ኢሎን መስክ የዓለም የመጀመሪያው ግማሽ ትሪሊየነር ሆነ

ኢሎን መስክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢሎን መስክ በዓለም የመጀመሪያው ግማሽ ትሪሊየነር ሆኗል።

አንጡራ ሃብቱ ከ500 ቢሊዮን ዶላር በላይ በመሆን የመጀሪያው ሰው ነው።

የመስክ የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ድርጅት ተስላ እንዲሁም ሌሎቹም ተቋሞቹ በያዝነው ዓመት ትርፋማነታቸው ጨምሯል።

ትናንት መስከረም 21/2018 ዓ. ም. የመስክ ሃብት 500.1 ቢሊዮን ደርሷል። የፎርብስ የቢልየነሮች ዝርዝር እንደሚያሳየው፣ አምና የመስክ ሃብት 499 ቢሊዮን ዶላር ነበር።

ባለፉት ጥቂት ወራት፤ የመስክ አዲስ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ተቋም ኤክስኤአይ፣ ሮኬት አምራች ድርጅቱ ስፔስኤክስ እንዲሁም ተስላ ገቢያቸው ከመቼውም በላይ መናሩ ተገልጿል።

መስክ ግማሽ ትሪሊየነር የሆነው በቴክኖሎጂው ዘርፍ የሚፎካከሩትን ባለሃብቶች በመብለጥ ነው።

በፎርብስ የቢልየነሮች ዝርዝር መረጃ መሠረት የኦራክል መስራች ላሪ ኤልሰን ሃብቱ ወደ 350.7 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሲሆን፣ የዓለም ሁለተኛው ቱጃር ነው።

ባለፈው ወር የኦራክል የገበያ ድርሻ ከ40% መብለጡን ተከትሎ የኤልሰን ሃብት ከመስክ በጥቂቱ የላቀ ነበር።

ኦራክል የገበያ ድርሻው ከፍ ያለው አዲስ የክላውድ አሠራር በመዘርጋቱና የሰው ሠራሽ አስተውሎት አቅርቦት ስምምነቶች በመፈረሙ ነው።

መስክ በተስላ ያለው ድርሻ 12% ሲሆን በያዝነው ዓመት የድርሻው መጠን መጨመሩ ተዘግቧል።

ኢሎን መስክ ከፖለቲካው ይልቅ ለተስላ ትኩረት መስጠት መጀመሩን ተከትሎ ኢንቨስተሮች በድርጅቱ ያላቸው እምነት ከፍ በማለቱ ትርፋማነቱም ጨምሯል።

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወጭ ቆጣቢ ተቋም (ዶጅ) ውስጥ መስክ ይጫወት የነበረው ሚና ሲያስተቸው ቆይቷል።

የኤክስ ባለቤት የሆነው መስክ ከስደተኞች ጉዳይ ጋር በተያያዘ ባንፀባረቀው አቋም ውዝግብ መነሳቱ አይዘነጋም።

መስክ፤ ፆታ እና ዘርን መሠረት ያደረገ መድልዎን ለመግታት የተዘረጋውን የእኩልነት መርሃ ግብር (DEI) መቃወሙም ሌላው የውዝግብ መነሻ ነው።

ከፖለቲካ ራሱን ማግለሉን የገለጸው መስክ ትኩረቱን ወደ ተስማ ማድረጉን የኩባንያው የቦርድ ኃላፊ ሮቢን ደንሆልም ተናግረዋል።

በቀጣይ አሥርት ዓመታት መስክ ዕቅዱን ካሳካ ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያገኝ የተስላ ቦርድ ጠቁሟል።

መስክ ውጥኑን ከግብ ለማድረስ አንድ ሚሊዮን ሮቦቶች እና 12 ሚሊዮን የኤሌክትሪክ መኪናዎች መሸጥ ይጠበቅበታል።

ባለፈው ወር አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የተስላ ድርሻ መግዛቱን ይፋ አድርጓል። ይህም በተቋሙ ላይ ያለውን ጠንካራ እምነት ያሳያል ተብሏል።

ተስላ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ፈተናዎች ገጥመውታል። ከቻይናው የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ቢዋይዲ የገጠመው ፉክክር ዋነኛው ነው።

ድርጅቱ ወደ ሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ሮቦቲክስ ዘርፍ ለመግባት በሂደት ላይ ይገኛል።