በፑቲን ከሥልጣናቸው የተባረሩት ሚኒስትር ሞተው ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, AP
የቀድሞ የሩሲያ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሮማን ስታሮቮይት ራሳቸውን በጥይት ገድለው መገኘታቸውን የሩሲያ መርማሪ ኮሚቴ አስታወቀ።
ግለሰቡ ራሳቸውን አጥፍተዋል ከመባሉ ቀደም ብሎ ሰኞ ዕለት በፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከሥልጣናቸው ተሰናብተዋል።
ስታሮቮይት ከሥልጣን የተነሱበት ምክንያት ያልተገለፀ ሲሆን፣ ብዙም ሳይቆይ ምክትላቸው አንድሬ ኒኪቲን በምትካቸው ተሾመዋል።
የምርመራ ኮሚቴው ሁኔታውን ለማጣራት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
ስታሮቮይት እአአ በግንቦት 2024 የትራንስፖርት ሚኒስትር ሆኖ ተሾመዋል።
ከዚያ በፊት ስታሮቮይት እስከ ግንቦት 2024 ድረስ ለስድስት ዓመታት ያህል የኩርስክ ክልል አስተዳዳሪ ሆነው አገልግለዋል።
ክልሉ በነሐሴ 2024 በዩክሬን መከላከያ ኃይል ከተፈጸመበት ድንገታዊ ጥቃት በኋላ በከፊል በዩክሬን ወታደሮች ተይዟል።
ሞስኮ የዩክሬይን ኃይሎችን ማስወጣት የቻለችው በቅርቡ ቢሆንም፣ በሰኔ ወር መጨረሻ ግን ኪየቭ በሩሲያ ውስጥ አሁንም አነስተኛ የግዛቱን አከባቢዎች በቁጥጥሯ ስር እንደሚገኝ አስታውቃለች።
የስታሮቮይት ሥልጣን የተረከቡት ግለሰብ አሌክሲ ስሚርኖቭ በቦታው ላይ የቆዩት ለአጭር ጊዜ ብቻ ነበር።
በሚያዝያ ወር በቁጥጥር ስር የዋሉት ሚኒስትሩ በዩክሬን ድንበር ላይ ምሽጎችን ለመገንባት የተመደበውን ገንዘብ በማባከን ተከስሰዋል።
እንደ ሩሲያዊው መገናኛ ብዙኃን ኮምመርሰንት ዘገባ ከሆነ ስታሮቮይት በዚሁ ክስ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ነበር።
ስታሮቮይት መቼ እንደሞቱ በትክክል አልታወቀም።
የዱማ መከላከያ ኮሚቴ ኃላፊ አንድሬይ ካርታፖሎቭ ለሩሲያ አርቲቪአይ ጋዜጣ እንደተናገሩት የሚኒስትሩ ሞት የተከሰተው "ከተወሰነ ጊዜ በፊት" ነው።
ሰኞ ዕለት የስታሮቮይት ሞት ከመሰማቱ ቀደም ብሎ በፊት የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወቅት የሚኒስትሩ ከኃላፊነታቸው መነሳት ፑቲን በኩርስክ በተከሰቱት ክስተቶች ላይ በስታሮቮይት ላይ ያላቸውን እምነት አጥተዋል ማለት ነው ተብለው ተጠይቀው ነበር።
"የእምነት ማጣት ካለ የእምነት ማጣት መኖሩ ይጠቀሳል። እንደዚህ ዓይነት ቃላት [በክሬምሊን መግለጫ] ጥቅም ላይ አልዋሉም " በማለት ፔስኮቭ ምላሽ ሰጥተዋል።















