ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቢቢሲ ከዓለማችን እጅግ ኃያል ሰው ጋር ከባድ የሕግ ፍልሚያ ገጥሞታል፤ ቀጥሎ ምን ይሆናል?
ቢቢሲ ለዶናልድ ትራምፕ ያቀረበው ይቅርታ የክስ ዛቻውን የሚያስቆም እንደሆነ የሚያስብ ማንኛውም ሰው በግልጽ ተታልሏል።
የቢቢሲ ቦርድ ሊቀመንበር ሳሚር ሻህ ዋና ዳይሬክተሩ እና የኒውስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ከሥልጣን ከተነሱ በኋላ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ጠቅለል አድርገውታል። ፕሬዝዳንቱን "የክስ ዶሴ ይዘው ወደ ፍርድ ቤት መሄድ የሚመርጡ" ሲሉ ጠርተዋቸዋል።
ትራምፕ በተለያዩ የአሜሪካ የሚዲያ ኩባንያዎች ላይ ያቀረቧቸው የሕግ ክሶች ብዛት ለተመለከተ ይህ የሊቀ መንበሩ ገለጻ ጠቅለል ያለ መግለጫ ነው።
ፕሬዝዳንቱ፣ በጂቢ ኒውስ ቃለ ምልልሳቸው ላይ በመመስረት፣ "አስከፊ" አርትዖት አድርገው በሚመለከቱት በግልጽ ተጎድተዋል፤ እና አሁን ኮርፖሬሽኑን የሚከሱበት የገንዘብ መጠን ከፍ ብሏል።
ትራምፕ አርብ ዕለት በኤር ፎርስ ዋን ላይ እያሉ፣ ለጋዜጠኞች የተናገሩት አሃዝ "ከ1 ቢሊዮን ዶላር እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር" እንደሚሆን ነው።
ይህንን በአውድ ለማስቀመጥ፣ ቢቢሲ ባለፈው ዓመት ከፈቃድ ክፍያ ያገኘው ዓመታዊ ገቢ 3.8 ቢሊዮን ፓውንድ ነበር።
ትራምፕ አርብ ዕለት ትራምፕ "ከአፌ የሚወጡትን ቃላት ቀይረዋል" ሲሉ ተናግረው፣ ፓኖራማ የንግግሩን ሁለት ክሊፖች "ፍጹም የተለየ ትርጉም" ለመስጠት ለምን አንድ ላይ ቆርጠው እንደቀጠሉ ማወቅ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ የተከሰተው ነገር ሆን ተብሎ እንዳልሆነ የተሰጠውን የቢቢሲ ምላሽ አይቀበሉም።
ይህ በቢቢሲ ታሪክ ውስጥ በጣም ከባድ ወቅት ነው። ቢቢሲ ስሙን የገነባው ገለልተኛ የዜና ተቋም በመሆን ነው፤ በዓለም ላይ ተቋማትን ማመን በተሸረሸረበት ዘመን ታማኝ የዜና ምንጭ በመሆን ስሙን ተክሏል።
በምትኩ ኮርፖሬሽኑ ከታማኝነት በተቃራኒው የቆመ ነው ተብሎ ተወነጀለ፤ እና በዓለም ላይ ካሉት ኃያላን ሰዎች ጋር ውድ የሆነ የፍርድ ቤት ክስ ተጋርጦበታል።
ታዲህ ነገሩ ከዚህ ወዴት ሊያመራ ይችላል?
ፕሬዝዳንቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ጉዳዩን ወደ ሕግ ለመውሰድ ካስፈራሩበት ወቅት ጀምሮ፣ ኮርፖሬሽኑ ካሳ ሊከፍላቸው እንዳልፈለገ ግልጽ ነበር። ምንም ዓይነት ስህተት ቢፈጠር፣ በፓኖራማ ፕሮግራም ሳቢያ በትራምፕ ላይ ምንም ጉዳት እንዳልደረሰ ያምናል።
ትራምፕ ፕሮግራሙ ከተላለፈ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡ የተመጡ መሆን እና ቢቢሲ እንደሚለው ፕሮግራሙ በማንኛውም የአሜሪካ ቻናሎች ላይ አልተላለፈም። ታዲያ ይህ እንዴት ሊጎዳው ቻለ?
