የሩሲያን ጥቃት ተከትሎ በዩክሬን ከ1ሚሊዮን በላይ ቤቶች ከኤሌትሪክ አቅርቦት ውጪ ሆኑ

የእሳት አደጋ ሠራተኛ በኦዴሳ የሩሲያ ጥቃት በደረሰበት ስፍራ እሳት እያጠፋ

የፎቶው ባለመብት, State Emergency Service Of Ukraine

ሩሲያ በተከታታይ በዩክሬን የኃይል እና ኢንዱስትሪ መሠረተ ልማቶች ላይ የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቤቶች የኤሌክትሪክ ኃይል ማጣታቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት ተናገሩ።

የዩክሬን የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሆር ክላይሜንኮ በጥቃቱ አምስት ክልሎች ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቀው ቢያንስ አምስት ሰዎች ቆስለዋል ብለዋል።

የአገሪቱ የአደጋ መከላከል ሠራተኞች እሳቶቹን ለማጥፋት እና አገልግሎቱን ወደነበረበት ለመመለስ እየሰሩ ነው።

ሩሲያ የዩክሬን የኃይል መሠረተ ልማት ላይ ድብደባ መፈጸሟ የተለመደ ቢሆንም፣ ሞስኮ በአገሪቱ ክረምት እየገባ ሲመጣ ጥቃቷን አጠናክራ ቀጥላለች።

ጥቃቱ የተፈጸመው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የውጭ ጉዳይ ልዑክ በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ጀርመን በመሄድ ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪን እና የአውሮፓ መሪዎች ጋር ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችል ተጨማሪ ውይይቶችን ለማድረግ በተዘጋጁበት ወቅት ነው።

በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል የሰላም ስምምነት እንዲደረስ የዋይት ሐውስን ጥረት የሚመሩት ስቲቭ ዊትኮፍ በበርሊን በአዲሱ የሰላም ስምምነት ነጥቦች ላይ ይወያያሉ።

ቅዳሜ ዕለት ዜሌንስኪ ሩሲያ በአንድ ሌሊት ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ450 በላይ ድሮኖች እና 30 ሚሳኤሎች እንደተጠቀመች ተናግረዋል።

ክላይሜንኮ በበኩላቸው የድኒፕሮፔትሮቭስክ፣ ኪሮቮራድ፣ ማይኮላይቭ፣ ኦዴሳ እና የቼርኒሂቭ ክልሎች የሩሲያ ጥቃት ሰለባ መሆናቸውን ገልጸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ በአውሮፕላን ጥቃቶቹ ላይ የኪንዛል ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን ጨምሮ ሌሎች ሚሳዔሎችን እንደተጠቀመ ገልጿል። ይህም መሣሪያዎቹ በአየር ላይ እያሉ አቅጣጫቸውን ሊቀይሩ ስለሚችሉ ለመከታተል አስቸጋሪ ያደርገዋል።

ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የዩክሬን የዛፖሪዝሂያ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ "በኤሌክትሪክ ማሰራጫው ላይ በተከሰቱ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃቶች ምክንያት" በአንድ ሌሊት ከጣቢያው ውጭ ያለው ኃይል በጊዜያዊነት ተቋርጧል ብሏል።

የኃይል ማመንጫው የሚገኘው በሩሲያ ቁጥጥር ስር ባለው የዩክሬን ግዛት ውስጥ ነው።

የኃይል ማመንጫው በስራ ላይ ባይሆንም፣ ነገር ግን ማብላያዎቹን ለማቀዝቀዝ የማያቋርጥ የኃይል አቅርቦት ማግኘት አለበት።

የትራምፕ አስተዳደር ጦርነቱ በገና በዓል ሰሞን እንዲቆም ለማድረግ በሚል በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ከዩክሬን እና ከሩሲያ ተወካዮች ጋር በርካታ ዙር ውይይቶችን ሲያካሂድ ቆይቷል።

ከስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ፍንጭ ግን እስካሁን ድረስ አልታየም።

በበርሊን በሚደረገው ንግግር የትኞቹ የአውሮፓ መሪዎች እንደሚገኙ እስካሁን አልተረጋገጠም።

የስብሰባውን ዝርዝር መረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የዘገበው ዎል ስትሪት ጆርናል የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር፣ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የጀርመን ቻንስለር ፍሬድሪክ መርዝ ይሳተፋሉ ብሏል።

የዊትኮፍ ዜሌንስኪ ስብሰባ የሚካሄደው ዩክሬን ለአሜሪካ የተሻሻለውን ባለ 20 ነጥብ የሰላም ዕቅድ ካቀረበች በኋላ ነው።

የምሥራቅ ዩክሬን የግዛት ዕጣ ፈንታ በድርድሩ ውስጥ ካሉት እጅግ ቁልፍ ፈታኝ ጉዳዮች መካከል አንዱ ሲሆን ኪየቭ በሕገ ወጥ መንገድ የተያዘውን ግዛት አሳልፋ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለችም።

ሞስኮ ዩክሬን አካባቢውን ለቅቃ ካልወጣች የዶንባስን ክልል ሙሉ በሙሉ በኃይል የመውሰድ ፍላጎት እንዳላት በተደጋጋሚ ገልጻለች።

የተፈጠረውን የግዛት ይገባኛል ጥያቄ ለመፍታት የዩክሬን ጦር ከክልሉ ለቅቆ ወጥቶ "ልዩ የኢኮኖሚ ቀጠና" እንዲፈጠር በሚል አሜሪካ በቅርቡ ያቀረበችውን ሀሳብ ዜሌንስኪ በጥርጣሬ እንደሚመለከቱት ምላሽ ሰጥተዋል።

በአሜሪካ በቀረበው ሀሳብ መሠረት፣ ሩሲያ የዩክሬን ጦር ወደሚለቅቃቸው አካባቢዎች ላለማለፍ ቃል እንደምትገባ፣ ከዚያም በክሬምሊን ቁጥጥር ስር ባሉ የዶንባስ አካባቢዎች እና የዩክሬን የመከላከያ መስመሮች መካከል ያለው መሬት ከወታደራዊ ኃይል ነፃ ቀጠናነት እንደሚቀየር መገለፁን የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ለጋዜጠኞች ይፋ አድርገዋል።

ዜሌንስኪ "[ሩሲያ] እንዳትገፋ የሚያግደው ምንድን ነው? ወይም ሰላማዊ ሰዎች መስለው ተደብቀው ሰርገው ከመግባት የሚያግደው ምንድን ነው?" ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል።

ዩክሬን እና በአውሮፓ ያሉ አጋሮቿ በይፋ በአሜሪካ የሚመራውን ውይይት ፍሬያማ እንደሆነ ይናገራሉ።

መጀመርያ ላይ ለሩሲያ ያደላ ነበር የተባለው የሰላም ዕቅድ ላይ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ የተደረጉ ለውጦችን አድንቀዋል።

ነገር ግን በቅርብ ሳምንታት ትራምፕ በዜሌንስኪ እና ደጋፊዎቻቸው ላይ ትዕግስት እያጡ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች ተስተውለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከፖሊቲኮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የአውሮፓ መሪዎችን "ደካማ" ብለው ጠርተው፤ ዩክሬን ምርጫ እንድታደርግም ጥሪያቸውን ዳግም አቅርበዋል።

ዜሌንስኪ በበኩላቸው አሜሪካ እና አውሮፓ አስፈላጊውን የጸጥታ ዋስትና የሚሰጡ ከሆነ ምርጫ በ90 ቀናት ውስጥ ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል።