ሩሲያ ለታሊባን ዕውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ አገር ሆነች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩሲያ አፍጋኒስታንን ለሚያስተዳድረው መንግሥት ዕውቅና በመሰጠት የመጀመሪያዋ አገር ሆነች።
ውሳኔው ታሊባን ካቡልን ከተቆጣጠረ እና ሥልጣን ከያዘ ከአራት ዓመታት በኋላ የተወሰደ ትልቅ እርምጃ ነው።
የአፍጋኒስታኑ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር ካሃን ሙታኪ የሩሲያ ውሳኔ ለሌሎች አገራት ምሳሌ ይሆናል ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።
ታሊባን አፍጋኒስታንን የሚያስተዳድረው በሸሪዓ ሕግ ሲሆን፣ ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የተለያዩ ገደቦችን ጥሏል።
የሩሲያን እርምጃ የተቃወሙት የቀድሞዋ የአፍጋኒስታን ፖለቲከኛ ፋውዚያ ኮፊ "የትኛውም አገር ከታሊባን ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል የሚወስደው እርምጃ ሰላምን አያመጣም፤ ጭቆናን ሕጋዊ ያደርገዋል" ብለዋል።
ኮፊ በመቀጠል "እንዲህ ያሉት እርምጃዎች የአፍጋኒስታንን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የዓለምን ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ" ሲል አስጠንቅቀዋል።
የአፍጋኒስታን የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ኔትዎርክ ደግሞ "አምባገነን፣ ፀረ ሴቶች እና መሠረታዊ የዜጎችን መብቶችን በትጋት የሚያፈርስ አገዛዝ" እውቅና አግኝቷል ሲሉ ውሳኔውን ተቃውመዋል።
የታሊባን መንግሥት በአፍጋኒስታን ባህል እና የእስልምና ሕግ መሠረት የሴቶችን መብት እንደሚያከብር ቀደም ሲል ተናግሯል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ 2021 ጀምሮ ግን ከ12 ዓመት በላይ የሆናቸው ልጃገረዶች ትምህርት እንዳያገኙ እንዲሁም ሴቶች ከበርካታ ሥራዎች ታግደዋል።
አንዲት ሴት ያለ ወንድ አጃቢ ምን ያህል ርቀት መጓዝ እንደምትችል፤ እንዲሁም በአደባባይ ድምጿን ከፍ ማድረግ ስለመትችልበት መጠን የሚደነግጉ ገደቦች ወጥተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሙታኪ ሞስኮ ሐሙስ ዕለት ሩሲያ ዕውቅና መስጠቷን ተከትሎ "በመከባበር ላይ የተመሰረተ አዲስ የአዎንታዊ ግንኙነት" መጀመሩን ገልጸው፣ ውሳኔውን "ድፍረት የተሞላበት" ብለውታል።
በአፍጋኒስታን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተበርክቷል የሚሉ ሪፖርቶች በስፋት ቢደመጥም በአውሮፓውያኑ 2021 ዳግም ሥልጣን የተቆጣጠረው ታሊባን ዓለም አቀፍ እውቅናን እና ኢንቨስትመንትን ከሌሎች አገራት ሲጠይቅ ቆይቷል።
የሩሲያ ውጪ ጉዳይ ሚኒቴር ባወጣው መግለጫ ለአፍጋኒስታን ይፋዊ ዕውቅና መስጠት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን አዎንታዊ ግንኙነት ያጠናክረዋል ብለን እናምናለን ብሏል።
ቀጥሎም ሩስያ ከአፍጋኒስታን ጋር በኢነርጂ፣ በትራንስፖረት፣ በግብርናና መሠረተ ልማት ዘርፎች ላይ የንግድ እና ኢኮኖሚ ትብብር ማድረግ የሚቻልበት ዕድልን እየተመለከተች ነው ሲል ገለጿል።
በተጨማሪም ሞስኮ ሽበርተኝነት የጋረጠውን ስጋት እና የአድንዛዥ ዕጽ ዝውውርን ለመግታት የካቡል መንግሥትን መርዳቷን እንደምትቀጥል አሳውቃለች።
በአውሮፓውያኑ 2021 ታሊባን ሥልጣን ሲቆጣጠር በአፍጋኒስታን ኤምባሲያቸውን ካልዘጉ ጥቂት አገራት መካከል ሩሲያ አንዷ ናት። የሩሲያ መንግሥት ከታሊባን ጋር የሚደረገውን ውይይት ማጠናከር ለቀጠናው ሰላምና ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ነው ብሏል።
በተጨማሪም ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2022 ከታሊባን ጋር ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ስምምነት በማድረግ የመጀመሪያዋ አገር ነች። በዚያ ስምምነት ሩሲያ ለአፍጋኒስታን ነዳጅ፣ ጋዝ እና ስንዴን ለማቅርብ ተስማምታለች።
በዚህ ዓመት ሚያዚያ ወር ታሊባን ከሩሲያ የአሸባሪነት ዝርዝር ውስጥ የተሰረዘ ሲሆን ይህ የሆነው ከካቡል መንግሥት ጋር የተሟላ ትብብርን ለመፍጠር እንደሆነ ሩስያ ገልጻ ነበር።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ታሊባን ሽብርተኝነትን ለመዋጋት "አጋር" ነው በማለት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ተናግረዋል።
በአውሮፓውኑ 1979 ሶቪየት ኅብረት አፍጋኒስታንን ከወረረች እና ለ9 ዓመታት ተዋግተው በሁለቱም ወገን በኩል በደምሩ 15 ሺህ ወታደር ከሞተ ወዲህ ሁለቱ አገራት ያላቸው ግንኙነት ውስብስብ የሚባል ነው።
የሶቪየት ኅብረት መንግሥት በካቡል የሚደግፈውን መንግስት ለማቋቋም ያደረገው ጦርነት ዓለም አቀፍ መገለለልን ያስከተለበት ሲሆን በአውሮፓውያኑ 1989 ደግሞ አፍጋኒስታንን ለቆ እንዲቀጣ አስገድዶታል።