ከቢቢሲ ውጭም ያሉ ሆኑ የድርጅቱ ተቀጣሪዎች የሚስማሙበት ከዜጎች የተሰበሰበን የአገልግሎት ክፍያ ገንዘብ ለትራምፕ ክስ በካሳ መልክ መክፈል አማራጭ አይደለም።
አንድ የቀድሞ የቢቢሲ ከፍተኛ ኃላፊ እንደገለጹት ቢቢሲ የካሳውን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ "ትክክለኛው እርምጃ ነው"።
ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ ክስ ለመመስረት ከወሰኑ ቢቢሲ "በፍሎሪዳ ውስጥ ምርጥ ጠበቆችን ማግኘት" እንዳለበት ተናግረዋል።
ጉዳዩን በስምምነት መጨረስ የሚለው አማራጭ የሚያገለግለው በረዥም ጊዜ የሚወጣን ወጪ ለመቀነስ ነው።
አሁን ቢቢሲ ሙሉ ትኩረቱን በቻርተሩ እድሳት ላይ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ትኩረት ማድረግ በሚገባው በዚህ ጊዜ ረጅምና ውድ በሆነ የፍርድ ቤት ክርክር ውስጥ የሚያልፍ ይመስላል።
የቢቢሲ ከፍተኛ ሹማምንት በአሁኑ ወቅት ለድርጅቱ ወሳኝ የሆነው ጉዳይ ላይ፣ እአአ በ2028 ከሚጀምረው አዲሱ ቻርተር በፊት፣ በመንግሥት እና በቢቢሲ መካከል ዓላማው፣ ስፋቱ፣ የገንዘብ ምንጩ ላይ በሚደረጉ መጻዒ ዕድሉን በሚመለከቱ ንግግሮች ላይ ማተኮር ነበረባቸው።
ቢቢሲ ይህንን ሊመሩ የሚገባቸውን ሰው ዋና ዳይሬክተሩን ቲም ዴቪን አጥቷል።
አሁን ከፍተኛ የቢቢሲ ኃላፊዎች ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በጣም ጎጂ እና የኅልውና ጉዳይ በሆነው የሕግ ጉዳይ ላይ ይጠመዳሉ። የሕግ ክፍያዎች ብቻ በጣም ውድ ሊሆኑ ይችላሉ።
ቢቢሲ ስህተቱን ቀደም ብሎ ግልጽ አድርጎ ቢያርመው ኖሮ ይህ ሁሉ ሊወገድ ይችል ነበር። በምትኩ ረጅም መንገድን መርጧል።
ነገር ግን ሌላ አማራጭ መንገዶች ሊኖሩ ይችላሉ።
ቢቢሲ የዩኬ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ሊጠይቅ ይችላል? ከጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር የሚላክ መልዕክት የትራምፕ ሀሳብን ሊያስቀይር ይችላል? ስታርመር ጣልቃ ገብተው ያላቸውን ተዐዕዕኖ አሜሪካ ላይ መጠቀም ይፈልጉ ይሆን?
በዚህ ሳምንት ለቢቢሲ አንድ አዎንታዊ ነገር የባህል ሚኒስትሯ ሊሳ ናንዲ ኮርፖሬሽኑን የተከላከሉበት ጠንካራ መንገድ ነው።
በርካታ ሰዎች ተቋሙ ላይ ያላቸውን እምነት ገልፀው፣ ቢቢሲን "በጨለማው ዘመን በተራራው ጫፍ የነበረ ብርሃን" ብለውታል፤ አክለውም አገሪቱን 'ሴሌብሪቱ ትሬተርስ' በሚለው ዝግጅቱ ወይንም ቪኢ ዴይ ላይ በሚሰጠው ሽፋን ወደ አንድነት የሚያመጣ ሲሉ አሞካሽተውታል።
ዶናልድ ትራምፕ በሌላ በኩል ቢቢሲን "ከሐሰት ዜና የከፋ" ሲሉ ጠርተውታል። ኮርፖሬሽኑ እና ጋዜጠኞቹ ምግባረ ብልሹ ናቸው ብለዋል።
በትራምፕ እና በቢቢሲ መካከል ያለው ፍጥጫ እና ፍትጊያ አሁን በይፋ ተጀምሯል።