ጋዛ፡ “የት እንድንሄድ ነው የሚፈልጉት? እንዲህ ሆነን የት እንሂድላቸው?”

ከፍርስራሾች መካከል ዳቦ የምትጋግር ፍልስጤማዊት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ከፍርስራሾች መካከል ዳቦ የምትጋግር ፍልስጤማዊት

ጋዛ ላይ ወታደራዊ እርምጃ እየወሰደ ያለው የእስራኤል ጦር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፊቱን ወደ ደቡብ ጋዛ በማዞር ኻን ዩኒስ የተሰኘችውን ከተማ ዒላማ ማድረግ ጀምሯል።

2.3 ሚሊዮን ፍልስጤማዊያን ሰሜናዊ ጋዛ ጥቃት ሲደርስበት ወደ ደቡባ አቅጣጫ ነው ያመሩት። መዳረሻቸው ደግሞ ኻን ዩኒስ።

ከተማዋ በአዲስ መጥ ተፈናቃዮች ተጨናንቃለች። ምግብ፣ ውሃ እና መጠለያ ማግኘት ከባድ ሆኗል።

ከሰርጡ ቢያንስ 1.9 ሚሊዮን ያክል ሰዎች እንደተፈናቀሉ መረጃዎች ይገልጣሉ።

በእስራኤል እርምጃ ምክንያት አንድ ተፈናቃይ ወዳጅ ቤተሰቡን ይዞ እንደተሰደደ ለቢቢሲ ይናገራል።

“የእስራኤል ባለሥልጣናት በሄሊኮፕተር የማስጠንቀቂያ ወረቀት ሲበትኑልን ነበር። ሲበትኑ የነበሩት ኻን ዩኒስ ላይ ነበር። ወደ ደቡባዊው የጋዛ ሰርጥ ክፍል እንድንሄድ ነው የሚሹት። ከሰሜን ተፈናቅለን ወደ ደቡብ መጥተናል። የት እንድንሄድ ነው የሚፈልጉት? እንዲህ ሆነን የት እንሂድላቸው? ከሰሜን ስንፈናቀል ይዘነው የወጣነው ገንዘብ አልቋል። ከዚህ በኋላ የትም ልንሄድን አንችልም።”

ኻን ዩኒስ ወደ ግብፅ ከሚያሻግረው ራፋህ 9.5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ደቡባዊ ጋዛ ከሚገኙ ከተሞች መካከልም ግዙፏ ናት። ከጦርነቱ በፊት የሕዝብ ቁጥሯ 400 ሺህ ነበር።

የሥፍራዋ ደማቅ የንግድ ከተማ ናት። ወደ ግብፅ የሚወስደው ጥንታዊ የንግድ መስመር መዳረሻም ሆና አገልግላለች።

ካርታ

የተፈናቃዮች መናኸሪያ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በከተማዋ ምዕራባዊ አቅጣጫ የስደተኞች መጠለያ ይገኛል። የከተማዋን ስም ይዟል። ይህ መጠለያ ከሜዲትራኒያን ባሕር ዳርቻ እና ከራፋህ 2 ኪሎ ሜትር ብቻ ርቆ የተተከለ ነው።

እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1948 በተቋቋመችበት ጊዜ ነው በርካታ ፍልስጤማዊያን ተፈናቅለው መጥተው እዚህ መጠለያ ሥፍራ ሕይወት የመሠረቱት።

የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤማዊያ ስደተኞች ድርጅት በዚህ መጠለያ ጣቢያ 90 ሺህ ተፈናቃዮች ተመዝግበው ይኖራሉ ይላል።

የትምህርት ሚኒስቴር አንደሚለው ደግሞ በኻን ዩኒስ ከተማ 60 ትምህርት ቤቶች እና 100 መዋዕለ ሕፃናት አሉ።

ከተማዋ ስድስት ገደማ ሆስፒታሎች አሏት። ዶክተሮች እንደሚሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተጎድተው ሕክምና በማግኘት ላይ ይገኛሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት፤ በደቡባዊ ጋዛ በተለይ ደግሞ በኻን ዩኒስ ከተማ የሚደረግ የምድር ጦር ዘመቻ ማለት በርካታ ሰዎች የጤና እርዳታ አያገኙም ማለት ነው ይላል።

ድርጅቱ በተለይ ደግሞ የናስር ሕክምና ማዕከል ጋዛ እና ዩሮፒያን ተሰኙት ዋና ሆስፒታሎች በሕክምና እርዳታ ፈላጊዎች ሊጨናነቁ እንደሚችሉ ይገምታል።

በቅርቡ የናስር ሜዳካል ኮምፕሌክስን የጎበኙት የዓለም ጤና ድርጅት ሠራተኞች በሆስፒታሉ ያለው ሁኔታ “አሳሳቢ ነው” ብለዋል።

የሆስፒታሉ ክፍሎች በበርካታ ሕክምና ፈላጊዎች ተጨናንቀዋል፤ ሌሎች ደግሞ መጠለያ በማጣታቸው ሆስፒታል ውስጥ አርፈዋል።

የድርጅቱ ቡድን እንደገለጠው ታካሚዎች ሆስፒታሉን ከመሙላታቸው ባለፈ የጤና ሠራተኞች ከአቅማቸው በላይ እየሠሩ ይገኛሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት አባላት አክለው እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት ከ1000 በላይ ታካሚዎች በሆስፒታሉ ሲገኙ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ማዕከሉን እንደመጠለያ እየተጠቀሙበት ነው።

