ትራምፕ ለሦስተኛ ጊዜ ፕሬዝደንት ይሆናሉ?

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ለሦስተኛ ጊዜ መመረጥ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

"እየቀለድኩ አይደለም። ለሦስተኛ ጊዜ ፕሬዝደንት መሆን ነው የምፈልገው" ብለዋል።

የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ማንም ሰው ከሁለት ጊዜ በላይ ፕሬዝደንት ሆኖ መመረጥ እንደማይችል ይደነግጋል።

የትራምፕ ደጋፊዎች ግን እንዴት የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ መተላለፍ እንደሚቻል እያሰቡ ነው።

ትራምፕ ከኤንቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ "ለሦስተኛ ጊዜ ፕሬዝደንት ለመሆን የሚቻልባቸው መንገዶች አሉ" ብለዋል።

"እየቀለድኩ አይደለም። በርካቶች ለሦስተኛ ጊዜ እንድመራ ይፈልጋሉ። እዛ ለመድረስ ብዙ ይቀረናል እላቸዋለሁ። አስተዳደሩ ገና እየጀመረ ነው" ሲሉም ትራምፕ አክለዋል።

ትራምፕ ሁለተኛውን የሥልጣን ዘመን ሲያጠናቅቁ 82 ዓመት ይሞላቸዋል።

ከዚያ በኋላም በአገሪቱ ከባድ የሆነውን ሥራ መቀጠል ይፈልጋሉ? ተብለው ሲጠየቁ።

"እንግዲህ መሥራት እወዳለሁ" ብለው መልሰዋል።

ትራምፕ ለሦስተኛ ጊዜ ፕሬዝደንት ስለመሆን ሲናገሩ የመጀመሪያቸው አይደለም።

"አንዴ ብቻ ሳይሆን፣ ሁለቴም፣ ሦስቴም፣ አራቴም ባገለግል ታላቅ ኩራት ይሰማኛል" ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።

ይህንን ካሉ በኋላ ደግሞ ነገሩ ቀልድ እንደሆነና "ለሐሰተኛ መገናኛ ብዙኃን" ሲሉ የተናገሩት መሆኑን ገልጸዋል።

የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ምን ይላል?

የአሜሪካ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 22 ላይ "ማንም ሰው ከሁለት ጊዜ በላይ ፕሬዝደንት ሆኖ መመረጥ አይችልም። ከሥልጣን ዘመኑ ውስጥ ከሁለት ዓመታት በላይ ፕሬዝደንት የሆነ ወይም ፕሬዝደንት ሆኖ ያገለገለ ከአንድ ጊዜ በላይ መመረጥ ይችላል" ይላል።

ሕገ መንግሥቱን ለመለወጥ በሴኔትና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ሦስተኛ ድምጽ መገኘት አለበት።

በአገሪቱ ጃሉ ግዛቶች ሦስት እጅ የሚሆኑትም ይሁንታ መስጠት ይኖርባቸዋል።

የትራምፕ ሪፐብሊካን ፓርቲ ሁለቱንም የኮንግረስ አካላት ይቆጣጠራል። የሚፈለገው አብላጫ ቁጥር ግን የላቸውም።

ዴሞክራቶች ከግዛቶች 50 ሕግ አውጪዎች መካከል 18ቱን ይቆጣጠራሉ።

ትራምፕ እንዴት ለሦስተኛ ጊዜ ፕሬዝደንት ይሆናሉ?

የትራምፕ ደጋፊዎች በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ክፍተት እንዳለ ይናገራሉ።

22ኛው አንቀጽ በግልጽ ያስቀመጠው አንድ ሰው ለሁለት ጊዜ "ከተመረጠ" ለሦስተኛ ጊዜ እንደማይመረጥ እንጂ ሥልጣኑን "መረከብ" እንደማይችል አላገደም ሲሉ ነው የሚከራከሩት።

ትራምፕ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው በ2028 ምርጫ መወዳደር እንደሚችሉ ደጋፊዎቻቸው ያምናሉ።

አሁን ያሉት ምክትል ፕሬዝደንት ጄዲ ቫንስ ምክትል ሆነው ትራምፕ ሊወዳደሩ ይችላሉ።

ምርጫውን ካሸነፉ ጄዲ ቫንስ ቃለ መኃላ ይፈጽሙና ከዚያ በኋላ ወዲያው ሥልጣን ለቅቀው ለትራምፕ ያስረክባሉ።

ዋነኛ የትራምፕ አማካሪ ስቲቭ ባነን ትራምፕ "በድጋሚ ተወዳድረው ያሸንፋሉ" ይላል።

የቴኒሲ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባል አንዲ አግልስ ከወራት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ማሻሻያ አስገብዋል።

