ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ በተደረገ ውድድር የእሳት አደጋ መከላከያ ሮቦት ሠርተው ያሸነፉት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች
በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ በ‘ሎውረንስ ቴክኖሎጂካል ዩኒቨርስቲ’ የሚያዘጋጀውን የሮቦቲክስ ውድድር ያሸነፉ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተው ተመልሰዋል።
ታዳጊዎቹ ላለፉት ሁለት ዓመታት በአቦጊዳ ሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ ማዕከል ውስጥ ሥልጠና ሲወስዱ እና የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ሲያቀርቡ የቆዩ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ናቸው።
በዚህ ‘ሮቦ ፌስት’ ውድድር ከአብርሆት የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን አቡጊዳ ሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ ማዕከል ሥልጠና የሰጣቸው ተማሪዎች የሠሯቸውን ሮቦቶች ለዕይታ አቅርበዋል።
እነዚህ ለውድድር የቀረቡ ተማሪዎች ከ12ኛ ክፍል በታች የሆኑ ኢትዮጵያውን ታዳጊዎች፣ በአምስት የተለያዩ መስኮች አገራቸውን መወከል ችለዋል።
አሸናፊዎቹ በዩኒቨርስቲው መማር የሚያስችላቸውን ዕድል ያገኙ ሲሆን፣ በተጨማሪም ሜዳልያ እና ዋንጫም እንደተሸለሙ የአቦጊዳ ሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ ዋና መሥራች ምህረት ዋልጋ ለቢቢሲ ተናግራለች።
አቦጊዳ ለሚያሰለጥናቸው ተማሪዎች አብርሆት የሕዝብ ቤተመጻሕፍት ለተማሪዎቹ ሥልጠና የሚሆኑ ግብዓቶችን በማቅረብ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደግሞ ተማሪዎቹን ስፖንሰር በማድረግ መሳተፋቸውን ምህረት ትናገራለች።
ውድድሩ 16 ዘርፎች የነበሩት ሲሆን ኢትዮጵያን ወክለው የተወዳደሩት ቡድን በአምስት የተለያዩ ዘርፎች ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያውያኑ ታዳጊዎች ከተወዳደሩባቸው አምስት ዘርፎች መካከል በሦስቱ በማሸነፍ ተሸላሚ መሆንም ችለዋል።
በሁለቱ የውድድር ዘርፎች ደግሞ አምስተኛ እና ስድስተኛ ወጥተዋል።
በውድድሩ ተሳታፊ የነበሩት የሰባተኛ እና የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ከሠሯቸው የፈጠራ ሥራዎች ውስጥ ሙቀት እና ቅዝቃዜን ማመታጠን የሚችል ጃኬት እንደሚገኝበት የአቡጊዳ ሮቦቲክስ እና ቴክኖሎጂ ማዕከል መሥራች እና ዳይሬክተር ምህረት ዋልጋ ለቢቢሲ ተናግራለች።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል መምህርት የሆነችው ምህረት “ተማሪዎቹ የሠሩት ጃኬት የሙቀት መጠንን ለክቶ ወዲያውኑ ተመጣጣኝ የሆነ ሙቀት ወይንም ቅዝቃዜ እንዲኖር የሚያደርግ ነው” ትላለች።
ይህንን ጃኬት ለመሥራት ተማሪዎቹ የተለያዩ የሒሳብ እና የፊዚክስ ቀመሮችን እና ሞዴሎችን መማር አስፈልጓቸው ነበር።
አክላም ይህንን ጃኬት ታምመው በአልጋ ላይ የዋሉ እና መገላበጥ የሚቸገሩ ሰዎች ሊጠቀሙት እንደሚችሉም ትናገራለች።
“አልጋ ላይ ዋሉ ህሙማን ለረዥም ጊዜ ሳይገላበጡ ተኝተው ስለሚያሳልፉ ጀርባቸው ይላጣል፤ ይህ ጃኬት ግን የሰውነታቸውን ሙቀት በመለካት የሚያስፈልጋቸውን የሙቀት መጠን በመስጠት ያግዛቸዋል።”
በተጨማሪም ጃኬቱን በተለያዩ አስቸጋሪ የአየር ጠባይ ውስጥ የሚሠሩ ሰዎች ሊጠቀሙት እንደሚችሉ ምህረት ታስረዳለች።
“ለምሳሌ የአየር መንገድ ሠራተኞች በተለዋዋጭ አየር ሁኔታ ውስጥ ስለሚያሳልፉ ሊጠቀሙት ይችላሉ።”
ምህረት በአውደ ርዕዩ ላይ ሌላው ተሳታፊ የሆነው ቡድን ከ10ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ያሉ ተማሪዎች ያሉበት መሆኑን ለቢቢሲ ገልጻለች።
በዚህ ዘርፍ የተወዳደሩ ተማሪዎች በትልልቅ ኢንዱስትሪዎች የሚፈጠሩ የአየር ብክለቶችን እንዲሁም የእሳት አደጋዎችን መከላከል የሚያስችል የሮቦቲክስ ሥርዓትን ማዘጋጀት ችለዋል።
በኢንዱስትሪዎች የሚለቀቁ በካይ ጋዞች ለክቶ ማሳወቅ የሚችለው የፈጠራ ሥራም ሌላው ተማሪዎች ተወዳድረው የተሸለሙበት መሆኑን ገልጻለች።