ሆስፒታሉ 350 አልጋዎች ነው ያሉት። ጋዛ ዩሮፒያን ሆስፒታልም እንዲሁ 370 አልጋዎች ቢኖሩትም 1000 ሰዎች ሕክምና ያሻቸዋል፤ 70 ሺህ ገደማ ደግሞ ተጠልለውበታል።

ሁለቱ ሆስፒታሎች ከአቅማቸው ሦስት እጥፍ በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ነው እያስተናገዱ የሚገኙት።

በአንድ ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት የተጎዱ ሕጻናት በናስር ሆስፒታል ውስጥ
የምስሉ መግለጫ, በአንድ ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት የተጎዱ ሕጻናት በናስር ሆስፒታል ውስጥ

ይበቃል ማለት ይበቃል ነው

በከተማዋ ያሉ ነዋሪዎች ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ እንዲህ ያለ የአየር ጥቃት አጋጥሞን አያውቅም ይላሉ።

የእስራኤል ባለሥልጣናት በከተማዋ በርካታ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ለቀው እንዲወጡ የሚያስጠነቅቁ ወረቀቶችን በትነዋል።

በከተማዋ መሐል እና በሌሎችም አካባቢዎች የተበተኑ ወረቀቶች እንደሚጠቀሙት እስራኤል በቅርቡ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ በኻን ዩኒስ ላይ ለማካሄድ አቅዳለች።

በሥፍራው በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት የተቋቋመው የቢቢሲው ጋዛ ቱደይ ሬዲዮ ያናገረው አንድ ግለሰብ “ዛሬ ጠዋት ስንነሳ የእስራኤል ጦር በዙሪያችን ከባድ ዘመቻ መጀመሩን ስንሰማ ደንግጠናል” ይላል።

“እየወረደ ያለው ቦምብ ኃይለኛ መሆኑን ስንሰማ በጣም ደንግጠናል። ሕፃናት ፈርተዋል። ሴቶች እና የተጎዱ ሰዎች ደግሞ ተዳክመዋል። በድምፅ ማጉያ ወደ ደቡባዊ አቅጣጫ ሄደን እንድንሸሸግ ማስጠንቀቂያ ተነግሮናል። ሰላም ናቸው ወደተባሉት ሥፍራዎች ለመድረስ እጅግ አዳጋች ነው። ወደዚያ መጓዝ ለማይችሉ ሰዎች ትራንስፖርት የለም።”

አንድ ሕፃን “ይበቃል ማለት ይበቃል ነው። ያየነው ነገር ይበቃል። በጣም ፈርተናል። ከሆስፒታሉ አጠገብ ያለን አንድ ቤት አፈንድተውታል። በጣም ብዙ የተጎዱ ሰዎች አሉ” ሲል ለሬዲዮው ተናግሯል።

አንዲት ሴት ደግሞ ቀይ መስቀል እሷን እና ሌሎች የተጎዱ ሰዎችን ሰሜናዊ ጋዛ ከሚገኘው ኢንዶኔዢያን ሆስፒታል እንዳጓጓዛት ትናገራለች።

“እዚህ የመጣነው ሰላም ይኖራል ብለን ነው። ነገር ግን ከዛሬ ጠዋት [ሰኞ] ጀምሮ ቦምብ መውረዱን አላቆመም። የተጎዱ ሰዎች እጅግ በጣም ፍራቻ ውስጥ ናቸው” ትላለች።

“ቀይ መስቀልን እዚህ ባለንበት እንዲጠብቀን፤ የምንሄድበተ እንደሌለን ነግረናቸዋል። እዚህ ያለንበት ትምህርት ቤት እንኳ ቢተኩሱብን አንቀሳቀስም። በአምቡላንስ አሊያም በባስ አንድ ላይ መንቀሳቀስ ብቻ ነው የምንችለው።”

ኻን ዩኒስ ከሚገኘው ከዩሮፒያን ሆስፒታል አጠገብ የሚገኘው ዋነኛው መጠለያ ቀይ መስቀል እንዲደርስለት ጥሪ እያቀረበ ይገኛል።

“እዚህ መጠለያ የሚገኙ ሁሉ ሰላማዊ ዜጎችና የተጎዱ ናቸው። ሞት አምልጠው ነው እዚህ የመጡት። አንድ ሰው ምግብ እየበላ ሳለ በፍንጣሪ ተመትቷል። ቀይ መስቀል የተጎዱ ሰዎችን እንዲጠብቅ ጥሪ እናቀርባለን።”

ቢሆንም ግን የእስራኤል ጦር እና ሐማስ ተኩስ ለማቆም ስምምነት እስካልደረሱ ድረስ ቀይ መስቀል ይህን ሥፍራ የመጠበቅ አቅም የለውም።

ካርታ