለ ቴክኖሎጂ እና በግሩም ፈጠራ እውን ይሆናል" ብለዋል።
"በቀላል አነጋገር ኢሎንን ማበረታታት ቴስላ እነዚህን ግቦች ለማሳካት እና በታሪክ ትልቅ ዋጋ ያለው ኩባንያ ለመሆን መሰረታዊ ነው" ሲሉም አክለዋል።
ሰብሳቢዋ አክለውም ለኢሎን መስክ የሚሸለመው ድርሻ "ለባለራዕዩ መሪያችን አፈፃፀሙን ጫፍ ላይ ያደርሳል" ብለዋል።
ይህ ዜና የተሰማው መስክ ቃል ተገብቶለት የነበረው 50 ቢሊዮን ዶላር ሽልማት በፍርድ ቤት ለባለድርሻዎች ፍትኃዊ አይደለም በሚል ውድቅ ከተደረገበት እና 29 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ድርሻ በተሸለመ ማግስት ነው።
በቅርቡ በወጣው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራቹ ቴስላ የሽያጭ ሪፖርት መሰረት በአስር ዓመት ውስጥ ሽያጩ ያሽቆለቆለ ሲሆን፤ የገበያ ባለሙያዎች ጉዳዩን ከኢሎን መስክ "መርዛማ" ዝና ጋር አያይዘውታል።
የቴስላ ቦርድ ያልተጠበቀ ሽልማት ያስታወቀው መስክን ለመተካት እያማተረ ነው የሚል ሪፖርትን ካስተባበለ ከወራት በኋላ ነው።
ባለፈው ግንቦት ዌል ስትሪት ጆርናል ባወጣው እና ቴስላ "ፍፁም ስህተት" ባለው ሪፖርት የኩባንያው ቦርድ መስክ ከቴስላ እያሽቆለቆለ ካለው የገበያ ድርሻ ይልቅ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ባለው ሥራ አተኩሯል በሚል ለመተካት መልማይ መቁጠሩን ገልጿል።