ማሻሻያው ፕሬዝደንቶች በተከታታይ የሥልጣን ዘመን እስካልሆነ ድረስ ለሦስት ጊዜ ፕሬዝደንት እንዲሆኑ የሚፈቅድ ነው።

ይህ ማሻሻያ ቢጸድቅ ተጠቃሚ የሚሆኑት ትራምፕ ናቸው።

ባራክ ኦባማ፣ ቢል ክሊንተን እና ዶርጅ ደብሊው ቡሽ ሁለት ተከታታይ የሥልጣን ዘመናት ነው የመሩት።

ትራምፕ ግን በ2016 አሸንፈው፣ በ2020 ተሸንፈው፣ በ2024 በድጋሚ አሸንፈዋል።

ይህ ማሻሻያ እውን የሚሆንበት ዕድል ግን ጠባብ ነው።

ትራምፕ ለሦስተኛ ጊዜ ቢመረጡ ማን ይቃወማል?

ዴሞክራቶች ይህንን ሐሳብ ይቃወማሉ።

ትራምፕ ላይ የመጀሪያውን ክስ ካቀረቡ የሕግ ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆነው ዳንኤል ጎልድማን "የመንግሥት ሥልጣንን ለመቆጣጠርና ዴሞክራሲያችንን ለማቀጨጭ የሚደረግ ጥረት" ሲል ነው የገለጸው።

"ሪፐብሊካኖች በሕገ መንግሥቱ የሚያምኑ ከሆነ ትራምፕ ለሦስተኛ ጊዜ ፕሬዝደንት የመሆን ሕልማቸውን መቅጨት አለባቸው" ሲልም ሐሳቡን ገልጿል።

በትራምፕ ፓርቲ ውስጥ ያሉ ሐሳቡን የሚነቅፉም ፖለቲከኞች አሉ።

የኦክላሆማው ሪፐብሊካን ሴናተር ማርክዌይን ሙሊን እንዳሉት ትራምፕ ወደ ዋይት ሀውስ ለመመለስ የሚያደርጉትን ጥረት አይደግፉም።

"አሜሪካውያን ካልፈለጉ በስተቀረ ሕገ መንግሥት አልቀይርም" ብለዋል።

የሕግ ባለሙያዎች ምን ይላሉ?

በኖተርዳም ዩኒቨርስቲ የምርጫ ሕግ ባለሙያው ፕ/ር ዴሬክ ሙለር፣ የሕገ መንግሥቱ 12ኛ አንቀጽ "ፕሬዝደንት የሆነ ሰው ምክትል ፕሬዝደንት ለመሆን ብቁ አይደለም" እንደሚል ያስረዳሉ።

ሁለት ጊዜ ፕሬዝደንት የሆነ ሰው ምክትል ፕሬዝደንት አይሆንም ማለት ነው።

"ለፕሬዝደንትነት የተቀመጠውን የጊዜ ገደም ማለፍ የሚቻልበት 'መንገድ' አለ ብዬ አላስብም" ሲሉም ፕሮፌሰሩ አክለዋል።

ሌላኛው የሕገ መንግሥት ፕሮፌሰር ጀርሚ ፖል "ሦስተኛ ጊዜ ፕሬዝደንት ለመሆን አሳማኝ የሕግ ማዕቀፍ የለም" ብለዋል።

ፍራንክሊን ሩዝቬልት አራት ጊዜ ነው የተመረጡት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፍራንክሊን ሩዝቬልት አራት ጊዜ ነው የተመረጡት

ከሁለት ጊዜ በላይ ፕሬዝደንት የሆነ አለ?

ፍራንክሊን ሩዝቬልት አራት ጊዜ ነው የተመረጡት።

አራተኛ የሥልጣን ዘመናቸውን ጀምረው በሦስት ወራት ውስጥ በ1945 ሞተዋል።

የአሜሪካ ታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የነበሩበት ወቅት ላይ ነበር ሩዝቬልት የመሩት።

ሥልጣናቸው የተራዘመበትን ምክንያት ይሄው ነበር።

በወቅቱ አንድ ሰው ፕሬዝደንት መሆን የሚችለው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው የሚል አንቀጽም በሕገ መንግሥቱ ውስጥ አልተካተተም ነበር።

ይህን አሠራር መተግበር የተጀመረው በ1796 ጆርጅ ዋሽንግተን ለሦስተኛ ጊዜ ፕሬዝደንት አልሆንም ሲሉ ነበር።