በዩኬ 10 ሴቶችን የደፈረው ተማሪ የ24 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደበት

በዩናይትድ ኪንግደም ቻይናዊው የፒኤቺዲ ተማሪ አስር ሴቶችን በመድፈር ወንጀል የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት ሲሆን በትንሹ የ24 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል።

ፖሊስ ግለሰቡን በዩኬ "ጨካኝ ከሆኑ ወንጀለኞች አንዱ" ሲል ገልጾታል።

ዥንሆ ዙዩ የተባለው የቻይና ዜጋ ከአውሮፓውያኑ መስከረም 2019 እስከ ግንቦት 2023 ባሉት ጊዜያት በለንደን ሦስት ሴቶችን፣ ሌሎች ሰባት ሴቶችን ደግሞ በቻይና በአደንዛዥ እፅ በማደንዘዝ አስገድዶ ደፍሯል።

ከአስሩ የጥቃት ሰለባዎች ውስጥ የሦስቱን ማንነት መለየቱን አቃቤ ሕግ ገልጿል። ሆኖም የከተማዋ ፖሊስ የወንጀል መርማሪዎች ግለሰቡ ሌሎች በርካታ ሴቶች ላይ ጥቃቱን ፈፅሞ ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ ጥቃት ተፈፅሞብናል የሚሉ ለፖሊስ ሪፖርት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የፍርድ ሒደቱ ከጀመረ አንስቶም 24 ሴቶች ቀርበዋል።

ፍርድ በተላለፈበት ችሎት ዳኛ ሮሲና ኮታጅ ኬሲ፣ ተከሳሹ የወሲብ ጥቃት ወንጀለኛ መሆኑን ለመደበቅ "የመልካምነትን ጭምብል በማጥለቅ" በጣም ብሩህ የሆነ ወጣት ይመስል ነበር ብለዋል።

በለንደን ክራውን ፍርድ ቤት ውሳኔው ሲሰማም ዳኛ ኮታጅ፣ ዙዩን "አንተ ለዓለም በጣም ጥሩ ሰው ትመስላለህ፤ ግን የወሲብ አዳኝ ነህ" ብለውታል።

ዳኛዋ ጨምረውም ዙዩ ሴቶቹን በማስፈራራት እና እንደ ወሲብ መጫዎቻ በመመልከት የአስገድዶ መድፈር ዘመቻን አቅዶ መፈፀሙን ተናግረዋል።

"ለተጠቂዎቹም የምትፈፅመውን ድርጊት መቃወም ከንቱ መሆኑን ተናግረሃል። ድርጊትንህን እንድታቆም ሲጠይቁህም ጉልበት አሳይተሃቸዋል። እነዚህን ሴቶች ለደስታህ ስትል አንደ የወሲብ መጫወቻ አሻንጉሊት ቆጥረሃቸዋል" ብለውታል።

ዳኛ ኮቴጅ እንደተናገሩት ፍርድ ቤቱ የተመለከታቸው የአስገድዶ መድፈር ቪዲዮዎች "እጅግ አስጨናቂ ናቸው።"አንዳንዶቹም ሲመለከቱት አልቅሰዋል" ብለዋል።

በደቡብ ምሥራቅ ለንደን ኤለፋንት ኤንድ ካስል ውስጥ ይኖር የነበረው ዙዩ በቀረቡበት 11 ክሶች ጥፋተኛ የተባለ ሲሆን ከእነዚህ ሁለቱ ወንጀሎች ከአንድ ተጎጂ ጋር የተያያዙ ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ የወሲብ ምስሎችን ይዞ በመገኘት፣ የውሸት እስራት እና የወሲብ ወንጀል ለመፈፀም በማሰብ መቆጣጠሪያ መድሃኒት ይዞ በመገኘት ሦስት ክስ ቀርቦበታል።

ዙዩ የሴቶችን መገልገያ ቁሳቁስ የያዘ ሳጥን የተገኘበት ሲሆን ከደፈራቸው ሴቶች ውስጥም ዘጠኙን ቀርጾ አስቀምጧል። በቪዲዮው ላይ ተጎጂዎቹ ራሳችን ስተው ይታያሉ። የከተማዋ ፖሊስ ኢንሰፔክተር ሪቻርድ ማኬንዚ፣ ዙዩ "እስከዛሬ ካየናቸው በርካታ ወሲብ አዳኝ ወንጀለኞች መካከል አንዱ ነው" ብለዋል።

አንደኛዋ ሴት የተደፈረችው ዙዩ ብዙ አልኮል መጠጥ እንድትጠጣ ከገፋፋትና ከቤት እንዳትወጣ ከከለከላት በኋላ እንደሆነ ተናግራለች። ተጎጂዋ በሰጠችው ቃል ጥቃቱ ስብዕናዋን ክፉኛ እንደጎዳው ጽፋለች።

" በሰዎች ላይ እምነት አጥቻለሁ። ማንንም አላምንም። ከጥቃቱ በፊት የሰው ልጅ እንዲህ ዓይነት ሰይጣናዊ ድርጊት እንደሚፈፅም አላውቅም ነበር" ብላለች።

" የሆኑ ሰዎችን ሳገኝ እርሱ የፈፀመብኝ ጥቃት ነው የሚታወሰኝ"

ሌላኛዋ ጥቃቱ እንደተፈፀመባት የተለየች ሴት አሁን ላይ በቻይና የምትኖር ሲሆን ዙዩ ጥቅምት 2021 ላይ ራሷን ከሳተች በኋላ በመኖሪያ ቤቱ ጥቃቱን እንደፈፀመባት ተናግራለች።

" የደረሰብኝን የጉዳት መጠን ቃላት አይገልጹትም። አንድ ነገር ግን እርግጠኛ ነኝ። በዚያ ምሽት የሆነው ነገር ውስጤ ላይ እስከወዲያኛው ታትሞ ቀርቷል"

" ፊቱ፣ አገላለጹ፣ መቼም ከፊቴ ላይ አይጠፋም፣ መቼም ይቅርታ አላደርግለትም" ብላለች።

የከተማዋ ፖሊስ ኮማንደር ኬቪን ሳውዝወርዝ፣በግለሰቡ ላይ የተላለፈው ፍርድ በጣም ለተሰቃዩት ሴቶች ትንሽም ቢሆን ያጽናናቸዋል ብሏል።

" አሁንም ምርመራችን ይቀጥላል። በዙዩ ጥቃት ደርሶብኛል የሚል ተጎጂ ካለ ቅሬታ እንቀበላለን። ለቡድናችን የሆነባችሁን ተናግሩ፣ በርህራሄ ፣ በደግነት እና በክብር እንቀባለችኋለን" ብለዋል።

የክራውን አቃቤ ሕግ አገልግሎት ሴራ ፓይክ በበኩላቸው ዙዩ "ተከታታይ ደፋሪ እና ለሴቶች አደገኛ የሆነ ግለሰብ ነው" ሲሉ የእድሜ ልክ እስራት ፍርዱ የፈፀመውን ሰይጣናዊ ተግባር የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።