የማይጾሙት እና ዕለታዊ ፀሎት የማያደርሱት የሙስሊም ማኅበረሰቦች

በማዕከላዊ ሴኔጋል በሚገኘው ማብኪ ካዲዮር መንደር የሙስሊሞች ዝማሬ ይሰማል።

ከመስጊድ ውጪ ክብ ሠርተው ድምጻቸው ጎልቶ ያስተጋባል። ድምጻቸው ከፍ እና ዝቅ የሚለው በኅብረት ነው። የባዬ ፎል ተከታይ ሙስሊሞች ናቸው።

ከጀርባቸው እሳት ሲነድ ይታያል። በእሳቱ ነበልባል ነፀብራቅ ውስጥ የሰውነታቸው እንቅስቃሴ ይስተዋላል።

ቁጥርጥር ያለው (ድሬድሎክ) ፀጉራቸው ከእንቅስቃሴያቸው ጋር አብሮ ይወዛወዛል። በዚህ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ከዛለ ሰውነታቸው ላይ ላብ ይስተዋላል። ሃይማኖታዊ ክንውኑ ሳም ፎል ይባላል።

ደስታን እንዲሁም አምልኮን መግለጫ መንገድም ነው።

በዚህ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ሲሳተፉ በተመስጦ ተነጥቆ የመወሰድ ዓይነት ስሜት ይነበብባቸዋል። በሳምንት ሁለት ጊዜ ሥነ ሥርዓቱን የሚያካሂዱ ሲሆን፣ ሁለት ሰዓት ይወስዳል።

ባዬ ፎል የተባለው ይህ ቡድን በሴኔጋል የሚገኘው ሞሪድ ወንድማማቻዊ ቡድን አካል ነው። እንደ ሌሎች ሙስሊሞች አይደሉም።

ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሴኔጋል ውስጥ ከሚኖሩ 17 ሚሊዮን ዜጎች አብዛኞቹ ሙስሊሞች ናቸው። የዚህ ቡድን አባላት ግን ውስን ናቸው።

ለየት ያሉ ስለሆኑ ትኩረት ይስባሉ። ከእስልምና የራቁ የእምነት እና የአስተሳሰብ መንገዶች አሏቸው።

እንደ አብዛኞቹ ሙስሊሞች በቀን አምስት ጊዜ አይፀልዩም፤ በረመዳን ወቅትም አይጾሙም። የሚያምኑት ጠንክሮ በመሥራት እና ማኅበረሰባዊ አገልግሎት በመስጠት ነው።

ገነትን እንደ መዳረሻ ሳይሆን ተግተው ለሚሠሩ ሰዎች እንደ ስጦታ የሚበረከት እንደሆነ ያምናሉ።

ሌሎች ሙስሊሞች ይሄንን ቡድን እምብዛም አይረዱትም። በምዕራባውያን ዘንድ የዚህ ቡድን አባላት መጠጥ ይጠጣሉ፣ ዕፀ ፋርስ ይወስዳሉ የሚል የተዛባ ዕሳቤ አለ። ይህ ግን የነሱ መርኅ አይደለም።

በማብኪ ካዲዮር መንደር ያለው የባዬ ፎል ቡድን መሪ የሆኑት ማም ሳምባ "የባዬ ፎል ፍልስፍና ያተኮረው ሥራ ላይ ነው። በመንፈሳዊ ሥራ እናምናለን። ጉልበት አውጥቶ መሥራት ለፈጣሪ መታመን ነው" ይላሉ።

በጠራራ ፀሐይ ማረስም ይሆን ትምህርት ቤት መሥራት አልያም ቅርጻ ቅርጽ ማዘጋጀት መንፈሳዊ ዋጋ አለው ብለው ነው የሚያምኑት።

ሥራ ኃላፊነትን መወጣት ብቻ አይደለም። ተመስጦ ውስጥ የሚከት እንደ ፀሎት ያለ ክንውንም ነው።

የዚህ ቡድን መሥራች ኢብራሒም ፎል በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብኪ ካዲዮር መንደር ውስጥ የሞሪድ ወንድማማቻዊ ቡድንን የመሠረተውን ቼኪሕ አሕማዱ ባምባን እንዳገኘው ያምናሉ።

