ሊቨርፑል አሌክሳንደር ኢሳክን በ125 ሚሊዮን ፓውንድ ለማስፈረም ተስማማ

አሌክሳንደር ኢሳክ በኒውካስል ማሊያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሊቨርፑል የእንግሊዝ ክብረ ወሰንን በሰበረ ዋጋ አሌክሳንደር ኢሳክን ከኒውካስል ለማስፈረም ተስማምቷል።

ለዝውውሩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለቢቢሲ ስፖርት እንደገለፁት ስዊዲናዊ ኤርትራዊው አጥቂ ወደ አንፊልድ ለማቅናት ከስምምነት ደርሷል።

የኒውካስል ምንጮች ደግሞ የዝውውር ዋጋው በጠቅላላው ወደ 130 ሚሊዮን ፓውንድ ይደርሳል ብለዋል።

ኢሳክ ሰኞ የስድስት ዓመት ስምምነት ከመፈረሙ በፊት የሕክምና ምርመራ እንደሚያደርግ ታውቋል።

የ25 ዓመቱ አጥቂ ወደ ሊቨርፑል ሊያቀና ይችላል የሚለው ወሬ መሰማት የጀመረው ከሳምንት በፊት ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት ቆይቷል።

ኒውካስል ባለፈው ሳምንት አጥቂው ኒክ ዎልትማድን ከስቱትጋርት ማስፈረሙን ተከትሎ ኢሳክን ለመሸጥ ተስማምቷል።

ሊቨርፑል በተጠናቀቀው የዝውውር መስኮት የክለብ ክብረ ወሰን በሆነ ዋጋ ጀርመናዊውን አማካይ ፍሎሪያን ሪትዝን ማስፈማቸው ይታወሳል። የዝውውር ዋጋው 100 ሚሊዮን ፓውንድ ሲሆን ሊቨርፑል ተጨማሪ 16 ሚሊዮን ፓውንድ ሊከፍል ይችላል።

ቀያዮቹ በተጨማሪም ኡጎ ኤኪቲኬ፣ ሚሎስ ኬርኬዝ፣ ጀረሚ ፍሪሞንግ እና ሌሎች ሦስት ተጫዋቾችን 416 ሚሊዮን ፓውንድ በሚያወጣ ዋጋ አስፈርመዋል።

አክለውም ሰዓታት በቀሩት የዝውውር መስኮት እንግሊዛዊው ተከላካይ ማርክ ጉዮን ከክሪስታል ፓላስ ሊያስፈርሙ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው።

ሉዊዝ ዲያዝ፣ ዳርዊን ኑኔዝ፣ ኩዋንሳህ፣ ኬሌሄር፣ አሌክሳንደር-አርኖድል እና ሌሎች ተጫዋቾች በድምሩ በ190 ሚሊዮን ፓውንድ ተሽጠዋል።

በአውሮፓውያኑ 2022 ከስፔኑ ክለብ ሪያል ሶሲየዳድ በ60 ሚሊዮን ዋጋ ወደ ኒውካስል የመጣው ኢሳክ በሁሉም ውድድሮች በ42 ጨዋታዎች 27 ግቦችን አስቆጥሯል።

ባለፈው መጋቢት ኒውካስል ሊቨርፑልን በመርታት የካራባዎ ዋንጫ ሲያነሳ ኢሳክ ጎል አስቆጥሯል። ክለቡ ኒውካስል ለቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር እንዲበቃም ማድረግ ችሏል።

ኒውካስል በክረምቱ እረፍት ለወዳጅነት ጨዋታ ወደ እስያ ባቀናበት ወቅት አለመጓዙ መነጋገሪያ ነበር። ከዚህ በኋላ ነው ክለቡን መልቀቅ እንደሚፈልግ መነገር የጀመረው።

አርጀንቲናዊው አማካይ ኤንዞ ፈርናንዴዝ በ2023 በ107 ሚሊዮን ፓውንድ ከቤንፊካ ወደ ቼልሲ የመጣበት ዋጋ የብሪታኒያ ክብረ ወሰን ሆኖ ቆይቷል።

ሪትዝ፣ ካይሴዶ፣ ራይስ እና ግሪሊሽ 100 ሚሊዮን ፓውንድ በሚገመት ዋጋ የተዘዋውሩ ተጫዋቾች ናቸው።

በዓለም እግር ኳስ የዝውውር ዋጋ ክብረ ወሰኑን የጨበጠው ኔይማር ሲሆን፣ በ2017 እአአ በ200 ሚሊዮን ፓውንድ ከባርሴሎና ወደ ፒኤስጂ መዛወሩ ይታወሳል።