የሮቦቲክስ ሲስተሙ ከኢንዱስትሪው ምን ያህል ጭስ ወደ አየር እየተለቀቀ እንደሆነ መመዝገብ ይችላል።
ይህንን መረጃ ወደ ኮምፒውተር በማስገባት ምን ያህል በካይ ጋዝ ከኢንዱስትሪው ወደ አየር አንደተለቀቀ እንደሚያሰላ ምህረት ታስረዳለች።
ከዚህ በተጨማሪም እሳት የሚያጠፋው ሮቦት የተማሪዎቹ የፈጠራ ውጤት ነው።
የእሳት ማጥፊያው ሮቦት እንዴት እንደሚሠራም ስታስረዳ “በኢንዱስትሪዎች ላይ ጭስን በቀላሉ መለየት የሚችሉ መሳርያዎች በተለያዩ ወለሎች ላይ ይገጠማሉ። መሳርያዎቹም ጭስ ሲኖር በቀላሉ ለሮቦቱ መልዕክት ያስተላልፋሉ። ከዚያም መልዕክቱን የተቀበለው ሮቦት በቀጥታ አደጋው ወደተፈጠረበት ስፍራ በማምራት እሳት ካለ ያጠፋል።”
የተነሳው እሳት ከጠፋም በኋላ ጭስ የሚለየው መሳርያ ወዲያውኑ ምልክት መስጠቱን ያቋርጣል።
በውድድሩ የተገኘ ሽልማት
ሎውረንስ ቴክኖሎጂካል ዩኒቨርስቲ ባዘጋጀው በዚህ ውደድር ላይ ከ33 አገራት የመጡ ታዳጊዎች በተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች መወዳደራቸውን የምትናገረው ምህረት “እናሸንፋለን የሚል ግምት አልነበረኝም” ትላለች።
ከሌሎች አገራት የመጡት ተወዳዳሪዎች የተራቀቁ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው ሥራዎችቻውን በማቅረባቸው የማሸነፍ ዕድልቸው ሰፊ ነው የሚል እምነት ነበራት።
“እኛ ባሉን ቁሶች በጣም ተጣበን ነበር እየሠራን የነበረው” ስትል የነበረውን ሁኔታ ታስረዳለች።
አሸናፊ የሆኑት ተማሪዎች ሜዳሊያዎችን፣ ዋንጫዎችን እና ነጻ የትምህርት ዕድሎችን ከአዘጋጁ ዩኒቨርስቲ ተቀብለዋል።
እነዚህን ተወዳዳሪዎችን በመጥቀስም “ትልቅ ስኬት ነበር” የምትለው ምህረት፣ ሌላ የተሻለ የፈጠራ ሥራ ለመሥራትም ማበረታቻ እንደሆናት ትናገራለች።
ተማሪዎቿ ምንጊዜም የተለያዩ መፍትሄ የሚሰጡ የፈጠራ ሀሳቦች ላይ እንዲያተኩሩ እንደምትጥር የምትናገረው ምህረት ተማሪዎች ወደ ቴክኖሎጂ መስክ ከመግባታቸው በፊት፣ በማዕከላቸው በፈጠራ ሀሳብ ላይ ስልጠና ወስደው ችግር ፈቺ ሀሳብ በማቅረብ እንደሚሠሩ ትናገራለች።
የወደፊት ዕቅድ
ምህረት ወልጋን የሮቦቲክስ እና የቴክኖሎጂ ማዕከል ከፍቶ ከመሥራት ባሻገር የመብት ባለቤትነት ያገኘችባቸው የፈጠራ ሥራዎች አሏት።
“የመጀመርያ ፓተንቴን ለማግኘት ጥያቄ ያቀረብኩት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ነው። 12ኛ ክፍል ከመጨረሴ በፊት የራሴን ነገር መክፈት የምችልበትን ነገር እፈጥራለሁ የሚል እምነት ነበረኝ።”
ምህረት አቦጊዳን ከአምስት ዓመት በፊት ስትመሠርት ዓላማ ያደረገችው፣ እርሷ በአፍላ እድሜዋ ማሳካት ያልቻለችውን አሁን ያሉ ታዳጊዎች ማሳካት እንዲችሉ በማሰብ ነው።
“ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በቴክኖሎጂ እና በሮቦቲክስ ፈጠራ አፍሪካን በአስተማማኝ እጅ ላይ የማሳረፍ፣ የማስተላለፍ ህልም ይዘን ነው የተነሳነው።”
አሁን ያሉ ታዳጊ ወጣቶች ወደ ሥራው ዓለም በሚቀላቀሉበት ወቅት በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የተነሳ አዳዲስ ሥራ ዕድሎች ተፈጥረው እንደሚጠብቋቸው የምትናገረው ምህረት፣ ለእነዚህ የሥራ ዕድሎች ብቁ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እና አፍሪካውያን ወጣቶች ላይ ከአሁን መሥራት ያስፈልጋል ትላለች።
ምህረት በአቦጊዳ ማዕከል ለታዳጊ ተማሪዎች በክረምት ወራት በሳምንት አምስት ቀናት እንዲሁም ከመስከረም እስከ ሰኔ ባሉት ጊዜያት በሳምንት አንድ ቀን ሥልጠናዎችን ትሰጣለች።
በተቋሙ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ በነጻ ሥልጣና ለማግኘት የሚጠይቁ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የምትናገረው ምህረት፣ እነርሱ ግን የተማሪዎቹን ጥንካሬ በመመዘን ለውስን ተማሪዎች ብቻ ይህንን ዕድል መስጠት እንደቻሉ ትናገራለች።
ነገር ግን በተቋሙ የተማሪዎቹን ወጪ የሚሸፍኑ ግለሰቦችም ሆነ ተቋማት ቢገኙ በርካታ ተማሪዎችን በመቀበል ማስተማር እንደሚቻል ታምናለች።
አቦጊዳ ሮቦቲክስ ከተቋቋመ አምስት ዓመቱ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት በኬንያ እንዲሁም በሩሲያ ተደረጉ ውድድሮች ላይ አሸናፊ የሆኑ ፕሮጀክቶችን የሠሩ ተማሪዎችን አፍርቷል።