ሞሪድ ወንድማማቻዊ የሱፊ እስልምና አንድ አካል ነው። በሴኔጋል ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።

ኢብራሒም ፎል ሙሉ በሙሉ አገልግሎቱን ለቼኪሕ አሕማዱ ባምባ ሰጥቶ ስለ ራሱ እንደዘነጋ በማኅበረሰቡ ዘንድ ይነገራል። መብላት፣ መጾም፣ መፀለይና ራሱን መንከባከብ አቁሞ እንደነበርም ያምናሉ።

በጊዜ ሒደት ልብሱ አርጅቶ እንደተቀዳደደ ይናገራሉ። ራስን ጥሎ ታማኝ የመሆን ተምሳሌት ነው። ልብሱ ሲቀደድ እየሰፋ ይለብስ ስለነበር የባዬ ፎል ተከታዮች የተጣፈ ልብስ አድርጎ መሄድን እንደ ፍልስፍና ወርሰዋል።

ለሃይማኖት መሪ በዚህ መጠን ታማኝ መሆንን ማኅበረሰቡ አሁንም ይተገብራል። ይህ ሥርዓት ኒጉል ይባላል።

የባዬ ፎል ተከታዮች ይሄንን ሥርዓት ለልጆቻቸው መጠሪያም ያደርጉታል።

በማብኪ ካዲዮር መንደር በሚገኝ ወርክሾፕ ውስጥ የማኅበረሰቡ የትብብር እና የሥራ መንፈስ ይታያል። በፈጠራ የተሞሉ ውብ የተጣፉ ልብሶች ያዘጋጃሉ።

ሴቶቹ ሙሉ ትኩረት ሰጥተው ጨርቆች ቀለም ውስጥ እየነከሩ ያሳምራሉ። የቀለማቱ ውህድ ቆንጆ ልብስ ይፈጥራል።

ወንዶቹም ሙሉ ትኩረት ሰጥተው የቀለሙትን ልብሶች ይሰፏቸዋል። ለመልበስ ምቹና የባዬ ፎል ማንነት መገለጫ ሆነው ይሠራሉ።

ፈጠራው እና ታታሪነታቸው ምን ያህል ተመስጦ እንዳላቸው ያሳያል። ልብሶቹ ተሰፍተው ሲጠናቀቁ በሴኔጋል ገበያ ይቀርባሉ። ማኅበረሰቡን በገንዘብ የሚደግፉ እና የማኅበረሰቡን ፍልስፍና የሚያስተዋውቁ ናቸው።

የባዬ ፎል ቡድን መሪ የሆኑት ማም ሳምባ እንደሚሉት፣ የባዬ ፎል ዘዬ የራሳቸው ፈጠራ ነው።

አባታቸው የተከበሩ የባዬ ፎል ሼኽ ነበሩ።

"የተጣፈው ልብስ ዓለም አቀፋዊ አንድነትን ይወክላል። ሙስሊም ሆኖ ባህልን መጠበቅ ይቻላል። ሁሉም ሰው ይሄን አይረዳም። ትችት የማይቀበል ሰው አያድግም እንላለን" ይላሉ መሪው።

በረመዳን ወቅት ሌሎች ሙስሊሞች ሲጾሙ የባዬ ፎል ተከታዮች ለኢፍጣር ምግብ ያዘጋጃሉ።

የጋራ የንግድ ድርጅቶች እና በገጠራማ ሴኔጋል ድጋፍ የሚሰጡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም መሥርተዋል።

ሥራ ለመኖር ሲባል የሚደረግ ሳይሆን መንፈሳዊም ተደርጎ ይወሰዳል።

"ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማትና ንግዶች አሉን። የሕይወት ፍልስፍናችንን በአክብሮት፣ ፍቅር እና ለተፈጥሮ ትኩረት በመስጠት ነው የምንከውነው። ዘላቂነት ላለው ዕድገት ብዝሃ ሕይወት መጠበቅ አለበት" ይላሉ መሪው።

ሆኖም ግን ቡድኑ መንገድ ላይ በመለመን ትችቶች ቀርበውበታል።

በባዬ ፎል እምነት ገንዘብ መጠየቅ ባይከለከልም፣ ገንዘብ ሰብስቦ ለመሪው በመስጠት መልሶ ለማኅበረሰቡ ማከፋፈል የተለመደ ነው።

ሞሪድ ወንድማማቻዊ ቡድን ላይ ጥናት የሠሩት የቀድሞው የዲዮፕ ዩኒቨርስቲ ምክትል ቻንስለር ሼክ ሴን "እውነተኛ ባዬ ፎል እና ሐሰተኛ አለ" ይላሉ።

በዳካር እነዚህ "ሐሰተኛ" የተባሉት ባዬ ፎሎች በብዛት እንደሚታዩ ገልጸዋል።

"እንደኛ ለብሰው ይለምናሉ። ለማኅበረሰቡ ግን ምንም አያደርጉም። ስማችንን እያጠፉ ነው" ይላሉ።

የባዬ ፎል ጠንክሮ የመሥራት እና ማኅበራዊ መደጋገፍ ከሴኔጋልም ያለፈ ታዋቂነት አግኝቷል።

እአአ በ2019 ማኅበረሰቡን ከጎበኘች በኋላ የባዬ ፎል ተከታይ የሆነችው አሜሪካዊቷ ኪቶን ሳውየር ስካንሎን ተጠቃሽ ናት። ስሟን ወደ ፋጢማ ባቱለይ ባሕ ለውጣለች።

"ከሰውነቱ ብርሃን ሲመነጭ አየሁ። ልቤ እውነታውን አወቀ። መንፈሳዊ መነቃቃት አገኘሁ" ትላለች።

ሌሎችም ሰዎች ከተለያዩ አገራት ወደ ማኅበረሰቡ እየተቀላቀሉ ነው።

ማኅበረሰቡ በተለይም በግብርናው ዘርፍ ለሴኔጋል ምጣኔ ሃብት ከፍተኛ ሚና አለው። በየጊዜው ለሞሪድ መሪ ወይም ካሊፍ ታማኝነታቸውን በመግለጽ ቃል ይገባሉ። ገንዘብና የቀንድ ከብትና ሰብል ይለግሳሉ።

በሴኔጋል ቅዱስ ከተማ ቶባ ያለውን ግራንድ መስጊድ ይጠብቃሉ። በሞሪዲዝም ጉልህ ቦታ የሚሰጠው ነው።

በቶባ ኢ-መደበኛ የደኅንነት ጠባቂዎች ግራንድ መስጊድን ይጠብቃሉ። በየዓመቱ ማጋል ሃይማኖታዊ ጉዞ ሱደረግ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ቶባ ይሄዳሉ።

ሰዎች በአግባቡ እንዲለብሱ፣ አደንዛዥ ጽፅ እንዳይሸጥ እና መሪ የሆኑት ካሊፍ እንዲከበሩ የደኅንነት ጠባቂዎች ይሠራሉ።

በባዬ ፎል ላይ ጥናት የሠሩት ባለሙያ "የካሊፉን እና የከተማውን ደኅንነት ሁሌም ያስጠብቃሉ። ባዬ ፎል እያለ ማንም አያፈነግጥም" ይላሉ።

የሚነቅፏቸው ቢኖሩም በሴኔጋል ሃይማኖታዊና ባህላዊ መድረክ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ እየጨመረ ነው። በእርግጥ ባህልና ዘመናዊነትን ለማመጣን የተወሰነ ይቸገራሉ።

የገንዘብ ውስንነትም የሚያስፈልጋቸውን እንዳያደርጉ አግዷል።

ሕልማቸው በእምነት እና በአገልግሎት ላይ የተመረኮዘ ዘላቂነት ያለው ዕድገት ነው። በሴኔጋል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሥራ አጦችን ሊደግፉም ይችላሉ።

አብዛኞቹ ሥራ አጦች ወደ አውሮፓ ለመሻገር አደገኛ የባሕር ጉዞ ያደርጋሉ።

የባዬ ፎሌ መሪ "ብዙ ማድረግ እንሻለን። ብዙ ሥራ መፍጠር እንሻለን። ከመንግሥት እና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር መጣመር አለብን። በዚያ መንገድ ነው የወደፊቱን የምናስተካክለው" ይላሉ።

ጠንክሮ መሥራት ለአገሪቱ የምጣኔ ሃብት ችግር እና መንፈሳዊ ጥያቄም መልስ ነው ብለው ያምናሉ።